የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የተለያዩ አካባቢዎች እየደረሱ ያሉ ግድያዎች፣ ድብደባና ማሰቃየት፣ እንዲሁም ሕገወጥ እስራቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሱ መምጣታቸው እጅግ አሳስቦኛል አለ፡፡

ኢሰመጉ ማክሰኞ ታኅሳስ 27 ቀን 2013 ዓ.ም. ምሽት ባወጣው መግለጫ፣ ከአሁን ቀድም በኦሮሚያ ክልል፣ በተለይም በምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች ውስጥ ያለው የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑንና መንግሥት ሕጋዊ፣ ትክክለኛና ተገቢ የሆኑ የመፍትሔ ዕርምጃዎችን እንዲወስድ፣ ጥቅምት 21 እና 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጣቸው አስቸኳይ ጋዜጣዊ መግለጫዎች ማሳሰቡን አስታውሷል፡፡

ሆኖም በእነዚህ አካባቢዎች ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰና በሰዎች ላይ የሚደርሰው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት እጅግ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን፣ ኢሰመጉ በየሳምንቱ ከሚያከናውነው የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ዳሰሳ ለመረዳት መቻሉን አስታውቋል፡፡

ኢትዮጵያ ፈርማ ያፀደቀቻቸውና የሕጎቿ አካል ያደረገቻቸው ዓለም አቀፍና አኅጉር አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶች ሰዎች ደኅንነታቸው ተጠብቆ፣ በማንኛውም ቦታ በሕይወት የመኖር ሰብዓዊ መብቶች እንዳሏቸው እንደሚደነግጉ ኢሰመጉ በመግለጫው አስረድቷል፡፡

የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥትም ማንኛውም ሰው ‹ሰው› በመሆኑ ብቻ የማይደፈርና የማይገሰስ በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደኅንነትና የነፃነት መብት እንዳለው በአንቀጽ 14 ሥር ቢደነግግም፣ ይሁንና በኦሮሚያ ክልል፣ ምዕራብ ወለጋ፣ ቄለም ወለጋ፣ ምሥራቅ ወለጋና ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞኖች ሥር ባሉ አካባቢዎች ፀጥታ አስካበሪዎችን ጨምሮ ሰላማዊ ሰዎች በሕይወት የመኖር መሠረታዊ መብታቸው በታጣቂ ኃይሎች፣ እንዲሁም የክልሉ መደበኛ ፖሊስና ልዩ ኃይል አባላት በሚወስዱት ዕርምጃ እየተጣሰ፣ ከፍርድ ውጪ መገደላቸውን፣ ለእንግልትና ለሕገወጥ እስሮች መዳረጋቸውን አስታውቋል፡፡

ለአብነት ያህል ያለው የኢሰመጉ መግለጫ ታኅሳስ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን፣ በዓባይ ጮመን ወረዳ፣ ጃሬ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ምሽት 4፡00 ሰዓት አካባቢ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት፣ መርጋ ዳንጋላና ጫላ ተረፈ የተባሉ ሁለት የቀበሌ ታጣቂ ሚሊሻዎች ተገድለዋል ብሏል፡፡ ጥቃት ፈጻሚዎቹ የሁለት ግለሰቦችን ቤትም ማቃጠላቸውን ኢሰመጉ ከአካባቢው የደረሰው መረጃ እንደሚያሳይና በዞኑ ጃርዳጋ፣ ጃርቲና አሙሩ ወረዳዎችም ተመሳሳይ ግድያዎች ስለመፈጸማቸውም አቤቱታዎች እንደደረሱት ገልጿል፡፡

በሌላ በኩል ሰዎች መረጃ የማግኘትና የማስተላለፍ መብት ቢኖራቸውም፣ በምዕራብ ወለጋና ቄለም ወለጋ ዞኖች የስልክና የኢንቴርነት አገልግሎቶች ላለፉት ሦስት ወራት የተቋረጡ በመሆናቸው የአካባቢው ሰዎች የዕለት ተዕለት ኑሮዋቸው መስተጓጎሉን ኢሰመጉ ጠቁሟል፡፡

በመሆኑም የኦሮሚያ ክልልና የፌዴራል መንግሥት የሚመለከታቸው አካላት በአካባቢዎቹ ለረጅም ጊዜ የዘለቁትን የደኅንነት ሥጋቶች በመለየት የረጅምና የአጭር ጊዜ ዕቅዶችን በማዘጋጀት ወደ ፈጣን ዕርምጃ እንዲገቡ፣ የተለያዩ የመብት ጥሰቶችን የሚፈጽሙም በሕግ እንዲጠየቁ በማድረግ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ኢሰመጉ በመግለጫው አሳስቧል፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *