ከመጋቢት መጨረሻ እስከ ሚያዝያ መጨረሻ እንዲሰማ ትዕዛዝ ተሰጥቷል
ከድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ ከተማ በተቀሰቀሰ ግጭትና ሁከት በተፈጠረ የሰዎች ግድያ፣ አካል ጉዳትና ንብረት ውድመት ጋር በተያያዘ ክስ በቀረበባቸው እነ አቶ እስክንድር ላይ የዓቃቤ ሕግን ምስክሮች ለመስማት ቀጠሮ ተሰጠ፡፡
ቀጠሮውን የሰጠው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የሕገ መንግሥትና የሽብርተኝነት አንደኛ ወንጀል ችሎት ታኅሳስ 16 ቀን 2013 ዓ.ም. እንዳስታወቀው፣ የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) አመራሮች በሆኑት፣ አቶ እስክንድር ነጋ፣ አቶ ስንታየሁ ቸኮል፣ ወ/ሮ ቀለብ ስዩምና ወ/ሮ አስካለ ደምሴ እንዲሁም በመዝገቡ ተካቶ የተከሰሰው አቶ ጌትነት በቀለ ላይ የዓቃቤ ሕግ ምስክሮቹን መጋቢት 29 እና 30፣ ሚያዝያ 13፣ 14 እና ከሚያዝያ 18 እስከ 28 ቀን 2013 ዓ.ም. እንዲያሰማ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
ፍርድ ቤቱ የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች የሚሰሙበትን ቀናት የተናገረው፣ በዕለቱ ችሎቱን የቀጠረበትን የዓቃቤ ሕግ ክስን መሻሻል ካረጋገጠና ተከሳሾቹ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ከሰጡ በኋላ ነው፡፡
ዓቃቤ ሕግ ባቀረበው ክስ ላይ ተከሳሾቹ በፌስቡክ በመጠቀም ስም ስለማጥፋታቸው ብቻ በመጥቀሱ ‹‹በምን አድራሻና ስም እንዳጠፋን አልተገለጸም›› በማለታቸው፣ ክሱን እንዲያሻሽል ትዕዛዝ እንደሰጠ መዘገቡ ይታወሳል፡፡ በመሆኑም ዓቃቤ ሕግ ክሱን አሻሽሎ፣ ተከሳሾቹ ይጠቀሙበት የነበረው አድራሻ ‹‹አማራ ማስ ሚዲያ እና ኦሮሚያ ላቭ›› የሚል መሆኑን በክሱ ገልጾ ማቅረቡን ችሎቱ አረጋግጧል፡፡ ሌላው ዓቃቤ ሕግ እንዲያሻሽል የተጠየቀው ክስ፣ ወ/ሮ አስካለ ተልዕኮ ተቀብላ ወጣቶች በቄሮዎችና በኦሮሞ ተወላጆች ላይ ዕርምጃ እንዲወስዱ ትዕዛዝ የሰጠችው ከጦር ኃይሎች ወደ ኮልፌ በሚወስደው ታክሲ መያዣ ቦታ ላይ መሆኑን በመግለጽ ‹‹ትዕዛዝ የሰጠችው የት ሆና ነው? ትክክለኛ ቦታው አልተገለጸም›› የሚለውን ተቃውሞ አሻሽሎ ማቅረቡንም ፍርድ ቤቱ አስታውቆ፣ ተከሳሾቹ የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ ጠይቋል፡፡
አቶ እስክንድር የእምነት ክህደት ቃሉን ከመስጠቱ በፊት ‹‹ይህ ለታሪክ የሚቀመጥ በመሆኑ በድምፅ መቅረጫ እንዲመዘገብለት ፍርድ ቤቱን ጠይቆ ነበር፡፡ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ምላሽ ‹‹የእምነት ክህደት ቃላችሁን ስጡና አቤቱታ ካላችሁ እንሰማችኋለን›› በማለቱ፣ ሁሉም ተከሳሾች በተመሳሳይ ሁኔታ ድርጊቱን አለመፈጸማቸውንና ጥፋተኛም አለመሆናቸውን ከተናገሩ በኋላ፣ የየግላቸውን አቤቱታ ለፍርድ ቤቱ አቅርበዋል፡፡
አቶ እስክንድር ለፍርድ ቤቱ ባቀረበው አቤቱታ እንደገለጸው፣ ከአሥር ጊዜ በላይ ተከሶ ያውቃል፡፡ በኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክ ጥፋተኛ አይደለም፡፡ ክሱ የፖለቲካ ክስ ነው፡፡ ‹‹ይህንን የክስ ሒደት ፈጣሪና አምላክ ያውቃል፡፡ እውነት ቆይቶም ቢሀን ይወጣል›› ብሏል፡፡ የአቶ እስክንድርን አቤቱታ ዓቃቤ ሕግ በመቃወም፣ ተከሳሾቹ ክሱን ፖለቲካዊ እያደረጉት በመሆኑ፣ ችሎቱ አካሄዱን እንዲያስተካክል ሲጠይቅ፣ የተከሳሾቹ ጠበቆች ‹‹ዓቃቤ ሕግ እምነት ክህደት ሲሰጥ ተቃውሞ ማሰማት አይችልም›› በማለት ተቃውመውታል፡፡
አቶ ስንታየሁ ለፍርድ ቤቱ ባቀረበው አቤቱታ ደግሞ እንደተናገረው፣ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ሕዝብ ይመዝነዋል፡፡ የሚፈልጉት ሕዝብ እንዲሰማቸው መሆኑንና 14 ሰ ዎችን እንደገደሉ አድርጎ ዓቃቤ ሕግ ቢከሳቸውም፣ እነሱ 14 ሰዎችን ይመግቡ እንደሆነ እንጂ እንደማይገድሉ ተናግሯል፡፡ ክሱ የሐሰትና ፖለቲካዊ እንደሆነ ጠቁሞ፣ የተከሰሱት ምርጫ ለማድረግ እየተዘጋጁ ባሉበት ወቅት እንደሆነም ገልጿል፡፡
ዓቃቤ ሕግ በድጋሚ ባቀረበው ተቃውሞ ችሎቱ ክርክሩን መምራት እንዳቃተው በመናገር ተከሳሾች ሲሳደቡ ዝም የሚለው ተፅዕኖ ላይ ወድቆ እንደሚመስለው አስረድቷል፡፡ ፍርድ ቤቱም የዓቃቤ ሕግ አቤቱታ ትክክል መሆኑን በማመን፣ ተከሳሾች በአግባቡ ቃላቸውን እንዲሰጡ አስጠንቅቋል፡፡
ሦስተኛዋ ተከሳሽ ወ/ሮ ቀለብ ባቀረበችው አቤቱታ፣ ፖሊስ ጠርጥሮ ፍርድ ቤት ሲያቀርባት የሰውም ሆነ የሰነድ ማስረጃ እንዳላቀረበባት አስታውሳ፣ የመሀል ዳኛ ‹‹ጠርጥሬሻለሁ›› ስላሏት ብቻ መታሰሯን ገልጻለች፡፡ ለአገር፣ ለፍትሕና ለሰብዓዊነት ባደረገችው ትግል መታሰሯ እንዳልቆጫትም አክላለች፡፡ በመቀጠልም ክሱ ‹‹የቡችላ ክስ ነው›› በማለቷ ዓቃቤ ሕግ ከፍተኛ የሆነ ተቃውሞ አቅርቧል፡፡ ችሎት መድፈር በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ቅጣት እንዲጥል ሲያመለክት፣ አቶ እስክንድርና አቶ ስንታየሁ ትክክል እንደሆነች ድጋፋቸውን አሰምተዋል፡፡ በመሆኑም ዓቃቤ ሕግ ሦስቱም ተከሳሾች ችሎት በመድፈር ወንጀል እንዲቀጡለት በድጋሚ ሲጠይቅ፣ ወ/ሮ አስካለም የእሷም ሐሳብ መሆኑን በመናገር ተባባሪ መሆኗን ገልጻለች፡፡ ዓቃቤ ሕግም አራቱም ተከሳሾች ችሎቱን እንደደፈሩ አጽንኦት ሰጥቶ በማመልከት ቅጣቱ እንዲጣልባቸው ጠይቋል፡፡
ከባልደራስ አባላት የመጨረሻ ቃሏን የሰጠችው ወ/ሮ አስካለ ለፍርድ ቤቱ እንደገጸችው፣ የተከሰሰችው በምትሠራበት የመንግሥት ተቋም ውስጥ ኮንዶሚኒየምና መሬት ዝም ብሎ ሲሰጥ በመቃወሟ ነው፡፡ ብዙ ጥቅማ ጥቅም፣ ቤትና ሥልጣን ‹‹እንስጥሽ›› ሲሏት ባለመቀበሏ፣ ጥያቄው በቀረበላት ከ42 ቀናት በኋላ መታሰሯንና መከሰሷን ለፍርድ ቤቱ አስረድታለች፡፡
የዋስትና መብቱ ተከብሮለት በውጭ ሆኖ በመከራከር ላይ የሚገኘውና በመዝገቡ የተካተተው አቶ ጌትነት በቀለም አቤቱታውን አሰምቷል፡፡ እንደገለጸውም፣ ሽልማት ሲጠብቅ መታሰሩ አሳዝኖታል፡፡ በክሱ ውስጥ ጋላ ብሎ እንደተሳደበ ቢገለጽም፣ እሱ ግን እንዳላለና ሊል እንደማይችል በመናገር፣ እሱም ሆነ ባለቤቱ ኦሮሞዎች መሆናቸውን አስረድቷል፡፡ ለክስ የተዳረገውም ከሚሠራበት ድርጅት ተመርጦ ለሥልጠና ወደ ውጭ አገር ሊሄድ ሲል፣ በተቋሙ ውስጥ ሙስና እንዴት እንደሚፈጸም ለፌዴራል ፖሊስ መረጃ ከሰጠ በኋላ ‹‹እንዴት መሥሪያ ቤትህን ትከሳለህ?›› ተብሎ መሆኑንም ገልጿል፡፡
የግራ ቀኙን አቤቱታና ክርክር ከሰማ በኋላ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ተከሳሾቹ በችሎት መድፈር ወንጀል እንዲቀጡ ያቀረበው አቤቱታን በሚመለከት ሁለቱም ወገኖች በስሜታዊነት ያደረጉት ይሆናል በሚል ፍርድ ቤቱ መገንዘቡን በመግለጽ በማስጠንቀቂያ እንዳለፈው ተናግሮ፣ የዓቃቤ ሕግ ምስክሮችን በተሰጠው ቀጠሮ መሠረት እንደሚሰማ አስታውቋል፡፡ ተከሳሾቹ ግን የቀጠሮው ቀን መርዘሙ በምርጫ እንዳይሳተፉ እንደሚያደርጋቸው አራቱም ተከሳሾች በአንድ ላይ በመናገር ተቃውሞአቸውን አሰምተዋል፡፡ ችሎቱ በድምፅ በመታወኩ ፖሊሶች በርከት ብለው ወደ ችሎቱ በመግባት ታዳሚዎች እንዲወጡ ሲጠይቁ ‹‹አንወጣም›› በማለታቸው በኃይል እየሳቡ እንዲወጡ በማድረግ፣ የችሎት አዳራሹን አስለቅቀዋል፡፡ ከችሎት ውጪ አንድ ላይ የቆሙት ታዳሚዎች ተከሳሾቹ ሲወጡ ጭብጨባ በማሰማት ለመረበሽ ሲሞክሩ ፖሊስ ከፍርድ ቤቱ ጊቢ በማስወጣት እንዲበታተኑ አድርጓል፡፡