በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በመተከል ለሁለት ዓመታት ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ከቆዩ ተጠርጣሪዎች መካከል 614ቱ ጥር 14 ቀን 2013 ዓ.ም. በዋስ ተለቀቁ።

በአካባቢው አገራዊ ለውጡን መቀበል እንደ ወንጀል ተቆጥሮ፣ የዕለት ተዕለት ሥራቸውን በማከናወን ላይ እያሉ በድንገት ከታሰሩ በኋላ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ወራትንና ዓመታትን ማሳለፍ የተለመደ ክስተት ሆኖ መቀጠሉም ታውቋል፡፡ ድንገት ‹‹ትፈለጋላችሁ›› ተብለው ከተወሰዱ በኋላ ማረሚያ ቤት ተወርውረው ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ የቆዩ ዜጎች ብዙ መሆናቸውም ታውቋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተቋቋመው የመተከል የተቀናጀል ግብረ ኃይል የዞኑን የፀጥታና ሕግ ማስከበር ሥራ ከተረከበ በኋላ፣ በዞኑ ማረሚያ ቤት ያለውን ችግር መመልከቱ ታውቋል፡፡ በዚህም ከሁለት ዓመታት በላይ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ የታሰሩ ተጠርጣሪዎች እንዳሉ በማረጋገጡ፣ ችግሩን ለመፍታት በፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግና ፖሊስ አማካይነት ሒደቱን ሲከታተል ቆይቷል። የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግና ፖሊስ ከግብረ ኃይሉ ጋር በመቀናጀት ተጠርጣሪዎቹን ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ በማድረጋቸው፣ በተደረገው የማጣራት ሒደት 614 ተጠርጣሪዎች በዋስ እንዲለቀቁ ተደርጓል።

የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ጌታሁን አብዲሳ እንደገለጹት፣ ተጠርጣሪዎቹ ከዚህ በኋላ በወንጀል የሚፈለጉ ሳይሆን የልማት አርበኞች ሆነው እንዲገኙ አሳስበዋል። የክልሉ መንግሥት በመተከል ዞን ይፈጸም የነበረውን ኢሰብዓዊ ድርጊትና ሠፍኖ የነበረውን የመልካም አስተዳደር ችግር ለመፍታት መዋቅራዊ ለውጥ እያደረገ መሆኑንም አመልክተዋል።

በመሆኑም ከማረሚያ ቤት የወጡ ዜጎች በተለይ ደግሞ ወጣቶች ከመንግሥት ጎን በመሠለፍ ሰላም ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ ለጋራ ደኅንነታቸው በቅንጅት እንዲሠሩ ጠይቀዋል። የመተከል የተቀናጀ ግብረ ኃይል አባል ብርጋዴር ጄኔራል ዓለማየሁ ወልዴ፣ ‹‹ወጣቶች በተለያዩ ወንጀሎች ተጠርጥረው ማረሚያ ቤት መቆየታቸውን የቂም በቀል መወጣጫ ሳይሆን፣ መማሪያ ሊያደርጉት ይገባል፤›› ብለዋል።

ወጣቶቹ ኢትዮጵያን የማተራመስና የማፈራረስ ተልዕኮ ተሰጥቷቸው ከሚንቀሳቀሱ ድርጅቶችና ቡድኖች ጋር ግንኙነት መፍጠር እንደሌለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡ በተለይም መተከል እንዳትረጋጋና በአገሪቱ ሰላም እንዳይሰፍን የሚያደርጉ ቡድኖች እንዳሉ ያስታወሱት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ወጣቶቹ እነዚያን አገር አፍራሽ ቡድኖች በቃችሁ ብለው መዋጋት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የዋስትና መብታቸው ተከብሮላቸው ከማረሚያ ቤት የወጡ ታራሚዎች በበኩላቸው፣ ‹‹የዛሬውን ቀን ዳግም የተወለዱበት ያህል እንደተሰማቸው፤›› ገልጸዋል። በሐሰት ወንጅለው ወደ ማረሚያ ቤት ያስገቧቸውን ግለሰቦችን ከመበቀል ይልቅ ከስህተታቸው እንዲማሩ አርዓያ እንደሚሆኗቸውም ተናግረዋል።

በመተከል የተከሰተውን ችግር ማረሚያ ቤት ሆነውም ሲከታተሉ እንደነበር ጠቁመው፣ በዞኑ ሰላም ሠፍኖ መተከል ወደምትታወቅበት የአብሮነትና የመቻቻል ባህል እንድትመለስ ከመንግሥት ጎን ሆነው እንደሚሠሩም መናገራቸውን ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *