ሴቶች በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ አነስተኛ በመሆኑ፣ በመጪው አገራዊ ምርጫ የመሳተፍና በላይኛው የሥልጣን እርከን የመወከል ዕድላቸው ሊቀንስ እንደሚችል ተለገጸ፡፡

የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት (ኢሴማቅ) ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሥርዓተ ፆታ እኩልነትና ሴቶችን ከማብቃት ክፍል (ዩኤን ውሜን) ጋር በመተባበር፣ ‹‹የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን በማጠናከር የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማጎልበት›› በሚል መሪ ቃል ባዘጋጀው የምክክር መድረክ፣ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ  እንዲጎለብት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል፡፡

‹‹ሴቶች መራጭ፣ ተመራጭ፣ ታዛቢና አጀንዳ እንዲሆኑ እንፈልጋለን፤›› ያሉት የኢሴማቅ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሳባ ገብረ መድኅን፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችና በሴቶች ዙሪያ የሚሠሩ ተቋማት ይህንን ሊያደርጉ ይችላሉ ብለዋል፡፡

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምርጫ ላይ እንዲሠሩ መፈቀዱን በመግለጽ፣ የሲቪል ማኅበራት በተናጠል ሆነው ተደጋጋሚ የምርጫ ሥራ ላይ እንዲሳተፉ በመቀናጀትና መርሐ ግብር በማውጣት ለመሥራት ኢሴማቅ ውይይቶችን እያደረገ መሆኑንም አክለዋል፡፡

በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ የሴቶች ውክልና አነስተኛ መሆን በፓርላማም ሆነ በካቢኔ ሴቶችን ለማምጣት እክል ሊሆን እንደሚችል የገለጹት ወ/ሮ ሳባ፣ በምርጫ ቦርድ ሕግ ላይ የተቀመጠው የፖለቲካ ፓርቲዎች ሴቶችን ሲያሳትፉ የሚገኙት ጥቅም ብዙም ሲያበረታታ ባለመታየቱ፣ ሌሎች መንገዶችን መፈለግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ፓርቲዎች ሴቶችን በማሳተፋቸው እንደሚጠቀሙ ማሳወቅና አቅም መስጠትም ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ያለው የፖለቲካ ምኅዳር ሴቶችን የማይጋብዝ ከሆነ ሴቶች ተሳተፉ ቢባሉም እንደማይመጡ፣ በመሆኑም ተመራጮች ላይ ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ፓርቲዎቹ፣ፕሮግራሞቻቸውና የፆታ ፖሊሲዎቻቸው ላይ ጭምር መሥራት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

የሴቶች የፖለቲካ ውክልናን አስመልክቶ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች በትንሹ ምን ያህል ሴት ዕጩዎች ማምጣት እንዳለባቸው የምርጫ ሕጉ ላይ እንዲገባ ከዚህ ቀደም ሐሳብ ቢቀርብም ተቀባይነት እንዳላገኘ የገለጹት የገለጹት ወ/ሮ ሳባ፣ ይህ ካልሆነ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ላይ መሥራትና እንዲያምኑበት ማድረግ እንዲሁም ማበረታቻ  መስጠት ይገባል ብለዋል፡፡

‹‹የሴቶች የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ አለመገኘት እኛም ያሳስበናል፤›› በማለትም፣ ሴቷ የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ ካልገባች መወከል የምትችልበት መድረክ ስለሌለ ፓርቲዎች ሴቶችን እንዲያሳትፉ የጀመሩትን እንቅስቃሴ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *