የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር በታኅሳስ 2013 ዓ.ም. አጋማሽ በምዕራብ፣ በደቡብና በመካከለኛው ትግራይ ባካሄደው ወቅታዊ ግምገማ፣ እንዲሁም በሰሜን ጎንደር፣ በሰሜን ወሎ፣ በመተከል ዞን፣ በኮንሶና ቤንቺ ሸኮ አካባቢዎች ከ2.53 ሚሊዮን በላይ ተጋላጭ ሰዎች አጠቃላይና ተጨማሪ የምግብ ድጋፍ እንደሚያስፈልገው አስታወቀ፡፡
በእነዚህ አካባቢዎች መጠለያና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች፣ መተዳደሪያና ቅድመ ማገገም፣ የመጀመርያ ሕክምና ዕርዳታና የአምቡላንስ አገልግሎቶች፣ የሥነ ልቦና፣ የማኅበራዊና መልሶ ማቋቋም፣ እንዲሁም የቤተሰብ ማገናኘት ድጋፎች፣ የጤና ማዕከል ተቋማትንና የቀይ መስቀል ቅርንጫፎችን ለመጠገንና መልሶ ለመገንባት ከዘጠኝ ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልገው የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ አበራ ቶላ አስታውቀዋል፡፡ ኅብረተሰቡ የገናና የጥምቀት በዓልን ሲያስብ ሳይፈልጉና ሳይወዱ በግዳጅ ለመከራ የተጋለጡ፣ የተራቡ፣ የታረዙና የተቸገሩ ወገኖችን እንዲያስብና እንዲረዳ ጠይቀዋል፡፡
በተለይ ባለፉት ሁለት ወራት የተከሰቱትን ግጭቶች ተከትሎ በትግራይ፣ በቤንሻንጉል ጉምዝ፣ በደቡብና በኦሮሚያ ክልሎች በ30 ሚሊዮን ብር ወጪ ከ200 ሺሕ ለሚበልጡ ሰዎች የሕክምና፣ የምግብ፣ የመጠለያና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች፣ የሥነ ልቦና ማኅበራዊና መልሶ የማቋቋም፣ ቤተሰብ የማገናኘት አገልግሎቶችን ሲያከናውን መቆየቱን አቶ አበራ ገልጸዋል፡፡ 300 የበጎ ፈቃደኞችና ሠራተኞችንና 100 አምቡላንሶችን በማሰማራት በቅርቡ በተከሰተው የአንበጣ መንጋ፣ ከዚያ በኋላ በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑትን ወገኖች ሕይወት ለማዳንና መልሶ ለማቋቋም ቀይ መስቀል በንቃት መሳተፉንም አስታውቀዋል፡፡
‹‹አደጋዎች ባለቡትና ሰብዓዊ ቀውስ በሚከሰትበት ቦታ ሁሉ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ሁልጊዜም ቀድሞ ይገኛል፣ ስለሆነም በጎ ፈቃደኞቹንና ሠራተኞቹን በማስተባበር ሕይወትን ለማዳንና ኑሮን ከመጠበቅ አንፃር የተለያዩ ሰብዓዊ አገልግሎቶችን ይሰጣል፤›› ያሉት አቶ አበራ፣ ማኅበሩ በ2012 የበጀት ዓመት የአምቡላንስና የመጀመርያ የአየር አገልግሎቶች፣ የምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ዕቃዎች ድጋፍ፣ የሥነ ልቦናና ማኅበራዊ ድጋፍ፣ የቅድሚያ ማገገምና የመልሶ ማቋቋም ድጋፍ፣ የቤተሰብ ግንኙነቶችን ወደነበሩበት መመለስ፣ የኮሮና ወረርሽኝ ዝግጁነትና ምላሽ ሥራዎችን አከናውኗል ብለዋል፡፡
በ2012 ዓ.ም. ማኅበሩ ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ከ36 ሚሊዮን ለሚበልጡ ግለሰቦች ድጋፍ ማድረጉን፣ በ2013 በጀት ዓመት የመጀመርያ ሩብ ዓመት ደግሞ በ70 ሚሊዮን ብር ወጪ 138 ሺሕ ሰዎችን መድረሱንም አክለዋል፡፡
የ2012/13 ዓ.ም. የአንበጣ ወረርሽኝ እስከ ጥቅምት አጋማሽ ድረስ በመቶ ሺዎች በሚቆጠር ሔክታር የሰብልና የግጦሽ መሬቶች ላይ ጉዳት ማድረሱን ይህም በአማራ፣ በትግራይ፣ በኦሮሚያ፣ በድሬዳዋ፣ በአፋር፣ በሐረሪና በሶማሌ ክልሎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ግለሰቦችን ለጉዳት ማጋለጡንም ተናግረዋል፡፡
በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ዳሰሳ በተደገባቸው ሥፍራዎች ለጉዳት መጋለጣቸው ለተረጋገጠ 2,534,297 ሰዎች 9,048,581,423 ብር እንደሚያስፈልግ ገልጸው፣ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያለው ኅብረተሰብ የጉዳት ተጋላጮችን በዓይነትና በገንዘብ እንዲረዳ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን እ.ኤ.አ. በመስከረም 2020 ያወጣውን ሪፖርት ጠቅሰውም፣ የጎርፍ አደጋም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን መጉዳቱን ከእነዚህ ውስጥ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በመላ አገሪቱ መፈናቀላቸውን ተናግረዋል፡፡
የኮሮና ወረርሽኝን አስመልክቶ በኢትዮጵያ በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ሰዎች ላይ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ ጤና፣ ትምህርትና ፖለቲካዊ ተፅዕኖዎችን እያደረሰ መሆኑን፣ በእነዚህ በተወሳሰቡ ተከታታይ የሰብዓዊ ቀውሶች ላይ የተጨመረው የቅርብ ጊዜ ግጭትና ሁከትም የሰብዓዊ ምላሹን ውስብስብ አድርጎታል ብለዋል፡፡
ግጭቶች፣ የጎርፍ መጥለቅለቅ፣ የአንበጣ መንጋ፣ ኮሮና ወረርሽችና ሌሎችም ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ኢትዮጵያን በማወክ ተከታታይ ሰብዓዊ ቀውስ አስከትለዋል፡፡ ኢትዮጵያ በቅርቡ የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ በአግባቡ ሳትወጣ ትግራይ፣ ኦሮሚያ፣ ቤንሻንጉል ጉምዝና ደቡብ ክልሎችን ያዳረሰና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት አደጋ ላይ የጣለ ውስጣዊ ግጭትና ብጥብጥ አጋጥሟታል፡፡
በሚሊዮን የሚቆጠሩ በአገር ውስጥ የተፈናቀሉ ዜጎች በተለይ ሕፃናት፣ ሴቶች፣ አዛውንቶች አካል ጉዳተኞችና ቁስለኞች የግጭት አካባቢዎችንና ሌሎች የተፈጥሮ አደጋዎችን በመሸሽ ቤታቸውን ለቀው ለመሰደድ ተገደዋል ሲሉም አቶ አበራ ገልጸዋል፡፡
ማኅበሩ ለተጎዱ ወገኖች ዕርዳታ ለማሰባሰብ ማክሰኞ ታኅሳስ 27 ቀን 2013 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ፣ ከኅዳር 29 እስከ ታኅሳስ 6 ቀን 2013 ዓ.ም. በአምስት ክልሎች በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩ ችግሮችን አስመልክቶ የሠራውን ዳሰሳ ያቀረቡት የማኅበሩ የአደጋ ሥጋት መምርያ ምክትል ዋና ጸሐፊ እንዳሉት፣ በአካባቢዎቹ በደረሱ ግጭቶችና አደጋዎች ሰዎች ሞተዋል፣ ቤተሰብ ተለያይቷል፣ የኑሮ መመሰቃቀል ገጥሟል፣ ቤት ተቃጥሏል፣ የቁም እንስሳት ተዘርፈዋል፣ እህልና እርሻ ወድሟል፣ ተዘርፏል፣ እንዲሁም የሥነ ልቦና ችግር ገጥሟል፡፡
ሰዎች በዛፍ ጥላ ሥርና ሜዳ ላይ እንዲኖሩ መገደዳቸውን፣ የመንግሥት ተቋማት በከፊልና ሙሉ ለሙሉ መዘረፋቸውን፣ ማኅበሩ በአንበጣ ወረርሽኝ፣ በጎርፍ፣ በኮሮና ወረርሽኝ በኋላም በትግራይና በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰተ ግጭት የተጎዱትን ለመርዳት እየተሯሯጠ ቢሆንም፣ በአምቡላንሶቹና በሠራተኞቹ ላይ ጉዳት መድረሱንም ገልጸዋል፡፡ አምቡላንሶችን መዝረፍ፣ ጉዳት ማድረስና በጥይት መደብደብ እንዳጋጠመም አክለዋል፡፡
ዳሰሳ ከተደረገባቸው ሥፍራዎች በምዕራብ ትግራይና ሰሜን ጎንደር 677 ሺሕ ሰዎች ጉዳት የደረሰባቸውና የተፈናቀሉ ናቸው፡፡ በማዕከላዊ፣ በሰሜን ምዕራብ፣ በምሥራቅና ደቡብ ትግራይ 1.3 ሚሊዮን ሰዎች፣ በሰሜን ትግራይ፣ ሰሜን ወሎና አፋር 395 ሺሕ ሰዎች፣ በመተከል 340 ሺሕ ሰዎች፣ እንዲሁም ኮንሶ፣ አሌ፣ ደራሼ፣ ቤንች ሸኮ (ጉራፈርዳ) 205 ሺሕ ሰዎች ለጉዳቱ የተጋለጡ ሲሆን፣ ማኅበሩ እነዚህን በቀጣዮቹ ስድስት ወራት ለመደገፍ ከዘጠኝ ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልገው ምክትል ዋና ጸሐፊው አስታውቀዋል፡፡
በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ዳሰሳ በተደገባቸው ሥፍራዎች ለጉዳት መጋለጣቸው ለተረጋገጠ 2,534,297 ሰዎች 9,048,581,423 ብር እንደሚያስፈልግ ገልጸው፣ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያለው ኅብረተሰብ የጉዳት ተጋላጮችን በዓይነትና በገንዘብ እንዲረዳ ጥሪ አቅርበዋል፡፡