የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ‹‹በሕግ ተመራቂ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና ምክንያት፣ ራሱን በእሳት አቃጥሎ ስለሞተው የሕግ ተማሪ ጉዳይ ተጣርቶ ይቅረብልኝ›› ሲል ጠየቀ፡፡

የዲላ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ትምህርት ቤት ተማሪ የነበረው አብርሃም ዱሬሳ  በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት የመውጫ ፈተና በመውሰድ ላይ በነበረበት አራተኛው ቀን በተፈጠረ አጋጣሚ፣ ፈተናውን ባለመውሰዱ ምክንያት ሕይወቱን እንዳጠፋ ተነግሯል።

ከ12 ዓመታት በፊት የተጀመረው የመውጫ ፈተና፣ ተማሪዎች ከመመረቃቸው ወራት አስቀድሞ በአገር አቀፍ ፈተናዎች ድርጅት አዘጋጅነት የሚሰጥ ነው።

በተማሪው ሞት ምክንያት በተፈጠረው የሕዝብ ቁጣና የአካል ጉዳተኞች ጥያቄ በጉዳዩ ላይ ፓርላማው ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት፣ ከፈተናዎች ኤጄንሲ፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ከአካል ጉዳተኞች ማኅበራት ጋር ማክሰኞ ታኅሳስ 27 ቀን 2013 ዓ.ም. ውይይት አካሂዷል።

የፓርላማ አባላት የተከሰተው ሁኔታ ለምንና እንዴት እንደተፈጠረ፣  የተማሪውን ሞት በተመለከተ ለሕዝቡ ለምን በቂ ማብራሪያ እንዳልተሰጠበት ጠይቀዋል።

በግንቦት 2012 .ም. መደረግ የነበረበት የመውጫ ፈተና በአገሪቱ እየታዩ ባሉ የፀጥታ ችግሮችና የኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት መራዘሙንና ተማሪው ፈተናውን ለሦስተኛ ጊዜ እየወሰደ እንደነበር፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

በአብዛኛው በአገር አቀፍ ደረጃ የመውጫ ፈተና ለሦስት ጊዜያት የሚሰጥ መሆኑን፣ በመጀመርያ፣ በሁለተኛውና በሦስተኛው ዙሮች እንደሚያልፉ ሚኒስቴር ዴኤታው ገልጸዋል። ይሁን እንጂ ተማሪው ከሦስት ጊዜ በላይ ለፈተና እንደቀረበና የፈተና ሰዓቱ ሕጉ ከሚፈቅደው 30 ደቂቃ በላይ ለ45 ደቂቃ በመቆየቱ ምክንያት፣ በመጨረሻው የፈተና ቀን እንደተመለሰ አክለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተሰጠውን ፈተና መውሰድ ለመቻሉ፣ ሽሮሜዳ አካባቢ በሚገኘው ሠፈሩ ምሽት ላይ ቤቱን ዘግቶ በራሱ ላይ ጋዝ አርከፍክፎ እንዳቃጠለና ጉዳት እንደደረሰበት፣ ከዚያም የካቲት 12 ሆስፒታል ተወስዶ ሕክምና ቢደረግለትም ሕይወቱን ማትረፍ አለመቻሉን አስረድተዋል፡፡

የአገር አቀፍ ፈተናዎች ኤጄንሲ ዋና ዳይሬክተር ዲላሞ ኦቶሬ (ዶ/ር) በኩላቸው፣ በአገር አቀፍ ፈተና መመርያው መሠረት ከተፈቀደው ሰዓት በላይ ተፈታኞችን ወደ ፈተና ማስገባትም ሆነ ከፈተና ማስወጣት የማይቻል እንደሆነ፣ ፈታኞችም በፈተናው ወቅት ከተፈቀደው አሠራር ውጪ ከሄዱ እንደሚጠየቁ ተናግረዋል፡፡

ለአራት ቀናት የተካሄደው የመውጫ ፈተና ከመጀመሩ በፊት ለፈታኞችና ለተፈታኞች  በቂ ገለጻ መደረጉን የገለጹት ና ዳይሬክተሩ፣ ፈታኞች ከተሰጣቸው መመርያ ውጪ ለሰብዓዊነት ተብሎ የሚጣስ ሕግ አይኖርም ብለዋል።

ወደ ፈተና አዳራሽ ለመግባት ማንኛውም ተማሪ በእኩል ሰዓት አንደሚገባ ሕጉ ያስገድዳል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ለአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ደግሞ ተጨማሪ ሰዓት የሚሰጥበት አሠራር እንዳለ አክለው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዓይነ ሥውራን ማኅበር ፕሬዚዳንት ወሰን ዓለሙ በበኩላቸው፣ ተማሪው በቦታው የደረሰው በሰዓቱ እንደነበርና ወደ ፈተና ለመግባት የፈተና ኮድ ወይም መታወቂያ ባለመያዙ ወደ ቤቱ ተመልሶ እንዲያመጣ በመጠየቁ ምክንያት አጋጣሚው መፈጠሩን ተናግረዋል።

ሟች አጠገቡ ያሉ ቤተሰቦቹንና በወቅቱ የነበሩ ሰዎችን በመጠየቅና በማጣራት፣ ለተበዳዩ ካሳ የሚከፈልበት ሁኔታ እንዲያመቻች አክለው ጠይቀዋል።

ሰዓታት ከፈጀው ውይይት በኋላ ምክር ቤቱ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር፣ ከፈተናዎች ኤጄንሲና ከአካል ጉዳተኞች ማኅበራት ጋር በመሆን ጉዳዩን አጣርቶ እንዲያሳውቀው አሳስቧል፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *