‹‹የእኛ ቀጣዩ ሥራ ትግራይን መገንባት ነው። የትግራይ ሕዝብ ከፍተኛ ችግር ያለበትና በሬሽን የሚኖር ነው። ስለሆነም ቶሎ ብለን ሕዝባችን ከዚህ ችግር እንዲወጣ መደገፍ አለብን፣ ማቋቋም አለብን፣ የተሰደዱትን መመለስ አለብን።››
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶር)
በኅዳር ወር 2013 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው በክልሉ የተካሄደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ መጠናቀቁን የገለጹበትና ቀጣይ ትኩረታቸውን በተመለከተ፣ ለምክር ቤቱና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በቀጥታ ሥርጭት የገቡት ቃል ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ከተናገሩ ከሁለት ወራት በላይ የተቆጠሩ ሲሆን፣ ባለፉት ሁለት ወራት በትግራይ ክልል በሲቪል ነዋሪዎች እየደረሰ ነው የሚባለው ሰቆቃ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለመላው ሕዝብና ለምክር ቤቱ ከገቡት ቃል በተቃራኒ የዋለ ስለመሆኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተጠሪ የሆነው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ይፋ እያደረጋቸው የሚገኙ የምርመራ ሪፖርቶች ተጠቃሽ ናቸው።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመጉ) የሕግ ማስከበር ዘመቻው በይፋ ከተጀመረበት ዕለት አንስቶ እስከ ተጠናቀቀበት ወቅት ድረስ፣ በትግራይ ክልል ተፈጽመዋል ያላቸውን የሰብዓዊ መብቶች ጥስቶች በከፊል የሚያሳዩ የምርመራ ሪፖርቶቹን ከዚህ ቀደም ይፋ አድርጓል።
ከዚህ ሪፖርት በኋላም ኮሚሽኑ በትግራይ ክልል ያለውን የሰብዓዊ መብቶች አያያዝና አጠቃላይ የሰብዓዊ ሁኔታዎችን ባለው አቅም መከታተሉን አጠናክሮ እንደቀጠለ ያስታወቀ ሲሆን፣ በቅርቡ ካካሄዳቸው ምርመራዎች አንዱን ሐሙስ የካቲት 3 ቀን 2013 ዓ.ም. ለመገናኛ ብዙኃን ይፋ አድርጓል።
ኮሚሽኑ ከጥር 2 ቀን አንስቶ እስከ ጥር 15 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ በመቀሌ ከተማና በደቡባዊው የትግራይ ዞን አካል በሆኑት በአላማጣ፣ በመሆኒና በኩኩፍቶ ከተሞች ክትትል በማድረግ ያስተዋላቸውን አሰቃቂ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት በመሰነድ ለሕዝብና ለመንግሥት እንዲደርሱ አድርጓል።
ኮሚሽኑ ክትትል ባደረገባቸው አካባቢዎች ከፍተኛ ወታደራዊና ሲቪል አመራሮችን፣ የጤና ዘርፍ ሠራተኞችን፣ ነዋሪዎችን፣ ተጎጂዎችንና እንደ ጊዚያዊ መጠለያ በሚያገለግሉ የተለያዩ ትምህርት ቤቶች የሚገኙ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮችን በማነጋገር ይፋ ያደረገው ሰብዓዊ ቀውስ ዘግናኝ ከመሆኑ ባለፈ፣ ጥቃቶቹ እየተፈጸሙ ያሉት በክልሉ የተካሄደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ መጠናቀቁን መንግሥት በይፋ ከገለጸ በኋላ መሆኑ አሳሳቢ ያደርገዋል።
ኮሚሽኑ ከመረመራቸው ጉዳዮች አንዱ በሕፃናት ላይ እየደረሰ ያለውን ሞት፣ አካል ጉዳትና አሰቃቂ ቀውስ የሚመለከት ሲሆን፣ የኮሚሽኑ የምርመራ ቡድን በአይደር ሆስፒታል በመገኘት በሕክምና ክትትል ላይ የሚገኙ በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸው 20 ሕፃናት ሁኔታ የችግሩን መጠንና ስፋት ገላጭ ነው።
በሆስፒታሉ የሕክምና ክትትል ላይ ከሚገኙት መካከል የሦስት፣ የአምስትና የሰባት ዓመት ሦስት ሕፃናት ይኖሩበት በነበረው በሐውዜን ከተማ የሚገኝ መኖሪያ ቤታቸው ላይ በወደቀ ተወንጫፊ ከፍተኛ የአካል ጉዳት ደርሶባቸው በሆስፒታሉ ሕክምና እየተከታተሉ ቢሆንም፣ ሕፃናቱ ከደረሰባቸው ጉዳት ባለፈ ወላጅ አባታቸው የት እንደደረሱ እንደማያውቁ መረዳቱን በሪፖርቱ አመልክቷል።
በአይደር ሆስፒታል የሕፃናት ተኝቶ መታከሚያ ክፍል ተኝተው በመታከም ላይ ከነበሩት 20 ሕፃናት ውስጥ 16ቱ በጦርነት ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን፣ ሕፃናቱ ከፍተኛ የአዕምሮ ጭንቀትና ድንጋጤ (Trauma) ላይ መሆናቸውንም አመልክቷል።
በሆስፒታሉ ውስጥ ተኝተው በመታከም ላይ ከነበሩ ሕፃናት መካከል እጃቸውንና ዓይናቸውን ያጡ፣ በጭንቅላት፣ በሆድና በአጥንታቸው ላይ ጉዳት የደረሱባቸው ናቸው። ‹‹የ12 ዓመት ሕፃን የሆነው መሐሪ ፍፁም ከሚኖርባት ተንቤን አቅራቢያ የምትገኝ መንደር ከብቶች እያገደ በነበረበት ወቅት በተከሰተ ፍንዳታ የግራ እግሩን አጥቷል። መሐሪ የደረሰበትን ጉዳት አባቱ በሐዘን ሲያስረዱ፣ ‹እሱ ከብት እየጠበቀ በነበረበት ወቅት ሌሎች ሕፃናት ጓደኞቹ በጦርነቱ ተጥሎ ያልፈነዳ ተቀጣጣይ ፈንጂ አግኝተው በጨዋታ መልክ ፈንጂውን ሲቀጠቅጡ በመፈንዳቱ፣ ሁለቱ ሕፃናት ሕይወታቸው ሲያልፍ መሐሪን ጨምሮ ሦስት ሕፃናት ልጆች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል። መሐሪ ታፋው ላይ በፍንጣሪ ምክንያት ቆስሎ ነበር፣ ቁስሉ ቀላል መስሎን ቤት አቆየነው፣ ቁስሉ እየተባባሰ ቢሄድም ሐኪም ቤት መውሰድ አልቻልንም። አቢ አዲ የሚገኘው የጤና ተቋም ለወታደራዊ ተግባር እየዋለ ስለነበር ልጃችንን መቀሌ ድረስ ይዘን መጣን፣ ሆኖም ትራንስፖርት ስላልነበረና በፍጥነት ባለመድረሳችን ጉዳቱ ተባብሶ የልጃችን አንድ እግር ተቆረጠ› ብለዋል፤›› ሲል የኮሚሽኑ ሪፖርት ሁኔታውን ያስረዳል።
ከአይደር ሆስፒታል በተገኘው መረጃ መሠረት፣ በተለይ በሕፃናት ላይ ለደረሱት ጉዳቶች አንዱ ምክንያት በመሬት ውስጥ የተቀበሩና በሜዳ ላይ የተጣሉ ፈንጂዎች የሚደርስ ጉዳት ነው።
አንድ የሌላ ተጎጂ ሕፃን አባት ለኮሚሽኑ ሲያስረዱ፣ ‹‹ልጄ በዋና መንገድ ላይ እየተጓዘ በነበረበት ወቅት ፈንጂ በመርገጡ ምክንያት አንድ እግሩንና አንድ ዓይኑን አጥቷል፤›› ማለታቸውን የሚገልጸው ሪፖርቱ፣ የአካባቢው ነዋሪዎች ጦርነቱ ተፋፍሞ በነበረት ወቅት ሸሽተው በዋሻ ውስጥ ማሳለፋቸውንና ከጦርነቱ በኋላ ሲመለሱም፣ በተለይ ከዋና መንገድ ውጪ ፈንጂዎች ተቀብረው ማግኘታቸውን ለምርመራ ቡድኑ እንደገለጹ ሪፖርቱ ያስረዳል።
በተለይ በገጠር አካባቢዎች ይህንን ችግር በተደጋጋሚ መመልከታቸውን ኮሚሽኑ በሆስፒታል ውስጥ ያነጋገራቸው ታካሚዎችና ቤተሰቦቻቸው መናገራቸውንና የክልሉ ጤና ቢሮም ጦርነቱን ተከትሎ በየገጠሩ ያሉ የጤና ተቋማት አገልግሎት በማቆማቸው ምክንያት መቀሌን ጨምሮ ሕክምና ለማግኘት ወደሚቻልባቸው ከተሞች ለመጓጓዝ የትራንስፖርት እጥረት በመኖሩ፣ የተጎዱ ሰዎች ሕይወት እያለፈና ከባድ የአካል ጉዳት እየደረሰ እንደሆነ ለምርመራ ቡድኑ ማስረዳቱን ይጠቁማል።
በሕፃናት ላይ እየደረሰ ካለው ከፍተኛ ጉዳት እኩል በአሳሳቢ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሴቶችን አስገድዶ የመድፈር (ፆታዊ ጥቃት)፣ ሌላው በኮሚሽኑ ትኩረት ያገኘ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው።
‹‹በመቀሌ ከሚገኙ ሕክምና ባለሙያዎች እንዲሁም ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጤና ቢሮ በተገኙ መረጃዎች መሠረት፣ ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ 108 ሴቶች በመቀሌና በአካባቢው በሚገኙ ከተሞች ተገደው ተደፍረዋል፤›› በማለት ኮሚሽኑ በአካባቢው ተገኝቶ ስለደረሰው ፆታዊ ጥቃት ሪፖርት አድርጓል።
በክልሉ የተከሰተውን ጦርነትና የቀድሞውን መስተዳድር መፍረስ ተከትሎ ፆታዊ ጥቃቶች መፈጸማቸውን የሚያመለክተው የኮሚሽኑ ሪፖርት፣ ጥቃቱ የተፈጸመውም ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ እንደሆነ የገለጸ ሲሆን፣ ይህም የሚያሳየው ጥቃቱ የተፈጸመው የትግራይ ክልል የሕግ ማስከበር ዘመቻ መጠናቀቅና ቀጣይ ትኩረት የክልሉን ሕዝብ መልሶ ማቋቋም እንደሆነ በጠቅላይ ሚኒስትሩ በይፋ ከተገለጸ በኋላ መሆኑን ነው፡፡
ኮሚሽኑ ባቀረበው ሪፖርት እንደተመለከተው በመቀሌ ሆስፒታል 52፣ በአይደር ሆስፒታል 27፣ በአዲግራት ሆስፒታል 22፣ በውቅሮ ሆስፒታል ሰባት፣ በአጠቃላይ 108 የአስገድዶ መድፈር ጥቃቶች ለጤና ተቋማት ሪፖርት ተደርገዋል።
የፆታዊ ጥቃት ተጎጂዎች ወንጀሉን ለማሳወቅና የሕክምና ዕርዳታ ለማግኘት የሚሄዱባቸው እንደ ፖሊስ ጣቢያና ጤና ጣቢያ ያሉ ተቋማት በአንዳንድ አካባቢዎች ፈርሰው በመቆየታቸው፣ ሪፖርት የተደረጉ ጥቃቶች ቁጥር ትክክለኛውን የጉዳት መጠንና ስፋት እንደማያመላክትና የፆታዊ ጥቃት መጠኑ ከዚህ የበለጠ ሊሆን ይችላል ተብሎ እንደሚገመት ኮሚሽኑ በሪፖርቱ ገልጿል።
በኮሚሽኑ የተገለጸው የአስገድዶ መድፈር (ፆታዊ ጥቃት) በውስን ቦታ ላይ ብቻ የተፈጸመ ጥቃትን የሚያመለክት በመሆኑ፣ በመላው ትግራይ ክልል ውስጥ ምርመራ ቢከናወን የጥቃቱን ጥልቀትና ስፋት እንዲሁም ከጀርባው ያለውን ምክንያት ለመለየት እንደሚያስችል የሚገልጹ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ባለሙያዎች ያስረዳሉ።
ይህንን ማድረግ ከተቻለና ፆታዊ ጥቃቱ ሆን ተብሎ የተከናወነ ከሆነ፣ ዓለም አቀፍ የጦር ወንጀልን ሊያቋቁም እንደሚችልም ገልጸዋል።
አሁን ባለው ደረጃም ቢሆን የተገለጸው የጥቃት መጠን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሴት ሰብዓዊ መብቶች ራፖርተርን፣ እንዲሁም የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤትን ትኩረት ሊስብ እንደሚችልና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚሰየም ገለልተኛ አጣሪ ቡድን ወደ ትግራይ ክልል እንዲላክ ሊያስገድድ እንደሚችልም ጠቁመዋል።
ይሁን እንጂ በግጭት ወቅት በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን መርምሮ የጦር ወንጀልን ወይም በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀልን ማሟላታቸውን ለማረጋገጥ የሚደረገው ምርመራ አስቸጋሪ እንደሆነ የሚገልጹት ሪፖርተር ያነጋገራቸው ባለሙያው፣ ለዚህም ጥቃቱ የተፈጸመባቸው ሴቶች መገለል አልያም ፖለቲካዊ ጥቃት እንዳይደርስባቸው በመሥጋት ቃላቸውን እንደማይሰጡ ያስረዳሉ።
ከዚህም በተጨማሪ ጥቃት አድራሾቹ ጥቃቱን የፈጸሙት በአለቆቻቸው ታዘው ስለመሆኑ ለማገጋገጥ አስቸጋሪ እንደሚያደርገው፣ ይህ ካልተረጋገጠ ደግሞ በዓለም አቀፍ ወንጀል ለመጠየቅ እንደሚያዳግት ያክላሉ።
‹‹በበርካታ የዓለም አገሮች በነበሩ ግጭቶች ወይም ጦርነቶች ጀርባ ፆታዊ ጥቃቶችን መፈጸም እንደ አንድ የጦርነት መሣሪያ የሚያገለግል ነው። እንዲህ ዓይነት ጥቃቶችም በበርካታ አገሮች ይፈጸማሉ፡፡ ነገር ግን እስከ ዛሬ ድረስ በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት የጦር ወንጀል ክስ የተመሠረተባቸው በሩዋንዳ የዘር ፍጅት ወቅት የተፈጸሙትና ሌሎች ጥቂት ወንጀሎች ናቸው፤›› ብለዋል።
በትግራይ ክልል የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎችን እየፈጸሙ የሚገኙት የመከላከያ ሠራዊት አባላትና በክልሉ በተካሄደው ውጊያ ተሳትፈዋል የሚባሉት የኤርትራ ወታደሮች መሆናቸውን የተለያዩ መረጃዎች የሚያመለክቱ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ሪፖርት ግን ስለወንጀሉ ፈጻሚዎች ያለው ነገር የለም።
ይሁን እንጂ በክልሉ በሴቶችና ሕፃናት ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶችን በተመለከተ በመንግሥት ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባና ወንጀሉን የፈጸሙ አጥፊዎች በሕግ እንዲጠየቁ፣ እንዲሁም ጥቃት ለደረሰባቸው ሰዎች ተገቢውን ዕርዳታ ማድረግ እንደሚገባው በምክረ ሐሳቡ አሳስቧል።
‹‹እጅግ አሳዛኝና አሳሳቢው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ፆታዊ ጥቃት፣ በሕፃናት ላይ የደረሰው ጥቃትና ጉዳቱ ከዚህ የበለጠ እንዳይስፋፋ ልዩ ትኩረትና ጥረት ይሻል፤›› በማለት ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) አበክረው አሳስበዋል።
ኮሚሽኑ ተዘዋውሮ በጎበኛቸው የትግራይ ክልል አካባቢዎች የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት እጥረቱን ለመቅረፍ በመደረግ ላይ ያሉ እንቅስቃሴዎች አበረታች መሆናቸውን እንዳስተዋለ የገለጸ ቢሆንም፣ ካለው የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጎት አንፃር አሁንም ሰፊ ሥራን የሚጠይቅ እንደሆነ አመልክቷል።
በመሆኑም የመንግሥትና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ዕርዳታ ሰጪ ድርጅቶች የሰብዓዊ ድጋፍ ፍላጎቶች ባለባቸው አካባቢዎች ሁሉ ተንቀሳቅሰው ተገቢውን ዕርዳታ ማቅረብ እንዲችሉ የፌዴራል፣ የክልልና ወታደራዊ አመራሮች አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንዲያደርጉና የሰብዓዊ ዕርዳታ ሰጪ ድርጅቶቹ ለዕርዳታ ሥራው አስፈላጊ የሆነውን የባለሙያ ሠራተኞች ያለ አስተዳደራዊ መሰናከል ወደ ቦታው ለማሰማራት እንዲችሉ ሊደረግ እንደሚገባ አሳስቧል።
‹‹በትግራይ ክልል እየደረሰ ያለውን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት መጠን የሚያመላክቱ በርካታ ጥቆማዎችና መረጃዎች ቢኖሩም፣ የአካባቢው የፀጥታ ሁኔታ ገና ያልተረጋገጠ በመሆኑ፣ በሲቪል ሰዎች ላይ የደረሰውን የጉዳት መጠን ገና በተሟላ መንገድ ለማወቅ አልተቻለም። ሆኖም ኮሚሽኑ የማጣራትና የመመርመር ሥራውን ይቀጥላል፤›› ሲሉ ዋና ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።
መንግሥት በክልሉ ተፈጽመዋል ተብለው የቀረቡ ፆታዊ ጥቃቶችን በመመርመር የሕግ ተጠያቂነትን ለማረጋገጠጥ እንደሚሠራ የገለጸ ሲሆን፣ በተለይ በሴቶች ላይ የደረሱ ፆታዊ ጥቃቶችን የሚመረምር ቡድን በሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር መሪነት ተደራጅቶ ወደ ሥፍራው እንደሚላክም አስታውቋል።
ጠቅላይ ሚስትር ዓብይ (ዶ/ር) ባለፈው ሳምንት በአንድ የውጭ ድረ ገጽ ላይ ባቀረቡት ጹሑፍ፣ ‹‹በትግራይ ክልል የተካሄደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ በክልሉ ሕግና ሥርዓት በፍጥነት የማስከበር ዓላማን ለመተግበር የተቀረፀ ነው፣ በዚህም ተሳክቶልናል፤›› በማለት ገልጸዋል።
‹‹በዚህ ዘመቻ ሰብዓዊ ጉዳት እንዳይደርስ ካደረግነው ሰፊ ጥረት በተቃራኒ በትግራይ ክልል ነዋሪዎች ላይ የደረሰው ሞትና መከራ በግል ለእኔ፣ እንዲሁም በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ በሚገኙ ሰላም ወዳዶች ላይ ከፍተኛ ሐዘን ፈጥሯል፤›› ሲሉ አስረድተዋል።
ይህንን ሞትና መከራ በትግራይ ክልልም ሆነ በተቀረው ኢትዮጵያ እንዲያበቃ ማድረግ፣ አሁን ቀዳሚና ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጡት ኃላፊነታቸው እንደሆነ ገልጸዋል።