ግጭቶች ፣ የጎርፍ መጥለቅለቅ ፣ የአንበጣ መንጋ ፣ ኮቪድ 19 እና ሌሎችም ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች አገራችንን በማወክ ተከታታይ ሰብአዊ ቀውስ አስከትለዋል፡፡ ኢትዮጵያ በቅርቡ የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ በአግባቡ ሳትወጣ ትግራይ ፣ ኦሮሚያ ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ደቡብ ክልሎችን ያዳረሰና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይዎት አደጋ ላይ የጣለ ውስጣዊ ግጭትና ብጥብጥ አስተናግዳለች፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ በአገር ውስጥ የተፈናቀሉ ዜጎች፣ ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ ሕፃናት፣ ሴቶች፣ አዛውንቶች፣ አካል ጉዳተኞች እና ቁስለኞች የግጭት አካባቢዎችን እና ሌሎች የተፈጥሮ አደጋዎችን በመሸሽ ቤታቸውን ለቀው ለመሰደድ ተገደዋል፡፡

ሁላችንም እንደምናውቀው የ2012/13 ዓ.ም የአንበጣ ወረርሽኝ እስከ ጥቅምት አጋማሽ ድረስ በመቶ ሺዎች ሄክታር የሚቆጠር የሰብል እና የግጦሽ መሬቶች ላይ ጉዳት አድርሷል፡፡ ይህም በአማራ፣ በትግራይ ፣ በኦሮሚያ ፣ በድሬዳዋ ፣ በአፋር ፣ በሐረሪና በሶማሌ ክልሎች ሰብዓዊ ድጋፍ የሚፈልጉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወገኖችን ለጉዳት አጋልጧል፡፡ የብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን እ.ኤ.አ. በመስከረም 2020 ያወጣው ሪፖርት እንደሚያመለክተው የጎርፍ አደጋም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ጎድቷል፡፡ ከዚህ ውስጥ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በመላ አገሪቱ ተፈናቅለዋል፡፡ የኮቪድ -19 ወረርሽኝን አስመልክቶ በኢትዮጵያ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ላይ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ የጤና፣ የትምህርት እና ፖለቲካዊ ተፅእኖዎችን እያደረሠ ይገኛል፡፡ በእነዚህ ሁሉ በተወሳሰቡ ተከታታይ የሰብአዊ ቀውሶች ላይ የተጨመረው የቅርብ ጊዜ ግጭት እና ሁከትም የሰብዓዊውን ምላሽ ውስብስብ አድርጎታል፡፡

አደጋዎች ባሉበት እና ሰብዓዊ ቀውስ በሚከሰትበት ቦታ ሁሉ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ሁል ጊዜም ቀድሞ ይገኛል! ስለሆነም በጎ ፈቃደኞቹንና ሠራተኞቹን በማስተባበር ህይወትን ለማዳን እና ኑሮን ከመጠበቅ አንፃር የተለያዩ ሰብአዊ አገልግሎቶችን ይሰጣል፡፡ ማህበሩ በ2012 የበጀት ዓመት አምቡላንስ እና የመጀመሪያ ህክምና እርዳታ አገልግሎቶች፣ የምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ዕቃዎች ድጋፍ፣ የስነ-ልቦናና ማህበራዊ ድጋፍ፣ የቅድሚያ ማገገም እና የመልሶ ማቋቋም ድጋፍ፣ የተጠፋፉ ቤተሰቦችን ማገናኘት፣ የኮቪ -19 ዝግጁነት እና ምላሽ ስራዎችን አከናውኗል፡፡ በአጠቃላይ በ2012 ዓ.ም ማህበሩ ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ከ36 ሚሊዮን ለሚበልጡ ግለሰቦች ድጋፍ አድርጓል፡፡ በ2013 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ደግሞ በ70 ሚሊዮን ብር ወጪ 138 ሺህ ሰዎችን ደርሷል፡፡

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ላለፉት ሁለት ወራት የተከሰቱትን ግጭቶች ተከትሎ በትግራይ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች እና ኦሮሚያ በ30 ሚሊዮን ብር ወጪ ከ200 ሺህ ለሚበልጡ ሰዎች የህክምና፣ የምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች አቅርቦቶች፣ መጠለያ አቅርቦት፣ የስነ-ልቦናና ማህበራዊ ድጋፍ፣ መልሶ የማቋቋምና የተጠፋፉ ቤተሰቦች የማገኛኘት አገልግሎቶችን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ ማህበሩ 300 የበጎ ፈቃደኞች እና ሠራተኞችን እንዲሁም 100 አምቡላንሶችን በማሰማራት በቅርቡ በተከሰተው የአንበጣ መንጋ እና ከዚያ በኋላ በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑትን ወገኖች ህይወት ለማዳን እና ኑሯቸውን መልሶ ለማቋቋም በንቃት ተሳትፏል፡፡ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በታህሳስ 2013 ዓ.ም አጋማሽ ላይ በምዕራብ፣ ደቡብ እና መካከለኛው ትግራይ፣ በሰሜን ጎንደር፣ በሰሜን ወሎ፣ በመተከል፣ በኮንሶ እና ቤንቺ ሸካ አካባቢዎች ባካሄደው የዳሰሳ ጥናት አጠቃላይ እና ተጨማሪ ምግብ የሚፈልጉ ከ 2.53 ሚሊዮን በላይ ተጋላጭ ሰዎች መኖራቸውን ለማወቅ ችሏል፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች መጠለያ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች፣ መተዳደሪያ እና ቅድመ ማገገም፣ የመጀመሪያ ህክምና እርዳታና አምቡላንስ አገልግሎቶች፣ የስነ-ልቦና እና መልሶ ማቋቋም እንዲሁም የቤተሰብ ማገናኘት ድጋፎች፣ በተጨማሪም የጤና ማዕከል ተቋማትን እና የቀይ መስቀል ቅርንጫፎችን ጥገና እና መልሶ መገንባት ያስፈልጋል፡፡ ለእነዚህ አካባቢዎች በጠቅላላ የሚገመተው የገንዘብ ፍላጎት ከ9 ቢሊዮን ብር በላይ ነው ፡፡

ማኅበሩ በትግራይ ክልል በግጭት ለተጎዱ ወገኖች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ቀጥሏል

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር (ኢቀመማ) በትግራይ ክልል ተከስቶ በነበረው ግጭት ለተፈናቀሉ እና ጉዳት ለደረሰባቸው 2000 ወገኖች ከብር 3 ሚሊዮን በላይ ወጪ በማድረግ ልዩ ልዩ ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች ድጋፍ አድርጓል፡፡

ማኅበሩ በትግራይ የተለያዩ አካባቢዎች ካደረገው ድጋፍ መካከል ብርድ ልብስ፣ ምንጣፍ የመመገቢያ እና የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች እና መሠረታዊ መድኃኒት ድጋፍ ይገኝበታል፡፡

ኢቀመማ ግጭቱ ከተከሰተ በኋላ ከዓለም ዓቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ እና ከሌሎች ተባባሪ አካላት ጋር በመሆን ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች አስቸኳይ ሠብዓዊ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ ከዚህም መካከል የመጀመሪያ ደረጃ የህክምና እርዳታ፣ የአምቡላንስ አገልግሎት፣ የተጠፋፉ ቤተሰቦችን የማገናኘት፣ የተለያዩ የምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች ድጋፍ ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ ማኅበሩ በመቀሌ ከተማ ተፈጥሮ የነበረውን የንፁህ መጠጥ ውሀ እጥረትን ተከትሎ ለከተማዋ ነዋሪዎች መጠጥ ውሀ ድጋፍ እንደተደረገ ይታወቃል፡፡

ሰብዓዊ ድጋፍ ለምታደርጉ ፡ – በአይነት ድጋፍ ማድረግ ለምትፈልጉ የብሔራዊ ማኅበሩ ዋና ማስሪያ ቤት እና በሁሉም ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች፣ በገንዘብ የሰብአዊነት ድጋፍ ፈንድ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሒሳብ ቁጥር 1 000 000 902 008 ፣ እንዲሁም በኦንላይን ልገሳ ለማድረግ የማህበሩ ሊንክ https://donate.bankofabyssinia.com/dashboard/ercs.php

ለተጨማሪ መረጃ፡-

ዶ/ር ሰለሞን አሊ – የኮሙኒኬሽን ኃላፊ – +251 911 252428
አቶ መሐመድ ዳዳ – የበጎ ፈቃደኞች አመራርና ቅርንጫፍ ልማት ኃላፊ – +251 911 411719

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *