የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በተለይም በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል እየተፈጸመ ባለው የዜጎች ሞትና የሰላም አጦት ዙሪያ በዝግ ተወያይቶ አፋጣኝ ሪፖርት እንዲቀርብለት ጠየቀ ።
ምክርቤቱ እየታየ ያለውን ችግር አስመልክቶ ዛሬ ታህሳስ 15ቀን2013 ጠንከር ባለ መልኩ ውይይት ማድረጉን ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የምክርቤቱ አባል ለሪፖርተር ገልፀዋል።
የፓርላማ አባላቱ ኦነግ ሸኔ፣ህወሀትና የቤንሻንጉል ጉምዝ ነፃ አውጭ ግንባር የተባሉ ድርጅቶች በአሸባሪነት እንዲሰየሙ ለአስፈፃሚው የመንግስት አካል መየጠየቃቸውንና መንግስት የሚደርስበትን ውሳኔ እንዲያሳውቅ መጠየቃቸው ተነግሯል ።
በመጨረሻም ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን እየተደረገ ያለውን የዜጎች ሞት በመገምገምና የአሰፈፃሚ አካላቱን እንቅስቃሴ በመፈተሽ ምክርቤቱ ላቀረቧቸው ጥያቄዎች የተጠናቀረ መረጃ አዘጋጅተው በአንድ ሳምንት ውስጥ እንዲያቀርቡ ለፓርላማው የህግ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴና ለሰላምና የውጭ ግንኙነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መመሪያ ሰጥቷል።
በዚሁ ለሚዲያ አባላት ዝግ በነበረው የፓርላማው 6ኛ አመት 5ኛ መደበኛ ጉባኤ የመከላከያ ሠራዊት ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ በመጀመሪያ ንባብ በሙሉ ድምጽ ማፅደቁ ተሰምቷል ።