የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስዳደራዊ በደል ደርሰውብናል የሚሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች አቤቱታዎችና ቅሬታዎች ቁጥር መጨመሩን አስታወቀ፡፡
ቦርዱ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ቅሬታዎች እየተቀበለ መሆኑን የገለጸው፣ ሰሞኑን ከፖለቲካ ፓርቲዎች ከፍተኛ አመራሮች ጋር በምርጫ ጉዳዮች ላይ በሐያት ሪጀንሲ ሆቴል ባደረገው ውይይት ነው፡፡
የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ስለጉዳዩ ሲያብራሩ፣ በፓርቲዎች የሚነሱ አቤቱታዎች በጣም ብዙ እንደሆኑና በተለይም ቦርዱ ወደ ምርጫ ዝግጅት ከገባ በኋላ እየመጡ ያሉትን ቅሬታዎችንና አቤቱታዎችን ለመለየትና ለመምራት አስቸጋሪ እንደሆነባቸው ጠቁመዋል፡፡
‹‹በተለያዩ ጊዜያት በተናጠል መፍትሔ ለመስጠት የተሄደባቸው አሉ፡፡ ብዙ ባይባልም በጥቂቱ ተሳክቶልናል፤›› ሲሉ ወ/ሪት ብርቱካን ገልጸዋል፡፡ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝና የሕግ አካሄድ በተለያዩ ጊዜያት እስር ቤት የገቡና በቁጥጥር ሥር የዋሉ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮችና አመራሮችን በተመለከተ ጥያቄና ማሳሰቢያ ቢቀርብም፣ ምላሽ እንዳልተገኘ ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ውይይት ተደርጎ ጭምር የማይፈታ ችግር ቦርዱን እየገጠመው መሆኑን፣ አብዛኛውን ጊዜ የብዙዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉዳይ በዝርዝር ቢቀርብም፣ በፍርድ ቤት ተይዟል የሚል መልስ ከገዥው ፓርቲ እንደሚቀርብ ወ/ሪት ብርቱካን አክለው ገልጸዋል፡፡
‹‹ነገር ግን እንደ አንድ ሕገ መንግሥዊ ተቋም ምርጫ ቦርድ የራሱ ሥራ አለው፡፡ ፍርድ ቤትም የራሱ ኃላፊነትና ተግባር አለው፡፡ ስለዚህ ፍርድ ቤት ያለውና የሚካሄደው ነገር ትክክል ነው ወይም አይደለም ለማለትና ለመጠየቅ ሥልጣንም ፍላጎት የለንም፤›› ብለዋል፡፡
‹‹ስለሆነም በፍርድ ቤት ጉዳይ ምንም ማለት ስለማንችል፣ ፓርቲዎች በጣም ብዙ አባላቶቻችን ታስረውብናል ብለው በተደጋጋሚ አቤቱታ ቢያቀርቡም መፍትሔ መስጠት አልቻልንም፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ለአብነትም በውይይቱ የባልደራስና የኦጋዴን ነፃነት ግንባር አመራሮች ተወካዮቻቸውና አመራሮቻቸው ስለታሰሩባቸው መንቀሳቀስ አለመቻላቸውን ተናግረዋል፡፡
የቦርድ ሰብሳቢዋ ግን ተፎካካሪ ፓርቲዎችና ገዥው ፓርቲ በመሀላቸው ያለውን ችግር ተመካክረው መፍታት ቢችሉ መልካም ነው ብለዋል፡፡
የሦስትዮሽ አሠራር መዘርጋቱን የገለጹት ሰብሳቢዋ፣ ወደ ፍርድ ቤት ከመሄድ በፊት ፓርቲዎችን በማገናኘት ችግሮችን ለመፍታት እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል በኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) እና በኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አባላቶች እንደታሰሩባቸውና ቢሮ እንደተዘጋባቸው አቤቱታዎች በሰፊው እንደሚቀርቡ ወ/ሪት ብርቱካን ጠቁመዋል፡፡
‹‹ነገር ግን ቢሮዎችን በተመለከተ ገዥው ፓርቲ ቢሮዎችን አልዘጋሁም ብሏል፤›› ካሉ በኋላ፣ ‹‹ከቢሮ መዘጋት ጋር በተገናኘ የሚነሱ ችግሮችን ከመፍታት አንዳንዴም ቢሮ መስጠት ይቀለን ነበር፤›› ሲሉ ወ/ሪት ብርቱካን ተናግረዋል፡፡
ቦርዱ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች የሚነሱ ችግሮችን በተለይም ከቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ ከኦሮሚያ፣ ከደቡብ ክልሎች የሚነሱ አቤቱታዎችን ለመፍታት ምርጫ ቦርድ የተካተተበትና ገዥው ፓርቲ ያለበት የሦስትዮሽ ንግግር እንዲያደርጉ በማድረግ ችግሮችን የመፍታት ሥራ እየተከናወነ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
አራት ወራት ያህል የቀረውን መጪው አገራዊ ምርጫ ለማካሄድ ቦርዱ ቅድመ ዝግጅቶችን አጠናቆ፣ ወደ ምርጫ ጣቢያ መላክ ያለባቸውን የምርጫ ቁሳቁሶች መላክ መጀመሩን አስታውቋል፡፡
ከትግራይ ክልል ውጪ ሃምሳ ሚሊዮን ያህል መራጮች ይሳተፉበታል ተብሎ የሚጠበቀው አገራዊ ምርጫ ባሉ ለ49,407 የምርጫ ጣቢያዎች የሚያገለግሉ ጄኔሬተሮች፣ ላፕቶፕ ኮምፒዩተሮችና ፕሪንተሮች ማሠራጨት እንደተጀመረ ወ/ሪት ብርቱካን አስረድተዋል፡፡
ቦርዱ ለምርጫ ማስፈጸሚያ የተለያ ቁሳቁሶችን፣ የመከላከያ ተሽከርካሪዎችን፣ አውሮፕላኖች፣ ትንንሽ መኪኖች፣ ጀልባዎችና የጋማ ከብቶችን ጭምር በመጠቀም ሥርጭቱን ያካሂዳል ተብሏል፡፡
ከ200 በላይ የውጭ አገርና 111 የአገር ውስጥ የምርጫ ታዛቢዎች ቦርዱ ዘንድ ቀርበው እንዳመለከቱ የተገለጸ ሲሆን፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር በመሆን የጋራ መግባቢያ ሰነድ ተዘጋጅቶ በቅርቡ እንደሚፈረም በቦርዱ የውጭ ግንኙነትና የሥርዓተ ፆታ አካታችነት ኃላፊ ወ/ሮ ማህሌት ጥሩነህ አስታውቀዋል፡፡