የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሸን (ኢሰመኮ) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የወንጀል ሥነ ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ (Criminal Procedure Code and Evidence Law) በርካታ ድንጋጌዎች ከሰብዓዊ መብቶች ሕግና መርሆች አንፃር ሊሻሻሉ እንደሚገባ፣ ማክሰኞ ጥር 4 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ጥሪ አቀረበ፡፡
ኮሚሽኑ ይፋ ባደረገው ባለ 33 ገጽ ሪፖርት ማሻሻያ እንዲደረግባቸው ካሳሰበው ዋና ዋና ነጥቦች መካከል መርማሪ ፖሊስ ተጠርጣሪን ለመያዝ፣ ለብርበራና በልዩ የወንጀል ምርመራ ዘዴ ኃይል ሊጠቀም የሚችለው ጥንቃቄ የማድረግን፣ የሕጋዊነትን፣ የጥብቅ አስፈላጊነትን፣ የተመጣጣኝነትንና አድልዎ ያለ ማድረግን መርሆችን ባከበረ መንገድና ሌላ አማራጭ መንገድ የሌለ መሆኑ ሲረጋገጥ ብቻ እንደሆነና በዚህ ረገድ ተጠያቂነትን የሚያሰፍን ሥነ ሥርዓትም በግልጽ ሊደነገግ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡
በወንጀል የተጠረጠረ ወይም የተያዘ ሰው የቃል አቀባበል ሒደትን ጨምሮ በማቆያ ቤት ወይም በእስር ወቅት ኢሰብዓዊ አያያዝ እንዳይፈጸምበትና ተፈጽሞም ሲገኝ ተጠያቂነት እንዲኖር የሚያስችሉ ማሻሻያዎች ሊካተቱ የሚገባ መሆኑን አሳስቧል፡፡
ለጥቃት ተጋላጭ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች በእስር በመያዝ፣ በምርመራ፣ በክስ፣ እንዲሁም ምስክርነት በመስጠት ሒደት ሰብዓዊ መብቶቻቸውን፣ ክብራቸውንና ልዩ ፍላጎቶቻቸውን የበለጠ ሊያስከበሩ የሚያስችሉ ማሻሻያዎች ሊካተቱ እንደሚገባ አስገንዝቧል፡፡
ሕፃናት ከእናታቸው ጋር የሚታሰሩበትን ሁኔታ ለማስቀረት ነፍሰ ጡር ለሆነች ሴት ወይም ከዘጠኝ ዓመት በታች የሆነ ሕፃን፣ ወይም የምንትንከባከበው የአካል ጉዳተኛ ልጅ ላላት እናት የዋስትና መብት ወዲያውኑ እንዲፈቀድና በጥፋተኝነት ፍርድ ጊዜም ከእስር ውጪ ያለ ቅጣት (Non-Custodial Measures) በአማራጭነት እንዲወሰድ ጥያቄ አቅርቧል፡፡
ማንኛውም የታሰረ ሰው በተጠረጠረበት ወይም በተከሰሰበት ወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ ቢገኝ ሊጣልበት የሚችለውን የመጨረሻውን የእስር ቅጣት እርከን ያህል በእስር የቆየ እንደሆነ ወዲያውኑ ሊለቀቅ የሚገባ መሆኑን፣ እንዲሁም ለሕገ ወጥ መያዝ ወይም ለእስር የተዳረገ ሰው ካሳ የሚያገኝበት ሥነ ሥርዓት ሊደነገግ የሚገባ መሆኑን ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ካቀረባቸው ነጥቦች መካከል ናቸው፡፡
ኮሚሽኑ በሪፖርቱ በአጠቃላይ ከ30 በላይ በሆኑ ድንጋጌዎች ላይ የማሻሻያ ምክረ ሐሳብ ከእነ ማብራሪያዎቹ ያቀረበ መሆኑን፣ ለምክር ቤቱ ሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴና ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጽ/ቤት ቀርቧል።
በሌላ በኩል ረቂቅ ሕጉ ከሰብዓዊ መብቶች አንፃር በርካታ ጠንካራ ጎኖች እንዳሉትና እነዚህም የወንጀል ምርመራ ዓላማ እውነትን ማውጣት መሆኑን፣ መካሄድና መጠናቀቅ ያለበትም አስፈላጊ ካልሆነ በስተቀር ተጠርጣሪው ሳይያዝ መሆኑን በግልጽ መደንገጉን፣ በስህተት የተሰጠ ፍርድ እንደገና የሚመረመርበት ሥነ ሥርዓት መደንገግ የሚሉትን ይጨምራሉ።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሸነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር)፣ ‹‹ረቂቅ ሕጉ በርካታ ጠንካራ ጎኖች ቢኖሩትም፣ በኮሚሽኑ ሪፖርት የተመለከቱትን የማሻሻያ ምክረ ሐሳቦች በማካተት ከዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ግዴታዎች ጋር የተጣጣመ ሕግ ማውጣት የግድ አስፈላጊ ነው፤›› ማለታቸው በመግለጫው ተካቷል፡፡