በውይይት ላይ ባለው ረቂቅ የመገናኛ ብዙኃን አዋጁ ውስጥ መገናኛ ብዙኃን የስም ማጥፋት ድርጊት ፈጽመው ሲገኙ፣ በፍትሐ ብሔር ኃላፊነት እንጂ፣ በወንጀል ሕግ አያስጠይቅም ተብሎ መቀመጡ አግባብ አይደለም ሲሉ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለጹ። የምክር ቤቱ የሕግ ፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ይህንን የተናገሩት በቀረበላቸው ረቂቅ አዋጅ ላይ በተወያዩበት ወቅት ነው ፡፡

 

ረቂቅ አዋጁ አሁን በሥራ ላይ ያለውን የብሮድካስት ባለሥልጣን ራሱን የቻለ የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤት በማድረግ፣ የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን አድርጎ የሚያቋቁም ሲሆን፣ ለኅትመትና ለብሮድካስት መገናኛ ብዙኃን መተዳደሪያና ለበይነ መረብ ሚዲያ የሕግ ማዕቀፍም ሆኖ ለመጀመርያ ጊዜ ተግባራዊ እንዲሆን የተዘጋጀ ነው።

የምክር ቤቱ የሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግና የብሮድካስት ባለሥልጣን ከፍተኛ ኃላፊዎች በተገኙበት፣ በረቂቁ ላይ የአስረጂዎች መድረክ ሰኞ ጥር 3 ቀን 2013 ዓ.ም. በምክር ቤቱ የመሰብሰቢያ አዳራሽ አካሂዷል።

በውይይቱ ወቅት የተገኙት ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) ረቂቅ አዋጁ የፕሬስና የመገናኛ ብዙኃን መብቶችን ጥበቃ በማድረግ ረገድ፣ ‹‹ቁልፍ ፋይዳና ትልቅ ትርጉም ያለው ብዝኃነት የሚስተዋልበት ነው፤›› ብለዋል።

ይሁን እንጂ የቋሚ ኮሚቴው አባላት የሚዲያ አካላት በስም ማጥፋት ተሳትፈው በወንጀል መጠየቅ ሲገባቸው፣ በፍትሐ ብሔር መደረጉ ትክክል አይደለም ብለዋል።

የቋሚ ኮሚቴው አባል አቶ ሁሴን ዳሪ በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 84 ስለተጠቀሰው የሚዲያዎች የስም ማጥፋት ድርጊት አስመልክተው ሲናገሩ፣ ‹‹ስም ማጥፋትና በመሬት ላይ ያለው ሀቅ በጣም ከባድ ነው። ይገባኛል የዴሞክራሲ ምኅዳሩን ለማስፋት የታሰበበትን ሁኔታ እኔም እስማማለሁ፡፡ ነገር ግን በወንጀል እንዳይጠየቁ ተብሎ በፍትሐ ብሔር ሲጠየቁ፣ እስከ 300 ሺሕ ብር የሚል ገደብ ቅጣት መጣሉ በጡንቻና በሀብት የሚተማመን አካል እንዲጠቀምበት ያደርጋል፤›› ብለዋል፡፡

እንዲህ ዓይነቱ አካሄድ የአንድን ማኅበረሰብ ባህላዊ እሴት ሞራል ወይም ሃይማኖት ውስጥ ገብቶ ወይም የአገሪቱን ሉዓላዊነት በመፈታተን ጭምር፣ በግለሰብም ሆኖ በቡድን እየተሠራ እንደሆነ መሬት ላይ ያለ እውነታ ነው ሲሉም አክለዋል፡፡

‹‹በፍትሐ ብሔር ሕግ 300 ሺሕ ብር ተቀጥቶ ነገ ላይደግመው የሚችልበት ምንም ዋስትና የለውም፡፡ ስለዚህ ሊያመጣ ከሚችለው ጉዳትና ጥፋት አንፃር ዳግም መታየት አለበት፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ሁሴን አክለውም፣ ‹‹ለዜጎቻችን እንዲጠቅም የወጣ አዋጅ መሆኑን አውቃለሁ። ነገር ግን አሁን እየተደረገ ያለው የስም ማጥፋት ጉዳይ በወንጀል ተጠያቂ አይሆንም የሚለው ነገር በድጋሚ ቢታሰብበት፤›› ሲሉ ተናግረዋል።

በተመሳሳይ ሐሳባቸውን የሰጡት የምክር ቤት አባል ወ/ሮ ኪሚያ ጁንዲ፣ ስም ማጥፋት በወንጀል ሕጉ እንኳን ተደንግጎ ችግሩን ማረምና ማስቀረት አልተቻለም ብለዋል።

ስም ማጥፋት አንዱ ሌላው ላይ በሰፊው አየተሄደበት ያለ ችግር በመሆኑ፣ በምን አግባብ ወደ ፍትሐ ብሔር እንደገባ በድጋሚ ይታሰብበት በማለት ጠይቀዋል።

ዋና ዓቃቤ ሕጉ ስለተነሳው ጉዳይ ሲመልሱ፣ የመገናኛ ብዙኃን ሙሉ ለሙሉ የሕግ ሰውነት ያላቸው አካላት ናቸው ብለው፣ በወንጀልም ሆነ በፍትሐ ብሔር ሕጉ ቢኬድ ሊሆን የሚችለው የገንዘብ ቅጣት አልፎም ዕገዳና ስረዛ እንጂ እስራት አይኖም ብለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ 300 ሺሕ ብር ሲባል ለህሊና ወይም ለሞራል ካሳ የሚከፈል ቅጣት ይሁን እንጂ፣ ቁሳዊ ጉዳትን አያካትትም ሲሉ አስረድተዋል። በመሆኑም አንድ ሚዲያ በስም ማጥፋት ቢጠየቅ ላደረሰው የሞራልና ቁሳዊ ጉዳት የሚቀጣ ከሆነ የእስር ቅጣቱ አይጠቅምም ብለዋል፡፡

ዓቃቤ ሕጉ አክለውም ከሚዲያ ባለቤቶችና ኃላፊዎች ጋር በነበረው ውይይት 300 ሺሕ ብር እንደበዛባቸው መናገራቸው፣ የአገሪቱ የወንጀል ሕግ ለህሊና ቅጣት 1,000 ብር እንደሚቀጣ፣ ይህን ያህል መደረጉ ሚዲያውን ልታጠፉት ነው የሚል ቅሬታ መቅረቡንም ጠቁመዋል፡፡

በመሆኑም ተጠያቂው አካል ይህን ያህል ቅጣት በገንዘብ ከተቀጣ እስር ቤት መክተቱ አይጠቅምም ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የወንጀል ድንጋጌው መቅረቱ ‹‹እስር ብቻ ነው የሚያስቀረው›› ያሉት ዓቃቤ ሕጉ፣ ስም አጥፍተሃል ብሎ ማረሚያ ቤት ማስገባት ተመጣጣኝ እንደማይሆን፣ በቂና አስተማሪ የሆኑ ሌሎች ቅጣቶችን መቅጣት ይቻላል ከሚል የመጣ ነው ብለዋል።

ስም ማጥፋት ሲባል ከግለሰቦች ማንነት ጋር ሲገናኝ ብቻ እንደሆነና ከሉዓላዊነትና ከማንነት ጋር በተገናኘ የሚደረግ ስም ማጥፋት ማለትም ማጥላላትና አገራዊ ጉዳት የሚያደርስ ከሆነ ግን በወንጀል ሕጉ የሚታይ እንደሆነ ተናግረዋል።

የመገናኛ ብዙኃን በስም ማጥፋት ተግባር ፈጽመው ሲገኙ መልስ ወይም እርማት እንዲሰጡ ሕጉ ያስገድዳቸዋል ያሉት ዓቃቤ ሕጉ፣ አሠራሩ ዓለም አቀፍ ልምዶችንና ተሞክሮዎችን ግምት ውስጥ በማስገባት ለአብነትም የኬንያና የጋናን አሠራር በመጥቀስ ስም ማጥፋትን ሙሉ በሙሉ በፍትሐ ብሔር እንዲታይ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡

 

ስም ማጥፋትን በወንጀል ሕጉ እንዲዳኝ ማድረግ የፕሬስ ነፃነትና ሐሳብን በነፃ የመግለጽ መብት ላይ፣ ከፍተኛ የሆነ ጫና ያስከትላል በሚል የተወሰደ እንደሆነ አስረድተዋል።

የብሮድካስት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው ድንቁ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በስም ማጥፋት ድርጊት የተገኙ አካላት ከዚህ በፊት በነበረው አሠራር በወንጀል ሕጉ ይጠየቁ እንደነበር፣ አሁን እየተሻሻለ ያለው ረቂቅ ሕግ ግን በዘርፉ ትልቅ ለውጥ ያመጣል ተብሎ እንደሚታሰብ ገልጸዋል፡፡

ረቂቅ አዋጁ የዕገዳ ዕርምጃዎችን ስለመውሰድና ዕግድ ስለመጣል በሚለው ድንጋጌው ሥር ‹‹በየጊዜው በሚወጣ ኅትመት ወይም የብሮድካስት አገልግሎት በብሔራዊ ደኅንነት ላይ ሊቀለበስ የማይችል ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስ ይዘት ሊያሠራጩ ስለመሆኑ ዓቃቤ ሕግ በቂ ምክንያት የኖረው እንደሆነ፣ ኅትመቱ ወይም የብሮድካስት አገልግሎቱ እንዳይሠራጭ የማድረግ ኃላፊነትን ይሰጣል››፡፡

ዓቃቤ ሕግ ይህን መሰሉ ሁኔታ ሊከሰት እንደሚችል ለማመን በቂ ምክንያት ሲኖረው ኅትመቱ ወይም የብሮድካስት አገልግሎቱ እንዳይሠራጭ ለፍርድ ቤት አመልክቶ ማስከወን እንደሚችል፣ ከነገሩ አጣዳፊነት የተነሳ ጉዳቱን ለመከላከል የፍርድ ቤት ማገጃ ትዕዛዝ በፍጥነት ማግኘት ባልቻለ ጊዜ በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ውሳኔ ማገድ እንዲቻል ሥልጣን ይሰጠዋል፡፡

ይህ ድንጋጌ ለጋዜጠኝነት ሙያ የተሰጠ ነፃነትና የሚደረግ ሕገ መንግሥታዊ ጥበቃን እንደሚጣረስና ጋዜጠኞችም ራሳቸውን ሳንሱር እንዲያደርጉ የሚያስገድድ በመሆኑ፣ ከረቂቅ ሕጉ እንዲወጣ ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርቡበትም በረቂቁ ተካቶ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡ የምክር ቤቱ የሕግ ፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ረቂቁን በተመለከቱበት ወቅት በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም ያሉት ነገር አልነበረም፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *