የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) በትግራይ ክልልና አዋሳኝ አካባቢዎች በነበረው ሕግ የማስከበር ሒደት ምክንያት፣ ባልታጠቁና ሰላማዊ በሆኑ ሰዎች ላይ የተፈጸመው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰትና አስቸኳይ ሰብዓዊ ድጋፍ የሚሹ ወገኖች ጉዳይ ከፍተኛ ሥጋት እንዳሳደረበት ገለጸ፡፡
ኢሰመጉ ጥር 14 ቀን 2013 ዓ.ም. አመሻሽ ላይ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ በወቅቱ ተከስቶ በነበረው ችግር ምክንያት ለስድስት ወራት ያህል የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመታወጁ፣ በሰብዓዊ መብቶች ላይ ገደቦች ተጥለዋል፡፡ በዚህ ምክንያትም ‹‹የሰዓት ዕላፊ ገደቦችን ጥሳችኋል›› በሚል፣ በፀጥታ ኃይሎች የኃይል ዕርምጃ የተወሰደባቸው ሰዎች እንዳሉ መረጃዎች እንደደረሱት ገልጿል፡፡
ለአብነት ያህል ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደና በረከት በርሄ የተባሉ ግለሰቦች ጥር 11 ቀን 2013 ዓ.ም. በፀጥታ ኃይሎች ተገድለዋል የሚል መረጃ እንደደረሰውና እያጣራ መሆኑን ተናገሯል፡፡ ኢሰመጉ ሕግ በማስከበሩ ወቅትና ከዚም ወዲህ ባሉት ጊዜያት አስገድዶ መድፈር፣ ከፍርድ ውጪ የሆነ ግድያ፣ ሕገወጥ እስራትንና ዕገታን ጨምሮ ብዙ ሰብዓዊ መብቶች ጥሰት በልዩ ልዩ አካላት እየተፈጸሙ ስለመሆኑ የሚጠቁሙ አቤቱታዎችን መቀበሉንና በርካታ መረጃዎችንም ማሰባሰቡን ተናግሯል፡፡
በእነዚህ የመብት ጥሰቶች ሴቶች፣ ሕፃናት፣ አካል ጉዳተኞችና አረጋውያን ቀዳሚ ሰለባዎች ስለመሆናቸውም ለማወቅ እንደቻለ ጠቁሟል፡፡ በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎችም በልዩ ልዩ ምክንያቶች የሚንቀሳቀሱ የትግራይ ተወላጆች እስር፣ እንግልትና አድልኦ እየደረሰባቸው ስለመሆኑም ኢሰመጉ በርካታ አቤቱታዎች እንደደረሱትም አክሏል፡፡
በሌላ በኩል በክልሉ ላለፉት ሦስት ወራት ገደማ ከጥቂት አካባቢዎች በስተቀር የባንክ አገልግሎት ያልተጀመረ በመሆኑ፣ መብራት፣ ውኃና ስልክ የመሳሰሉ መሠረታዊ አገልግሎቶች የተቋረጡ በመሆናቸው፣ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞች ወርኃዊ ደመወዛቸው ያልተከፈላቸው መሆኑንና የጤና አገልግሎት መስጫ ተቋማት በሚገባ አገልግሎት እየሰጡ ባለመሆናቸው፣ ነዋሪዎች ለብዙ እንግልትና መከራ እየተዳረጉ ስለመሆኑ ለማወቅ መቻሉንም አስታውቋል፡፡
በክልሉ እየተደረጉ ያሉ ሰብዓዊ ድጋፎች በፀጥታ ችግርና እንዲሁም በድጋፍ ሰጪ ድርጅቶችና በመንግሥት ተቋማት ተናቦ ያለመሥራት ችግሮች ምክንያት በበቂ ሁኔታና መጠን በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ተደራሽ ባለመሆናችው ነዋሪዎችን ለከባድ ችግር እያጋለጣቸው መሆኑን በተለያየ መንገድ እየተገለጸ እንደሚገኝ ኢሰመጉ በመግለጫው አስታውቋል፡፡፡፡ ይህም ሁኔታ በተገለጸው መልኩ እየተከሰተ ከሆነና ከፍተኛ የሆነ አስቸኳይ ሰብዓዊ ድጋፍ ሳይደረግ የሚቆይ ከሆነ ከባድ ሰብዓዊ ቀውስ ሊፈጠር እንደሚችል ጠቁሟል፡፡
በመሆኑም፣ የፌዴራል መንግሥም ሆነ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የፀጥታ ሥጋት ባለባቸውና በሌሎቹም አካባቢዎች አስቸኳይ ሰብዓዊ ድጋፍ የሚያስተላለፍባቸውን መተላለፊያ መስመሮችና ልዩ ሥልቶችን እንዲቀይሱ፣ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በሁሉም አካባቢዎች በፍጥነት ተደራጅተው አገልግሎት መስጠት እንዲጀምሩ እንዲያመቻቹ ኢሰመጉ አሳስቧል፡፡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሥር የተቋቋመው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መርማሪ ቦርድ የአዋጁን አፈጻጸም በቅርበት እንዲከታተልና ሕግ በማስከበሩ ወቅትና ከዚም ወዲህ ባሉት ጊዜያት የተፈጸሙትን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች መርምሮ፣ የአጥፊዎቹን ማንነት በግል እንዲለይና ለሕዝብ ይፋ እንዲያደርግ ጠይቋል፡፡፡፡ በተጨማሪም መንግሥት ነፃና ገለልተኛ የሆኑ የሰብዓዊ መበቶች ተቋማትና ብዙኃን መገናኛ በአካባቢዎቹ ተንቀሳቅሰው ጉዳዩን ለማጠራት የሚያስችላቸው ሁኔታ እንዲፈጠር እንዲያደርጉ አሳስቧል፡፡