በትግራይ ክልል የደረሱ የመብት ጥሰቶችን የሚያመላክቱ በርካታ ጥቆማዎች ቢኖሩም፣ የአካባቢው የፀጥታ ችግር ባለመረጋጋቱ በሲቪሎች ላይ የደረሰውን ጉዳት መጠን ማረጋገጥ እንዳልቻለ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ገለጸ፡፡

ከጥር 2 እስከ ጥር 15 ቀን 2013 ዓ.ም. በመቀሌ ከተማና በደቡባዊ የትግራይ ዞን አላማጣ፣ መሆኑና ኩኩፍቶ ከተሞች የሚገኙ ወታደራዊና ሲቪል አመራሮችን፣ የጤና ዘርፍ ሠራተኞችን፣ ነዋሪዎችን፣ ተጎጂዎችንና ተፈናቃዮችን ማነጋገሩን ኮሚሽኑ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

ኮሚሽኑ በአካል ተገኝቶ ክትትል ለማድረግ ባለመቻሉ በበርካታ የትግራይ ክልል አካባቢዎች የሰው ሕይወት ማለፉን፣ የአካልና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት መድረሱን፣ ፆታን መሠረት ያደረገ ጥቃት፣ ዘረፋና ሌሎች የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት መፈጸማቸውን መረጃዎች እንደደረሱት በመግለጫው አመላክቷል፡፡

ከመቀሌ፣ ከአዲግራት፣ ከአይደር እንዲሁም ከውቅሮ ሆስፒታሎች በተገኘ መረጃ መሠረት ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ 108 የአስገድዶ መድፈር ጥቃቶች እንደተፈጸሙ፣ ኮሚሽኑ ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡

ኮሚሽኑ የመመርመርና የማጣራት ሥራው እንደ ቀጠለ ያመለከተ ሲሆን፣ ‹‹እጅግ አሳዛኝና አሳሳቢ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት፣ ፆታዊ ጥቃት፣ በሕፃናት ላይ የደረሰው ጥቃትና ጉዳት ከዚህ የበለጠ እንዳይሰፋ ልዩ ትኩረትና ጥረት ያሻል፤›› በማለት ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ማሳሰባቸውን ገልጿል፡፡

ኢሰመኮ በአይደር ሆስፒታል ባደረገው ጉብኝት ተገኝተው በመታከም ከነበሩ 20 ከፍተኛ የአዕምሮ ጭንቀትና ድንጋጤ ታካሚ ሕፃናት መካከል ፣16 ያህሉ በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው እንደሆኑ በመግለጫው አመላክቷል፡፡

በሆስፒታሉ ተኝተው ከሚታከሙ ሕፃናት መካከል እጃቸውን፣ እግራቸውንና ዓይናቸውን ጨምሮ የአካላቸውን ክፍል ያጡ የተለያዩ ዓይነት የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሕፃናት እንደሚገኙና ለደረሰባቸው ጉዳት አንዱ ምክንያት በመሬት ውስጥ ተቀብረው የነበሩና በሜዳ ላይ የተጣሉ ፈንጂዎች እንደሆኑ ገልጿል፡፡

በመቀሌና በሌሎች ኮሚሽኑ በተዘዋወረባቸው አካባቢዎች የሰብዓዊ ዕርዳታ በማድረስ ረገድ አበረታች ዕርምጃዎች ቢኖሩም፣ አስቸኳይ የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጎቱ እንዳልተሟላ ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡

ከሌሎች አካባቢዎች ወደ መቀሌ የተፈናቀሉ ሰዎች የምግብ፣ የንፁህ መጠጥ ውኃና የጤና አገልግሎት አቅርቦት እጥረት እንዳለ የተገለጸ ሲሆን፣ በአንዳንድ አካባቢዎች ያለው የፀጥታ ሁኔታና የጤና ተቋማት አገልግሎት መቋረጥ ተጎጂዎችና የተጎጂ ቤተሰቦች የሕክምና ዕርዳታ ለማግኘት ረዥም የእግር ጉዞ እንደሚያደርጉ አክሎ ገልጿል፡፡

ኮሚሽኑ ከሦስት ወራት በላይ በዘለቀው የሕግ ማስከበር ዘመቻ የመሠረታዊ ልማት፣ የማኅበራዊና አስተዳደራዊ አገልግሎቶችን በአፋጣኝ ወደ ሥራ የመመለስ ተግባር ልዩ ትኩረት እንደሚሻ አሳስቧል፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *