ከነሐሴ ወር 2012 ዓ.ም. ጀምሮ በተለያዩ ዘርፎች የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በተለያዩ መድረኮች ሲያወያይ የቆየው የሁሉን አቀፍ ብሔራዊ ምክክር ኢኒሼቲቭ ኢትዮጵያ (Multi-stakeholder Initiative for National Dialogue Ethiopia (MIND – Ethiopia))፣ ለምክክሮቹ የሚረዱ አጀንዳዎችን እየሰበሰበ እንደሚገኝ አስታወቀ፡፡

የማይንድ ኢትዮጵያ አባላት የሆኑት አቶ ንጉሡ አክሊሉ ከዴስቲኒ ኢትዮጵያ፣ አቶ ግርማ በቀለ ከፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣ እንዲሁም ልዑል በዕደ ማርያም መኮንን ከዕርቀ ሰላም ኮሚሽን በጋራ በመሆን ጥር 14 ቀን 2013 ዓ.ም. በስካይላይት ሆቴል በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፣ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር በሦስት ጥያቄዎች ዙሪያ ውይይቶች ሲካሄዱ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡

አቶ ንጉሡ እንደገለጹት፣ የመጀመሪያው የብሔራዊ ምክክር አስፈላጊ መሆኑን፣ በዚህ ጥያቄ ላይ ከሁሉም ተሳታፊዎች አዎንታዊ ምላሽ መሰጠቱንና የምክክሩ አስፈላጊነት ላይ ከስምምነት መደረሱን ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በመቀጠል ለተወያዮቹ የቀረበው ጥያቄ ‹‹አጀንዳዎቹ ምን ይሁኑ?›› የሚል ሲሆን፣ ቅደም ተከተላቸውንም የሚመለከት እንደነበረ አስረድተዋል፡፡ በዚህ ረገድ በርካታ የአጀንዳ ጥቆማዎች እየመጡ እንደሚገኙ በመግለጽ፣ እነዚህ አጀንዳዎች እየተሰበሰቡ መሆናቸውንና በአንድ ቋት ገብተው የመምረጡ፣ የማደራጀቱና ቅደም ተከተል የማስያዙ ሥራ ይከናወናል ብለዋል፡፡

በሦስተኛ ደረጃ የቀረበው ጥያቄ ‹‹ማን ያወያይ?›› የሚል ሲሆን፣ በዚህ ላይም መሥፈርቶች እየተዘጋጁ እንዳሉና በጠቅላላው ትምህርትና ልምድ ያላቸው በሥነ ምግባራቸው የተመሰገኑ ገለልተኛ ባለሙያዎች እንዲሆኑ እንደሚፈለግ አስታውቀዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አወያዮቹ ኢትዮጵያውያን እንዲሆኑ የሚል መግባባት መኖሩን ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ከፓርቲዎች ጋር በመሆን ባደረገው ውይይት፣ ከምርጫ 2013 በፊትና በኋላ በቀጣይነት ሊደረጉ የሚገባቸውን የውይይት ነጥቦች መለየታቸውን አቶ ግርማ አስታውቀው፣ ከጥር 2 እስከ 4 ቀን 2013 ዓ.ም. በተደረጉት ውይይቶች፣ የምክር ቤቱ አባላት ከሆኑት 44 ፓርቲዎች መካከል 38 ፓርቲዎች በውይይቶቹ ላይ መገኘታቸውን ገልጸዋል፡፡

ከምርጫ በፊት ሊፈቱ የሚገባቸው ተብለው የተለዩት ለምርጫ አስቻይ ሁኔታዎች መኖር አለመኖራቸው፣ የምርጫ ሒደትን የተመለከቱ የታዛቢና መሰል ጉዳዮች፣ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድና የሌሎች አስፈጻሚ አካላት ገለልተኝነት፣ የሰብዓዊ መብት ጉዳዮችና የመንግሥት ኃላፊነትና ተጠያቂነት፣ የብሔረሰቦች የማንነት ጥያቄዎችና የምርጫ ክልል ተያያዥ ጉዳዮች፣ ሰላምና ፀጥታ፣ ከውጤት በኋላ ሊነሱ የሚችሉ ቀውሶችና ተጠያቂነት፣ የፀጥታ አካላት ተጠያቂነት፣ ሚዲያና ሚዛናዊነት፣ እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎዎችን የተመለከቱ ናቸው፡፡

ከምርጫ በኋላ በረዥም ርቀት እንዲታዩ የተባሉት ሕገ መንግሥት፣ የዴሞክራሲ ተቋማት ገለልተኝነት፣ የአገረ መንግሥት ግንባታ፣ የታሪክና ትርክቶች ንባቦች አረዳዶችና የብሔራዊ ዕርቅ ጉዳይ ናቸው፡፡

ለውይይቶቹ የሚሆኑ ወጪዎች ከተሳታፊ ተቋማቱ በሚገኝ ገንዘብ ሲሆን፣ በአንድ ቋት ከሚቀመጥ ገንዘብ ወጪዎቹ እንደሚሸፈኑ አቶ ንጉሡ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ወደፊት ለሚደረጉ ውይይቶች ድጋፎችን ለማድረግ ፍላጎት ያሳዩ ለጋሾች መኖራቸውን በመግለጽ፣ ገንዘብ የሚሰጡ አካላት ግን በውይይቱም ሆነ በውጤቱ ላይ ምንም ዓይነት ተፅዕኖ እንዳያሳድሩ ጥንቃቄ ይደረጋል ብለዋል፡፡

በዚህም አሁን ለዝግጅት ምዕራፉ በፋይናንስ ሰበብ መጓተቶች እንዳይኖሩ ማይንድ ኢትዮጵያን ያዋቀሩ ድርጅቶች ወጪውን እየሸፈኑ እንደሆነ፣ በውይይትና በትግበራ ወቅት ደግሞ የተለያዩ ድጋፎችን ከለጋሾች ለማግኘት እንደሚቻል አስታውቀዋል፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *