የሚኒስትሮች ምክር ቤት የኅትመትና የብሮድካስት መገናኛ ብዙኃን መተዳደሪያና ለበይነ መረብ ሚዲያ የሕግ ማዕቀፍ ሆኖ ለመጀመርያ ጊዜ ተግባራዊ የሚሆነው፣ ረቂቅ የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ አፅድቆ ለፓርላማ መራው፡፡

አዋጁ የመረጃና የፕሬስ ነፃነት ተግባራዊነት በከፍተኛ ሁኔታ የሚደግፍ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

በመገናኛ ብዙኃን ረቂቅ አዋጁ ከተካተቱ ከፍተኛ ማሻሻያዎች መካከል አንዱ የመገናኛ ብዙኃን በስም ማጥፋት ወንጀል እንዳይጠየቁ የሚለው ድንጋጌ ግንባር ቀደም ሲሆን፣ የውጭ ዜግነት ያላቸው በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ መዋዕለ ንዋያቸውን በሕግ ተገድቦ ማፍሰስ እንዲችሉ የተካተተው ድንጋጌ ሌላው ነው፡፡

ሥራ ላይ ባለው አዋጅ መሠረት የውጭ ዜግነት ያለው ማንኛውም ሰው፣ በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ባለቤት እንዳይሆን ይከለክላል። አዲስ በተረቀቀው አዋጅ ላይ ግን የውጭ ዜግነት ያላቸው እስከ 25 በመቶ ብቻ የባለቤትነት ድርሻ እንዲኖራቸው የሚፈቅድ ድንጋጌ ተካቷል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ለመገናኛ ብዙኃን ፈቃድ የሚሰጠውና የሚቆጣጠረው፣ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን የሚባለውን ተቋም በድጋሚ የሚያቋቋም ድንጋጌ እንዳካተተ ለማወቅ ተችሏል።

ይህ ተቋም፣ ‹‹የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን›› በሚባል አዲስ ስያሜ በድጋሚ እንዲቋቋም በረቂቁ ከቀረበው ድንጋጌ በተጨማሪ፣ የተቋሙ ቦርድ አባላት የፖለቲካ ፓርቲ አባል መሆን አይችሉም፡፡ እንዲሁም የተቋሙም ተጠሪነት በቀጥታ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሆን እንዳለበት የሚገልጽ ድንጋጌ አካቷል።

መንግሥት በመገናኛ ብዙኃን የሚፈጸሙ ስህተቶችን በራሱ በቀጥታ እንዲታረሙ ማድረጉ በመገናኛ ብዙኃን ነፃነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድር በመሆኑ፣ የመገናኛ ብዙኃን ራሳቸውን በራሳቸው የሚቆጣጠሩበትና የሚያርሙበት የመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት  የመቋቋምን  አስፈላጊነት  ዕውቅና  በመስጠት፣  የዚህ  ምክር  ቤት  አደረጃጀና  አሠራር  እንዲጠናከር  የመገናኛ  ብዙኃን  ባለሥልጣን  ተገቢውን  ድጋፍ  እንዲያደርግ  በረቂቅ  ድንጋጌው  ተካቷል።

አሁን ባለው ሕግ የበይነ መረብ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ብቻ የመገናኛ ብዙኃን አገልግሎቶችን የሚሰጡ፣ የጽሑፍም ሆነ የምሥል መረጃ የሚያቀርቡ ድረ ገጾች መመዝገብና ፈቃድ እንዲወስዱ የሚያስገድድ ድንጋጌ የለም። ለሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ግን እንዲህ ያሉ መገናኛ ብዙኃንም መመዝገብና ፈቃድ ማግኘት እንዳለባቸው ይደነግጋል።

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *