በኢትዮጵያ የሚፈጠሩ ተደጋጋሚ ግጭቶችን ተከትሎ በንፁኃን ላይ የሚፈጸሙ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዲቆሙና ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጥሪ አቀረቡ፡፡

ቁጥሩ እየጨመረ የመጣውን ከመኖሪያው የተፈናቀለ ሕዝብ ከግምት በማስገባት በሥርዓተ ጾታ እኩልነት፣ ሴቶችን በማብቃትና በሌሎች ዘርፎች የተሰማሩ 18 የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ለመንግሥት፣ ለዓለም አቀፍና አገር በቀል ድጋፍ ሰጪዎች፣ ለሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ለግሉ ዘርፍና ለመገናኛ ብዙኃን ነው ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አስቸኳይ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በኢትዮጵያ ግጭቶችን መሠረት አድርጎ የሚፈጸም የሰብዓዊ መብት ጥሰት የተለመደ ጉዳይ መሆኑን ያወሱት ድርጀቶቹ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ለተፈጠረው ሰው ሠራሽ ችግር ተገቢ የሰብዓዊነት ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ሀብት በአፋጣኝ እንዲያሰባስብና እንዲያቀርብ እንዲሁም ከሌሎች የዘርፉ ተዋናዮች ጋር በትብብር እንዲሠራ፣ ደረጃቸውን የጠበቁ ተጨማሪ መጠለያዎች ለማቋቋም ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጀቶችና ከበጎ አድራጎት ተቋማት ጋር በመተባበር እንቅስቃሴ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡

ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ተጎጂዎችንና ቤተሰቦቻቸውን ወደ መኖሪያቸው ለመመለስ፣ ለማቋቋም፣ ለመከላከል፣ ለመጠበቅና እንዲያገግሙ ለማገዝ የሚያስችል የተቀላጠፈ ዕርምጃ እንዲወሰድ፣ የግድያ ወንጀሎችና ጥቃቶች በተካሄዱባቸው አካባቢዎች ላይ ተገቢ ምርመራ እንዲያካሂድና ተጠያቂነትን እንዲያረጋግጥ ብሎም ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች ፍትሕ የሚያገኙበትንና የሚካሱበትን ሁኔታ እንዲያመቻችም ብለዋል፡፡

በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን ታሳቢ ያደረጉ ጥበቃዎች መደረጋቸውን እንዲከታተልና ተጋላጭ ለሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች በተለይ የሴቶችና ሕፃናት ደኅንነት እንዲረጋገጥ ተገቢውን ኃላፊነት የመወጣት ጥረቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል፡፡ ድርጅቶቹ አክለውም ለዕርዳታ ሥራና ለክትትል ሥራዎች እንዲረዳ በግጭቶች ምክንያት ሕይወታቸውን ያጡና ቀዬአቸውን ጥለው ስለተፈናቀሉ ጥቃት የደረሰባቸው ዜጎች ወቅታዊና ትክክልኛ መረጃ እንዲያቀርብ ጠይቀዋል፡፡ ሕይወታቸውን ያጡ፣ አካላቸው ለጎደለና ንብረታቸውን የወደመ ተጎጂዎችና ቤተሰቦቻቸው ፍትሕ እንዲያገኙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዓለም አቀፍና አገር በቀል ድጋፍ ሰጪዎች ሀብት በማሰባሰብ አስቸኳይ የምግብ፣ ውኃና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች የሕክምና፣ የማማከርና ሌሎች መሠረታዊ አገልግሎቶችን የማቅረብ ሥራዎችን እንዲያስተባብሩም ጠይቀዋል፡፡ በተጨማሪም በመጠለያ ጣቢያዎች ለሚገኙ ተፈናቃዮች ድጋፍ በማድረግና መልሶ በማቋቋም በኩል የኢትዮጵያን መንግሥት እንዲያግዙ ጥሪ ያቀረቡት ድርጅቶቹ፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በተሰማሩበት ዘርፍ ሌሎች የዘርፉ ተዋናዮችን በመጠቀም ሀብት እንዲያሰባስቡና በገንዘብና በዓይነት ሊቀርቡ የሚችሉ ድጋፎችን እንዲያስተባብሩ ጠይቀዋል፡፡ ከመኖሪያቸው ለተፈናቀሉ ሰዎች የማገገሚያና መልሶ ማቋቋሚያ ድጋፍ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ ተገቢውን ክትትል እንዲያደርጉ፣ መረጃዎችንም እንዲያጠናክሩና አስፈላጊ የግፊትና የጉትጎታ ሥራዎች ላይ እንዲታትሩ መክረዋል፡፡

ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች የደረሰባቸው ሴቶችና ሕፃናት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያገኙና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሠራተኞች ጉዳት ለደረሰባቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ድጋፍ ለመስጠት በሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች ጥቃት እንዳይደርስባቸው እንዲጠበቁም አሳስበዋል፡፡

የግሉ ዘርፍ ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ወገኖቻችን ለማገዝ በዘርፉ ካሉት አካላት ጋር በመቀናጀት ርብርብ እንዲያደርግና ለአስቸኳይ ድጋፍ በገንዘብ እንዲሁም በዓይነት እንዲደግፍ፣ ከጥቅም ውጪ የሆኑ መሠረተ ልማቶችን፣ መኖሪያ ቦታዎችን፣ የትምህርትና የጤና ማዕከላትን መልሶ ለመገንባትና ተፈናቃዮችን ወደ ተለመደው ኑሯቸው ለመመለስ የሚደረገውን ጥረት በማገዝ በሙያ፣ በሀብትና በሌሎች ድጋፎች ላይ እንዲሳተፍ አሳስበዋል፡፡

የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ስለግጭቶች ብሎም ግጭቶችን ሸሽተው ስለተፈናቀሉ ዜጎች መረጃ አዘል የሆኑና የጋዜጠኝነት ሥነ ምግባርን በጠበቀ መልኩ የተዘጋጁ ዘገባዎችን በየወቅቱ እንዲያቀርቡ፣ በተለያዩ ምክንያቶች የተፈናቀሉ ዜጎችን ለዘገባ ቃለ መጠይቆች በሚያደርጉበት ጊዜ ክብራቸውን ለመጠበቅና ለበለጠ ጥቃት ተጋላጭ እንዳይሆኑ ለመከላከል የሚያስችሉ ሙያዊ ጥበቃዎችን የማድረግ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡

በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚቀሰቀሱ ግጭቶች፣ አለመረጋጋቶችና የሰላም መደፍረስ ሴቶች ሕፃናት፣ አረጋውያንና አካል ጉዳዮችን ጨምሮ በርካቶች ሰላምንና ደኅንነትን በመሻት ከመኖሪያቸው እንዲፈናቀሉ ምክንያትና ግጭቶቹ የወለዷቸው መጠነ ሰፊ ችግሮች በኢትዮጵያ ዜጎች፣ ንፁኃን ነዋሪዎችና ከሌሎች አገሮች በስደት መጥተው በተለጠጡ በርካታ ሴቶችና ሕፃናትን ለማያበራ ስቃይ መነሾ መሆናቸውን የጠቆሙት ድርጅቶቹ፣ ይህም በርካታ ሕዝብ በሚኖርባቸው አካባቢዎችም ሳይቀር የምግብ፣ የውኃ፣ የባንክ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ መሠረተ ልማት፣ የትምህርትና የጤና አቅርቦትና አገልግሎቶች መጓደል ብሎም መቋረጥ የራሱን አሉታዊ ጫና ፈጥሯል ብለዋል፡፡

ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎችና የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ በሚሹ ቦታዎች ዓለም አቀፋዊ መርሆች ሳይሸራረፉ መተግበርና ተፈጻሚነታቸውን መከታተል ፈታኝ በመሆኑ፣ ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ሰዎች በተለይም ሴቶችና ሕፃናት ለተለያዩ ጉዳቶች ተጋላጭ የመሆናቸው መጠን ከፍ ስለሚል ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች፣ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ብሎም በቀጣይም የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛና የሴቶች ወሲባዊ ጥቃት የመጋለጥ አጋጣሚዎችን ይጨምራል ብለዋል፡፡

በኮንሶ ዞንና አካባቢው በሚገኙት አሌ ወረዳ፣ ሰገን አካባቢ ቀበሌዎች፣ በአማሮ ወረዳ ቡኒቲ ቀበሌ እንዲሁም በደራሼ ወረዳ ጋቶ ቀበሌ በኅዳር ወር ተደጋጋሚ ግጭቶች መከሰታቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ሰላምና ደኅንነት ቢሮም በእነዚህ ግጭቶች ምክንያት 66 ሰዎች መሞታቸውን፣ 39 መቁሰላቸውን እንዲሁም 132,142 ሰዎች ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸውን ይፋ አድርጓል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ከሚሽን፣ በትግራይ ክልል በተከሰተው ችግር ምክንያት ስለተጎዱ ዜጎች የተሟላ መረጃ ባይኖርም በትግራይ ውስጥ የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ከ53,300 በላይ ኢትዮጵያውያን ወደ ምሥራቅ ሱዳን ደኅንነት ፍለጋ በመፍለስ በስደት ላይ እንደሚገኙ፣ በአሁኑ ወቅት በክልሉ ላለፉት ሁለት ወራት የተቋረጡ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ተቋማት በተለይም የውኃ፣ ሕክምና፣ መብራት፣ ባንክና መገናኛ አገልግሎቶች በሁሉም አካባቢዎች ወይም ከተሞች አገልግሎት መስጠት ባለመጀመራቸው በመሠረታዊ ፍጆታዎች በተለይም ምግብና ውኃ ዕጦት በማጋጠሙ ለረሃብ እንዳይጋለጡ ከፍተኛ ሥጋት መፈጠሩን ድርጅቶቹ ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ ሌላ በጥምቀት ወር በምዕራብ ወለጋ ዞን ጋዋ ቃንቃ፣ ጊላ ጎጎላና ሰቃ ጀርቢ ቀበሌዎችም ግድያዎች ሪፖርት ተደርገዋል፡፡ ይፋዊ መረጃዎች 32 ሰዎች እንደተገደሉ ቢያሳዩም፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሟቾች ቁጥር ከዚህም ሊበልጥ እንደሚችል ጠቁሟል፡፡ ኮሚሽኑ ይፋ ባደረገው ጥናት ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም. በትግራይ ክልል ሀፍታ ሁመራ ወረዳ በማካይድራ ከተማ ከ600 በላይ ዜጎች ማንነት መሠረት ባደረገ ኢሰብዓዊ የጭካኔ ግድያ ሰለባ መሆናቸውን ዜጎች በዱላ ተደብድበዋል፣ ንብረታቸው ተዘርፏል፣ ተቃጥሏል፡፡ ይህም አሰቃቂ ክስተት ባስከተለው ፍርኃት በአካባቢው ያሉ ዜጎች መኖሪያቸውን ጥለው እንደተሰደዱ ተገልጿል፡፡

በተመሳሳይ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ መተከል ዞን ቡለን ወረዳ በኩጂ ቀበሌ ታኅሣሥ 14 ቀን 2012 ዓ.ም. በተፈጸመ ጥቃት ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር 207 መድረሱንና ከነዚህ መካከል 133ቱ ወንዶችና 35ቱ ሴቶች መሆናቸው መገለጹ ይታወሳል፡፡ ከዚህ ሌላ አንድ የስድስት ወር ሕፃናትን ጨምሮ 17 ልጆችና 20 አረጋውያን መገደላቸውም ተገልጿል፡፡ እንዲህ ያሉ በክልሉ ሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸሙ ጭካኔ የተሞላባቸው ድርጊቶች በአሥር ሺሕዎች የሚቆጠሩ የአካባቢው ነዋሪዎች መኖሪያቸውን ለቅቀው እንዲሰደዱ ምክንያት ሆነዋል፡፡

ማክሰኞ ታኅሣሥ 20 ቀን 2013 ዓ.ም. የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልን አስመልክቶ የወጣው የቅርብ ጊዜ መረጃ እንደሚያሳየው፣ 29,688 ወንዶችና 26,037 ሴቶች ከመኖሪያ ቀዬአቸው ተፈናቅለዋል፡፡ ይህም በአጠቃላይ ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉትን ሰዎች ቁጥር ወደ 55,703 አድርሶ የነበረ ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ አጠቃላይ የተፈናቃዮች ቁጥር 113,000 መድረሱን ወቅታዊ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ እነዚህ ዜጎች ለውስብስብ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰትና ቀውስ ተጋላጭነታቸው እየጨመረ እንዳይሄድ በቂ ጥበቃ እንዲሁም አስቸኳይ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ናቸው ሲሉ ድርጅቶቹ አስታውቀዋል፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *