የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ – ኢሰመጉ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት፣ መተከል ዞን፣ በቡለን፣ ድባጤ፣ እና ዳንጉር ወረዳዎች ላይ በንጹኃን ሰዎች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት አሁንም ተባብሶ መቀጠሉ እጅግ አሳስቦታል፡፡
ኢሰመጉ ታህሳስ 15 ቀን 2013 ዓ.ም ባወጣው አስቸኳይ ጋዜጣዊ መግለጫ በመተከል ዞን፣ ቡለን ወረዳ፣ በኩጂ ቀበሌ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት ከ100 በላይ ንጹኃን ሰዎች መገደላቸውን፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መፈናቀላቸውን እና ለከፍተኛ ችግር የተጋለጡ መሆናቸውን አውግዞ፤ መንግሥት በአካባቢው በተደጋጋሚ ጊዜ የሚከሰተውን የንጹኃን ሰዎች ሰቆቃ ለማስቆም የሚያስችል ፈጣን፣ ተጨባጭ እና ዘላቂ መፍትሔ እንዲያበጅ ማሳሰቡ አይዘነጋም፡፡
ሆኖም፤ ከሰሞኑ ይኸው ችግር ዳግም ተከስቶ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን ተጎጂዎች እና የተጎጂ ቤተሰቦች ለኢሰመጉ ተናግራዋል፡፡ ታህሳስ 25 ቀን 2013 ዓ.ም ከቻግኒ ወደ ግልገል በለስ የሚሄድ መኪና ውስጥ የነበሩ ተጓዦች ማንዱራ ከተማ ላይ በታጣቂዎች እንዲወርዱ ተደርጎ አንድ ሰው መገደሉን እና ሁለት ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ከጥር 2 – 3 ቀን 2013 ዓ.ም በቡለን እና ጉባ ወረዳዎች፣ ኦሜድላ እና አይነሸምስ በተባሉ ቀበሌዎች ላይ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ከ50 በላይ ሰዎች መገደላቸውን እና መኖሪያ ቤቶችም መቃጠላቸውን ኢሰመጉ መረጃዎች ደርሰውታል፡፡
በሌላ በኩል፤ ‹‹በድባጤ ወረዳ፣ ቆርቃ ቀበሌ፣ ዳሌቲ በተባለች መንደር ትላንት ጥር 4 ቀን 2013 ዓ.ም ከሌሊቱ 11፡30 ጀምሮ የኦነግ ሸኔ እና የቤኒን ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ሰዎች መገደላቸውን፣ እስከአሁን ድረስ እኔ ራሴ ባለሁበት የ82 ሰዎች አስከሬን በፍለጋ መገኘቱን እና የቀብር ቦታዎች እየተዘጋጁ መሆኑን አይቻለሁ›› ሲሉ አንድ የዓይን እማኝ ለኢሰመጉ ተናግረዋል፡፡
ኢሰመጉ፤ በትላንትናው ጥቃት ሰለባ የሆኑ ሰዎች ቁጥር ከ100 ሊበለጥ እንደሚችል፣ በአብዛኛው ሴቶችና ህጻናት መሆናቸውን እና ከ24 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ቆስለው በጋሊሳ ጤና ጣቢያ እና ቡለን ሆስፒታል ውስጥ ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑን ከአካባቢው ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለማወቅ ችሏል፡፡
1ኛ. ኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን መተከል ዞን ድባጤ ወረዳ “ዳለቺ” ጥር 4/ 2013 ዓ/ም ከ80 ሰዎች በላይ መገደላቸውን አረጋግጧል።
ኮሚሽኑ ለቢቢሲ በሰጠው መረጃ ህይወታቸው የተቀጠፈው እድሜያቸው ከ2-45 ነው ብልሏል።
2ኛ. የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ በቡለን፣ ድባጤ፣ እና ዳንጉር ወረዳዎች ላይ በንጹኃን ሰዎች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት አሁንም ተባብሶ ቀጥሏል ብሏል።
በድባጤ ወረዳ፣ ቆርቃ ቀበሌ፣ ዳሌቲ በተባለች መንደር ጥር 4 ቀን ከሌሊቱ 11፡30 ጀምሮ በተፈፀመው ጥቃት 82 ሰዎች መገደላቸውን አንድ አይን እማኝ አሳውቋል።
እንደ ኢሰመጉ በጥቃቱ ህይወታቸው ያለፈው ከ100 ሊበልጥ እንደሚችልና በአብዛኞቹ ሴቶችና ህጻናት ናቸው ብሏል።
ከ24 ሰዎች በላይ ቆስለው ጋሊሳ ጤና ጣቢያ ቡለን ሆስፒታል ህክምና ላይ ናቸው።
በተጨማሪ ፦ ከጥር 2-3 በቡለን ጉባ ወረዳዎች፣ ኦሜላ እና አይነሽመስ በተባሉ ቦታዎች በታጣቂ ኃይሎች በተፈፀመ ጥቃት ከ50 ሰዎች ተገድለዋል፤ መኖሪያ ቤቶች ተቃጥለዋል። (ሙሉ መግለጫቅ ከላይ ተያይዟል)
3ኛ. የቲክቫህ መተከል ዞን አባላት ከትላንት በስቲያ በድባጤ ወረዳው ጥቃት የተገደሉ ሰዎች ከ100 እንደሚበልጡ ጥቃቱ በተፈፀመበት ዕለት ተናገረዋል
ምንም የማያውቁ ንፁሃን ህፃናት እና እናቶች በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል። ከጥቃቱ በኃላ የነበረውን ሁኔታ በፎቶ እንዲሁም በቪድዮ ቀርፀው ለማስረጃነትም አቅርበዋል።
⚠️ ይህ የመተከል ዞን አሁንም ከስጋት ቀጠናነት ያልተላቀቀ መሆኑን ነዋሪዎች እያሳወቁ ይገኛል ፤ የሚጨመር ኃይል ተጨምሮ አካባቢው ከስጋት እናቶች እና ህፃናትን ከሞት መታደግ እንደሚገባ እያስገነዘቡ ነው።
በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን በትናንትናው ዕለት፣ ጥር 4/ 2013 ዓ.ም ከ80 ሰዎች በላይ መገደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ለቢቢሲ አስታወቀ።
የኮሚሽኑ ከፍተኛ አማካሪ እና ቃል አቀባይ አቶ አሮን ማሾ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ጥቃቱ የደረሰው በመተከል ዞን፣ በደባጤ ወረዳ፣ ዳለቲ በምትባል ከተማ ነው።
ኮሚሽኑ በደረሰው መረጃ መሰረት ህይወታቸው የተቀጠፈው ከ80 በላይ የሚሆኑት እድሜያቸው ከ2 እስከ 45 ነው።
በአካባቢው ተደጋጋሚ ጥቃቶችና ግድያዎች መድረሱን ያስታወሱት አቶ አሮን በፌደራልና በክልሉ መንግሥት የተቀናጀ እርምጃ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ተናግረዋል።
ከዚህም ጋር ተያይዞ በንፁሃን ዜጎች ላይ ጥቃት እየፈፀመ ባለው ቡድን ላይ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን በዞኑ የተቋቋመው ግብረ ኃይል አስታውቋል።
ግብረ ኃይሉ እየወሰድኩት ነው ባለው እርምጃ ባለፉት ሁለት ሳምንታት የመንግሥት አመራሮችን ጨምሮ በርካታ የቡድኑ አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ኢዜአ በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ በልጅጌን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን በሚደርሱ ተደጋጋሚ ጥቃቶች አሁንም የሰዎች ህይወት እየጠፋ መሆኑን ነዋሪዎች ገልፀዋል።
በጉዳዩ ላይ ቢቢሲ ምላሻቸውን የጠየቃቸው የክልሉ የኮምዩኒኬኬሽን ኃላፊ አቶ መለሰ በየነ በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት መስጠት የሚችለው የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት ነው በሚል ከመናገር ተቆጥበዋል።
አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የማንዱራ ነዋሪ ለቢቢሲ እንደገለጹት “አካባቢው ተረጋግቷል መባሉ እውነት አይደለም” ሲሉ ገልጸዋል።
“የፖለቲካ ጨዋታ አይደለም መሆን ያለበት እውነቱ መነገር አለበት” የሚሉት ነዋሪው በተለያዩ አካባቢዎች በሚደርስ ጥቃት የሰዎች ህይወት አሁንም እያለፈ መሆኑን ጠቁመዋል።
“ትላናንት በስተያ [ሰኞ] እንኳን የመተከል ዞን አንድ ወረዳ በሆነችው ዳንጉር [ቀደም ሲል የጤና ባለሙያዎች የታፈኑበት አካባቢ] ማታ ላይ ሰው ተገድሏል። ከቻግኒ ወደ ከግልገል በለስ በሚሄድ ሕዝብ ማመላለሻ ላይ ጥቃት ተፈጽሞ አንድ ሰው ሞቶ ሦስት ቆስለዋል።
“ማከስኞ ጠዋትም ወደ ግለግል በለስ በሚሄድ መኪና ኤዲዳ ወይንም ቁጥር 2 በምትባል ቦታ ላይ አንድ ሰው ተገድሏል፤ ሁለት ቆስለው አሁን ህክምና ላይ ነው ያሉት። በድባጤ ወረዳ ዳለቲ ቀበሌ ላይ አንድ ሰው ተገድሏል። ቤቶች እየተቃጠሉ ነው። የደረሰ አካልም የለም። የጸጥታ ችግር አለ ለማለት በአንድ ቀን 200 ወይም 300 ሰው መጨፍጨፍ አለበት?” ሲሉ ተናግረዋል።
ሰኞ ዕለት በጉባ ወረዳ በተፈጸመ ጥቃት ህይወታቸው ያለፉ ሰዎች ቁጥር 15 መድረሱን ቢቢሲ ከነዋሪዎች የሰማ ሲሆን የአካባቢው ኃላፊዎች ለማረጋገጥም ሆነ ለማስተባበል ፈቃደኛ አልሆኑንመ።
ጥቃት የሚፈጸመው በተለዩ ነዋሪዎች ላይ መሆኑን ነዋሪዎች ገልጸው “ቀደም ሲል ማንነትን መሠረት አድርጎ የነበረ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ቀይ የሚባል ሺናሻ ይሁን ኦሮሞ፣ አገው ይሁን አማራ ይሁን ትግሬ እየተለየ የጥቃት ኢላማ ይሆናል” ሲል ገልጸዋል።
በተለያዩ አካባቢዎች ያለውን ግድያ እና ንብረት ውድመት ሲመለከቱም አካባቢው ተረጋግቷል የሚባለውን ትክክል እንዳልሆነ ሌላ በአካባቢው በስጋት ውስጥ ያሉ ነዋሪ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
አሁን በአካባቢው ኅብረተሰብ ተመርጠው በኃላፊነት ላይ ያሉ አመራሮች ከችግሩ ጀርባ ያሉ ናቸው ብለው የሚያምኑት ነዋሪ “በድጋሚ ተጎጂዎችንም አካቶ ከአካባቢው ኅብረተሰብ ጋር በመሆን ጊዜያዊ አስተዳደር እየተመሰረተ ካልሄደና ጥቃት አድራሾችን ላይ ተገቢ እርምጃ ካልተወሰደ ጥቃቱ እየቀጠለ ሊሄድ ይችላል” ሚል ስጋታቸውን አስቀምጠዋል።
ሌላ የአካባቢው ነዋሪም ትላንት መተከል ዞን ጉባ ወረዳ አይሚሽሚሽ ቀበሌ ጥቃት መፈጸሙን ገልጸው፤ በጥቃቱ እናቱ ያዘለችውን ህጻን ጨምሮ 11 ሰዎች ህይወታቸው ማለፉን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“ትላንት ሰኞ ጠዋት በግምት 12፡30 አካባቢ ነው ጥቃቱ ተፈጸመው። እኔ አልመሃል ነው ያለሁትና ወዲያው ወደ እኛ ተደወለ። ለመከላከያ ተናግረን በማስተባበር አስከሬናቸው ተነስቷል። ማታ ላይ አልመሃል ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ነው የተቀበሩት” ሲሉ አስረድተዋል።
ቤቶች እና የተለያዩ ንብረቶች መቃጠላቸውንም አስታውቀው ጥቃት አድራሾቹ “የሚያስፈልጋቸውን ንብረት በአህያ ጭነው ሄደዋል” ሲሉ ነዋሪዎች ገልጸዋል።
ከጥቃቱ ጀርባ አሉ ያሏቸውን ሰዎች ለሕግ አካላት ቢያሳውቁም ከእስር እየተፈቱ መሆኑንና ጥቃቱን በመምራት ላይ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
አካባቢው ስላለበት ሁኔታ ተጠይቀውም “አልመሃል ላይ መከላከያም ፌደራልም አለ። በፊትም ደህና ነበር። አልመሃል ሠላም ነው ባይባልም ድባቡ ጥሩ አይደለም። . . . በእርሻ ኢንቨስትመንት ጥጥ ለቀማ ላይ የነበሩ ሠራተኞች እንዳሉ እየወጡ ነው። ይቅርብን አንሠራም አውጡን እያሉ ከባለሃብቶች ጋር ግብ ግብ እየፈጠሩ ወደ አልመሃል እየገቡ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
ቢቢሲ ሰሞኑን ስለተፈጸሙት ጥቃቶች ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የክልሉን የኮምዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ መለሰ በየነን ለማናገር ቢሞክርም እሳቸው በአሁኑ ጊዜ መግለጫ እንደማይሰጡና ጉዳዩን ከሚከታተለው ኮምንድ ፖስት እንድንጠይቅ በሰጡን ምላሽ፤ የኮምንድ ፖስቱ አባል የሆኑት አቶ ተስፋዬ በልጅጌ ጋር በተደጋጋሚ ስልክ ብንደውልም ጥሪያችን ስለማይነሳ ሐሳባቸውን ለጊዜው ማካተት አልቻልንም።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለወራት የዘለቀ ተከታታይ ጥቃት በነዋሪዎች ላይ ሲፈጸምበት በቆየበት የመተከል ዞን ውስጥ በሚገኘው ቡለን ወረዳ በኩጂ ቀበሌ ታኅሣስ 13/2013 ዓ.ም በታጣቂዎች በተጸፈመ ጥቃት ከ200 በላይ ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል።
በመተከል ዞን በተለያዩ ወረዳዎች በታጣቂዎች የሚፈፀመውን ግድያ ለማስቀረት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የተቋቋመው ግብረ ኃይል የዞኑን የፀጥታና የሕግ ማስከበር ሥራ ተረክቦ እየሰራ መሀኑ ይታወቃል።
ይህ ግብረ ኃይል ከፍተኛ የመንግሥት ባለሰልጣናትን፣ የመከላከያ ሠራዊት አመራሮችን ያቀፈ ሲሆን በመተከል ዞን የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ኃላፊነት እንደተሰጠው ተነግሯል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ታኅሣስ 13/2013 ዓ.ም በመተከል ዞን ከተፈጸመው የበርካታ ሰዎች ግድያ ጋር በተያያዘ እጃቸው አለበት የተባሉ አራት የምክር ቤቱ አባላትን ያለመከሰስ መብት ማንሳቱ ይታወሳል።
የቤንሻንጉል ክልል ምክር ቤት በተለያዩ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊነት ላይ የነበሩትንና የምክር ቤት አባል ከነበሩት መካከል የአቶ አድጎ አምሳያ፣ አቶ ሽፈራው ጨሊቦ፣ አቶ ግርማ መኒ እና አቶ አረጋ ባልቢድ ያለመከሰስ መብትን ነው ያነሳው።
የአራቱ የምክር ቤት አባላት ያለመከሰስ መብት በተነሳበት አስቸኳይ ስብሰባ ላይ የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ታደለ ተረፈ በመተከል ዞን የተፈጸመው ጥቃት አሳዛኝና ሊደገም የማይገባው መሆኑን መናገራቸውን የክልሉ ኮምዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ገልጾ ነበር።
በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ካለፈው ዓመት ጳጉሜ ወር አንስቶ በንፁሃን ዜጎች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት ሲፈፀም የቆ ሲሆን በዚህም የተነሳ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቀያቸውን ጥለው ሲሰደዱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ሕይወታቸውን አጥተዋል።
በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን ባለፈው ሳምንት በተፈፀመው ግድያ ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የዋሉ የክልልና የዞን አመራሮች ቁጥር ዘጠኝ ደረሰ።
እነዚህ የመንግሥት ባለሥልጣናት ታኅሣስ 13/2013 ዓ.ም በኩጂ ቀበሌ በደረሰው ጥቃት ወቅት የተሰጣቸውን የመንግሥት ኃላፊነት በአግባቡ ባለመወጣት እንዲሁም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተሳታፊ ናቸው በሚል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የክልሉ ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ መለሰ በየነ ለቢቢሲ ገልፀዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት በመተከል ዞን ከተፈጸመው የበርካታ ሰዎች ግድያ ጋር በተያያዘ እጃቸው አለበት የተባሉ አራት የምክር ቤቱ አባላትን ያለመከሰስ መብት ማንሳቱ ይታወቃል።
የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ መለሰ በየነ ለቢቢሲ በተጨማሪም አንድ የፀረ ሽምቅ አባል በኩጂ ቀበሌ በተፈፀመው ግድያ ላይ እጁ አለበት በሚል ተጠርጥሮ በቁጥጥር ሥር መዋሉን ተናግረዋል።
አክለውም የመተከል ዞን አስተዳዳሪ የነበሩት አቶ አትንኩት ዛሬ ረፋድ 3፡00 ላይ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ገልፀዋል። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለወራት የዘለቀ ተከታታይ ጥቃት በነዋሪዎች ላይ ሲፈጸምበት በቆየው የመተከል ዞን ውስጥ በሚገኘው ቡለን ወረዳ በኩጂ ቀበሌ ታኅሣስ 13/2013 ዓ. ም ንጋት ላይ በታጣቂዎች በተጸፈመ ጥቃት ከ200 በላይ ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል።
አቶ መለስ አክለውም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የተቋቋመው ግብረ ኃይል የመተከል ዞንን የፀጥታ ማስከበር ሥራን መረከቡን ተናግረዋል። ይህ ግብረ ኃይል ከፍተኛ የመንግሥት ባለሰልጣናትን፣ የመከላከያ ሠራዊት አመራሮችን ያቀፈ ሲሆን በመተከል ዞን የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ኃላፊነት እንደተሰጠው ተነግሯል።
አቶ መለስ፣ በአሁኑ ሰዓት ችግሩን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመፍታት ግብረ ኃይሉ በዞኑ በንፁሃን ላይ ጥቃት በመፈጸም፣ ህይወት በማጥፋት ወንጀል የተሳተፉ ተጠርጣሪዎችን በማደን ላይ መሆኑ በመግለጽ፣ በወንጀሉ የተሳተፉ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር አውሎ በሕግ ተጠያቂ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
በዞኑ በተደጋጋሚ የሚከሰቱ ጥቃቶችን ለመከላከል በተወሰደ እርምጃም ከ300 በላይ ታጣቂዎች መገደላቸውን፣ በውጊያውም ሂደት ከ200 በላይ የጦር መሳሪያዎች መማረካቸውን ኃላፊው ጨምረው ገልፀዋል።
በተጨማሪም በተፈጸመው ጥቃት ውስጥ ተሳታፊ ናቸው ተብለው የተጠረጠሩ ከ60 በላይ የሚሆኑ ነዋሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አብራርተዋል።
በመተከል ዞን ቡለን ወረዳ በኩጂ ቀበሌ ታኅሣስ 13/2013 ዓ.ም ንጋት ላይ በታጣቂዎች በተጸፈመ ጥቃት የተገደሉ ሰዎች ቁጥር 207 መድረሱን የአካባቢው ባለስልጣናትና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አስታውቀው ነበር።
በጥቃቱ ከተገደሉት 207 ሰዎች መካከል የ171ዱ ሥርዓተ ቀብር በጅምላ ታኅሣስ 15/2013 ዓ.ም ተፈጽሟል።
ኮሚሽኑ የተፈፀመውን የጅምላ ግድያ ተከትሎ ባወጣው መግለጫ ላይ ከሟቾቹ መካከል አዋቂዎቹ 133 ወንዶችና 35 ሴቶች ሲሆኑ፤ አንድ የስድስት ወር ሕጻንን ጨምሮ 17 ሕጻናት፣ የቀሩት 20 ሰዎች ደግሞ አዛውንቶች ናቸው ብሎ ነበር።
በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ካለፈው ዓመት ጳጉሜ ወር አንስቶ በንፁሃን ዜጎች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት ሲፈፀም ነበር።
በዚህም የተነሳ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቀያቸውን ጥለው ሲሰደዱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ሕይወታቸውን አጥተዋል።