በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ በምትገኘው የማይካድራ ከተማ ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም. በንፁኃን ዜጎች ላይ በተካሄደው ጭፍጨፋ በተለያዩ አካላት የተገለጸው ቁጥር፣ የተጋነነ ነው ሲል የፌዴራል ዋና ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አስታወቀ፡፡

ከጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በትግራይ ክልል በተካሄደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ የነበረውን አጠቃላይ ሁኔታ እንዲያጠና ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከጠቅላይ ዓቃቤ ሕግና ከአገር መከላከያ ሚኒስቴር የተውጣጣው ግብረ ኃይል የመጀመርያ የሆነውን ባለ 90 ገጽ ሪፖርት ይፋ አድርጓል፡፡

ምክትል ዋና ዓቃቤ ሕግ አቶ ፈቃዱ ፀጋና የፌዴራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዘለዓለም መንግሥቴ፣ ሪፖርቱን ለጋዜጠኞች ዓርብ ጥር 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ይፋ አድርገዋል፡፡

አቶ ፈቃዱ በማይካድራ በተከናወነው ጭፍጨፋ በተለያዩ አካላት ሲነገር የነበረው የሟቾች ቁጥር አንዱ ወደ ላይ አንዱ ወደ ታች ዓይነት በሆነ አገላለጽ የተዛባ መረጃ እንደነበር፣ በግብረ ኃይሉ የተገኘው የምርመራ ውጤት አነስተኛ የሟቾች ቁጥር ማሳየቱን ጠቁመዋል፡፡

ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ወደ ማይካድራ 14 የሕክምና ዶክተሮችንና ሌሎች አጋዥ ባለሙያዎችን ጨምሮ፣ 23 ሰዎችን የያዘ የአስከሬን ምርመራ የሚያደርግ ቡድን ወደ ቦታው መላኩን አቶ ፈቃዱ ተናግረዋል፡፡

በማይካድራ ለአንድ ወር ያህል ቆይታ ያደረገውና በቪዲዮ የታገዘ የአስከሬን ምርመራ ያደረገው የሐኪሞች ቡድን ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ ምንም እንኳ መቶ በመቶ ማረጋገጥ ባይቻልም 98 በመቶ በሚጠጋ ሁኔታ የሞቱትንና የተቀበሩትን ዜጎች መለየት መቻሉንና ውጤቱ ቀድሞ ከተገለጸው የተጋነነ ቁጥር ጋር እንደማይጣጣም ገልጸው፣  ነገር ግን የመጨረሻ ምርመራው እስኪጠናቀቅ የሟቾችን ቁጥር ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡

በምርመራው ወቅት የተገኙ መቃብሮች በተለይም ከአቡነ አረጋዊ ቤተ ክርስቲያን 85 መቃብሮች፣ በመስጊድ ሁለት፣ ስድስት የጅምላ መቃብሮችና 24 በእርሻ ቦታ ተቀብረው የተገኙ በአጠቃላይ 117 የአስከሬን ጉድጓዶች ተከፍተው ምርመራ እንደተደረገባቸው ተገልጿል፡፡

በዚህም በምርመራ የተረጋገጠው ከዚህ በፊት በተለያዩ አካላትና በሚዲያ ተቋማት ሲነሳ እንደነበረው  የሟቾች ቁጥር የተጋነነ አይደለም ሲሉ አቶ ፈቃዱ አመላክተዋል፡፡

ለአብነትም 57 አስከሬኖች ተቀብረውበታል የተባለው ጉድጓድ ተቆፍሮ ሲታይ፣ 23 አስከሬኖችና ሌላ አንድ የሰው እጅ መገኘቱን ምክትል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ገልጸዋል፡፡

በቀደሙት ሪፖርቶች የተጋነኑ ቁጥሮች እንዲወጡ ምስክርነት ሰጥተው የነበሩ ግለሰቦችን በድጋሚ የአስከሬን መቃብሮች ተከፍተው ሲመለከቱ፣ መጀመርያ መረጃ ሲሰጡ አስከሬኖቹ ሽታ ስለነበራቸው ቀርበው በማለመቁጠራቸው ግምታዊ ቁጥሮችን ይጠቀሙ እንደነበር መናገራቸውን አቶ ፈቃዱ አስረድተዋል፡፡

ከ98 በመቶ በላይ የአማራን ብሔር መሠረት አድርጎ የተደረገ ጭፍጨፋ እንደነበር የገለጹት አቶ ፈቃዱ፣ ግድያው ዘግናኝና ኢሰብዓዊነት የታየበት ነበር ብለዋል፡፡

የሟቾቹን ቁጥር አስመልክቶ ኅዳር መጨረሻ አካባቢ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የቀረበው ቁጥር ቢያንስ 600 እንደሆነ የሚያሳይ ሲሆን፣ የአስቸኳይ ጊዜ መርማሪ ቦርድ የገለጸው የሟቾች ቁጥር ደግሞ ወደ 700 እንደሚደርስ መረጃ ማውጣቱ ይታወሳል፡፡

በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የሚመራው የምርመራ ግብረ ኃይል ምርመራውን በቅርቡ አጠናቆ፣ ሙሉ መረጃውን ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡

የግብረ ኃይሉ የመጀመርያ ሪፖርት እንደሚያሳየው በትግራይ ክልል ከፍተኛ አመራሮችና በቀድሞ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች የተዋቀረ ቡድን፣ አገረ መንግሥቱን በሦስት ወራት በመገልበጥ ሥልጣን ላይ ለመውጣት ትልቅ ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን አመልክቷል፡፡

በተለይም የመከላከያ ሚኒስቴር የሚመስል የትግራይ የመከላከያ ካውንስል በሚል በማዋቀር ሲሠራ እንደነበር አቶ ፈቃዱ አክለው ተናግረዋል፡፡

የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩት ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) የፈረሙበት፣ የመከላከያ ሠራዊቱን አደረጃጀት የሚመስልና የሚመጥን አደረጃጀት መመደባቸው በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

የማዕከላዊ ኮማንዱን እንዲመሩ ሌተና ጄኔራል ታደሰ ወረደ በዋና አዛዥነት፣ ሜጄር ጄኔራል ምግባር ኃይለይ በምክትል አዛዥነት፣ ሜጄር ጄኔራል ኢብራሂም አብዲል ጀሊል የሎጂስቲክስ ኃላፊ፣ ሜጄር ጄኔራል ዮሐንስ ወልደ ጊዮርጊስ፣ ሜጄር ጄኔራል ብርሃነ ነጋሽና ሜጄር ጄኔራል ተክላይ አሸብር በምክትል ኃላፊነት መመደባቸው በሪፖርቱ ገልጿል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር እንዳሉት፣ የቀድሞው የክልሉ ፕሬዚዳንት ለቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕና ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ለአውሮፓ ኅብረት፣ ለፈረንሣይ፣ ለሌሎች አገሮችና ተቋማት የትብብር ደብዳቤ ጽፈዋል፡፡

እነዚህን የአገር ሉዓላዊነት የሚደፍሩ ሥራዎችና የውጭ አገር ግንኙነቶች፣ ከአዲስ አበባ በአዲስ ዓለም ባሌማ (ዶ/ር) በኩል ሪፖርት ይደረግ እንደነበር በመግለጫው ተገልጿል፡፡

የሕወሓት ከፍተኛ አመራሮች ከአዲስ አበባ ወደ መቀሌ ከሄዱበት 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ሲያደርጉት የነበረው ወደ ሥልጣን የመመለስ ዕቅድ፣ በከፍተኛ ሁኔታ ሲሠራበት እንደነበር ተገልጿል፡፡

በተለይ ክልሉ ከ2010 ዓ.ም. በፊት በየዓመቱ 450 ያህል ቁጥር ያላቸውን የልዩ ኃይሉ አባላት ሲያሠለጥን እንደነበር፣ ከ2010 በኋላ በዓመት 5,000 የሚደርሱ የልዩ ኃይል አባላትን እንደሚያስመርቅና ከ2010 ዓ.ም. በፊት 5,000 የሚሊሻ አባላትን ማስመረቁን፣ በ2012 ዓ.ም. ከ37,000 በላይ እንዳስመረቀ ተገልጿል፡፡

በአገር ክህደት ወንጀል፣ የፌዴራል ሥርዓቱን አደጋ ላይ በመጣልና በአገር ሉዓላዊነት የተቀጣ የሽብር ቡድን በሚል የተጠረጠሩ አካላት ሲመረምር የነበረው ግብረ ኃይሉ፣ በአጠቃላይ 253 በወንጀል የሚፈለጉና የተጠረጠሩ፣ ነገር ግን ጡረታ የወጡ የቀድሞ የመከላከያ መኮንኖችንና ከፌዴራል ፖሊስ በጡረታ የተገለሉና 96 የሚሆኑ የሕወሓት ቁልፍ አመራሮች በድምሩ 349 ተጠርጣሪዎች ላይ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ የማደን ሥራ መጀመሩን ገልጿል፡፡

ከተጠርጣዎቹ መካከል 124 የሚሆኑት በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አቶ ዘለዓለም ገልጸው፣ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ከ680 በላይ የሰውና የሰነድ ምስክር በተጨባጭ መገኘቱን፣ ተጠርጣሪዎቹ በተለያዩ ክልሎች እንዲፈጸሙ ተብለው የተቀረፁ የተለያዩ ፕሮጀክቶች እንደነበራቸው አመላክተዋል፡፡

ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. የተካሄደውን ጥቃት ተከትሎ በትግራይ ክልል በተለያዩ ወንጀሎች ተፈርዶባቸው በማረሚያ ቤት የነበሩ ከ13,000 በላይ ታራሚዎችን ከተለያየ ቦታ አምጥተው መቀሌ ውስጥ እንደበተኗቸው ተገልጿል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በክልሉ በዝርፊያና በአስገድዶ መድፈር እንቅስቃሴዎች መታየታቸው፣ ከታራሚዎች መለቀቅ ጋር ሊገናኝ እንደሚችልም በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *