በትግራይ ክልል በነበረው ውጊያ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ሊመረምር ነው

ካለፈው ዓመት ጀምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተፈጠሩት ውጥንቅጦች ብዙ አበሳዎች የታዩበት ጊዜ የሆነውን ያህል በጎ ምሳሌ የሚሆን ማኅበረሰብ የታየበት፣ እንዲሁም ሰለባ ለሆኑ ወገኖች ድምፅ የሚሆኑ ተሟጋቾች መጠንከር የታየበት ጊዜም ነበር ተብሏል፡፡

ይህ የተገለጸው ሐሙስ ታኅሳስ 1 ቀን 2013 ዓ.ም. ዘንድሮ ለ71ኛ ጊዜ የሚከበረውን የዓለም የሰብዓዊ መብት ቀን በተመለከተ በተዘጋጀው የመዝጊያ ሥነ ሥርዓት ላይ ነው፡፡ የሰብዓዊ መብት ቀኑ በኢትዮጵም ለተከታታይ አሥር ቀናት በተለያዩ ዝግጅቶች የተከበረ ሲሆን የበዓሉ ፍጻሜ በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል በተዘጋጀ የውይይት ኩነት ተጠናቋል፡፡

በዕለቱም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን ጨምሮ የተባበሩት መንግሥታት፣ የአፍሪካ ኅብረት የሰዎችና የሕዝቦች መብት ኮሚሽን እንዲሁም በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ላይ የሚንቀሳቀሱ መንግሥታዊ የሆኑና መንግሥታዊ ያልሆኑ የመብት አቀንቃኞችና፣ ተሟጋቾች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

በዕለቱም የመክፈቻ ንግግር ያቀረቡት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር)፣ ምንም እንኳ ካላፉት ሁለት ዓመት ተኩል ወዲህ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል የሰብዓዊ መብት ተስፋ ሰጪ መሻሻሎች ቢስተዋሉም፣ በአገሪቱ የተለያዩ ክልሎች እየጨመሩ በመጡ ግጭቶች፣ በንጹኃን ዜጎች ደህንነትና በሕይወት የመኖር መብት ላይ እየተከሰቱ ያሉ አደጋዎች አስደንጋጭ የሚባል ደረጃ ላይ መድረሻቸውን አመልክተዋል፡፡

በቀደሙ ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ በመንግሥት የሚደረጉ የሰብዓዊ ጥሰቶች ከፍተኛ እንደነበሩ አስታውሰው፣ ለመብት ተሟጋቾች በሰብዓዊ መብት ጉዳይ ላይ መንቀሳቀስ የማይታሰብ ደረጃ ላይ ደርሶ እንደነበር አመልክተዋል፡፡

ኮሚሽነሩ በንግግራቸው ካነሷቸው ዋና ዋና ጉዳዮች ውስጥ ኢትዮጵያ በቅርቡ የገጠሟት ፈተናዎች ይገኙበታል፡፡ ይህንን በተመለከተ ሲያስረዱ ‹‹ኢትዮጵያ በቅርቡ ያጋጠማት ፈተና ከባድ ቢሆንም ብዙ በጎ ነገሮች እንዳሉም የተረዳንበት መልካም አጋጣሚም ነበር፤›› ብለዋል፡፡

‹‹አገር ውስጥ በተፈጠሩት ውጥንቅጦች ብዙ አበሳዎች ብናይም፣ ምሳሌ የሚሆን ማኅበረሰብ እንዳለን ያየነበት ጊዜም ነበር፡፡ የሰብዓዊ መብት ማራመድ ሥራ መስፋፋት ታይቶበታል፣ ድምፅ አልባ ለሆኑ ዜጎቻችንም ድምፅ የሚሆኑ ተሟጋቾች ጠንከር ብለው የተስተዋሉበት ወቅት ነበር፤›› ሲሉም ዶ/ር ዳንኤል አስረድተዋል፡፡

ይሁን እንጂ ካለፈው ዓመት ጀምሮ በኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች የመብት ጥሰትና የዜጎች ግድያ እየተባበሰ መምጣቱን የሚገልጹት ዶ/ር ዳንኤል፣ እነዚህም ችግሮች እየተከሰቱ ያሉት የተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖች በሚፈጥሩት የጥላቻ ቅስቀሳና ግጭቶች መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ለአብነትም በተለያየ ክልሎች በተለይም በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ ክልል እንዲሁም ባለፈው ወር በማይካድራ የተከሰተውን ጨምሮ፣ በተለያዩ የትግራይ ክልል አካባቢዎች የበርካታ ንፁኃን ዜጎች ግድያን በማንሳት አብራርተዋል፡፡

በቅርቡ በማይካድራ ከ600 በላይ የሚሆኑ ንፁኃን ዜጎች በኢሰብዓዊ መንገድ መጨፍጨፋቸውን በተመለከት ኮሚሽኑ ባለሙያዎችን ልኮ የቅድመ ምርመራ አከናውኖ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት ማቅረቡን ያወሱት ኮሚሽነሩ፣ ግጭቱ በከፋባቸው በማይካድራና በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች የተሟላ ምርመራ ተደርጎ ሙሉ ግኝቱን ለማጠናቀቅ ሥራው መጀመሩን ገልጸዋል፡፡

ዓለም ዓቀፉ የሰብዓዊ መብት ቀን የመዝጊያ ሥነ ሥርዓት መጠናቀቅን ተከትሎ ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ፣ በአገሪቱ ከቅርብ ወራት ወዲህ ጀምሮ በተለያዩ ሥፍራዎች እየተከሰቱ ያሉትን የጅምላ ጭፍጨፋና ተያያዥ ጎዳዮች በተመለከተ በኮሚሽኑ እየተደርጉ ያሉ የምርመራ ሥራዎችን ዘርዝረዋል፡፡

በዚህም መሠረት በቅርቡ በማይካድራ የተፈጸመውን ጭካኔ የተሞላበት ግድያ ከ600 በላይ ንጹኃን ሕይወት ማለፉን በቅድመ ሪፖርቱ ይፋ ካደረገበት ዕለት በኋላ በመቶዎች ተጨማሪ አስከሬኖች መገኘታቸው የተረጋገጠ መሆኑንና በአሁኑ ወቅትም ሁለተኛ ዙር ምርመራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

ነገር ግን በሁለተኛ ዙር የሚካሄደው ምርመራ በማይካድራ ብቻ ያልተወሰነና የመከላከያ ሠራዊትና በትግራይ ክልል ኃይሎች መካከል ጦርነት የተካሄደባቸውን ቦታዎች ሁሉ የሚያጠቃልል እንደሆነም አመልክተዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር ኮሚሽኑ ከስብዓዊ መብት ጥሰትና ከንጹኃን ዜጎች ግድያ ጋር በተያያዘ ካለፈው ዓመት ጀምሮ መጠነ ሰፊ ግጭቶች በተስተዋለባቸው አካባቢዎች ባለሙያዎችን በማሰማራት የምርመራ ተግባራት እያካሄደና በአብዛኛው ቦታዎች የተካሄዱ የመረጃ ማሰባሰብና የትንተና ሥራዎች እየተገባደዱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከእነዚህ ሥፍራዎች ሰኔ 2012 ዓ.ም. የድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ መገደል ተከትሎ በበርካታ የኦሮሚያ ክልል ሥፍራዎች፣ በደቡብ ክልል ኮንሶ አካባቢ፣ በጥቅምትና ኅዳር 2013 ዓ.ም. በምዕራብ ኦሮሚያ በወለጋ አካባቢዎች እንዲሁም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ የመተከል ዞንን ጨምሮ በተለያዩ ሥፍራዎች የተስተዋሉ ተደጋጋሚ የንጹኃን ዜጎች ግድያ፣ የመብት ጥሰቶችን፣ መፈናቀልንና የንብረት ውድመትን የተመለከቱ ግኝቶችን የሰነዱ ሪፖርቶች በመገባደድ ላይ ናቸው ብለዋል፡፡ የምርመራ ግኝቶቹም ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካለት በቅርቡ የሚቀርቡና ለሕዝብም ይፋ እንደሚደረጉ አስረድተዋል፡፡

ነገር ግን እነዚህ መጠነ ሰፊ እንደሚሆኑ የሚጠበቁት ግኝቶችና ሪፖርቶች በቅርቡ ይቀርባሉ ቢሉም ትክክለኛ ቀኑን አላመለከቱም፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *