በሌሉበት በክሱ የተካተቱ ተከሳሾች ክስ እንዲቋረጥ ትዕዛዝ ተሰጠ

ከድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር ተያይዞ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በተፈጠረው ሁከትና ግጭት ተጠርጥረው ክስ በተመሠረተባቸው እነ አቶ እስክንድር ነጋ ላይ ዓቃቤ ሕግ የቆጠራቸው ምስክሮች፣ ከመጋረጃ ጀርባ ሆነው እንዲመሰክሩ ያቀረበውን ጥያቄ ፍርድ ቤት ውድቅ አደረገው፡፡

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የሕገ መንግሥትና የሽብር አንደኛ ወንጀል ችሎት ማክሰኞ ኅዳር 29 ቀን 2013 ዓ.ም. በሰጠው ውሳኔ እንዳስታወቀው፣ ከሳሽ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አዋጅ ቁጥር 699/2003 አንቀጽ (3) እና (6) ድንጋጌዎችን በመጥቀስ፣ በተከሳሾቹ በአቶ እስክንድር ነጋ፣ አቶ ስንታየሁ ቸኮል፣ ወ/ሮ ቀለብ ሥዩም፣ ወ/ሮ አስካለ ደምሌና አቶ ጌትነት በቀለ ላይ የቆጠራቸው ምስክሮች ከመጋረጃ ጀርባ ሆነው ምስክርነታቸውን እንዲሰጡ ትዕዛዝ እንዲሰጥለት መጠየቁን አስታውሷል፡፡

ዓቃቤ ሕግ የሕግ ድንጋጌውን ጠቅሶ ምስክሮች ከተከሳሾቹ ጋር ስለሚተዋወቁ፣ ማስፈራሪያም ደርሶባቸው እንደነበር በመግለጽ ከመጋረጃ ጀርባ ሆነው እንዲመሰክሩ ትዕዛዝ እንዲሰጥለት ከመከራከር ባለፈ፣ በተጨባጭ ስለሚደርስባቸው ጉዳት (አደጋ) አለማስረዳቱን በመግለጽ፣ ‹‹ምስክሮች ከመጋረጃ ጀርባ ሆነው ይመስክሩልኝ›› የሚለውን ጥያቄ እንዳልተቀበለው ፍርድ ቤቱ አስታውቋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ሰኔ 23 እና 24 ቀን 2012 ዓ.ም. ተገደሉ የተባሉ 14 ሰዎችን በሚመለከት፣ የተከሳሾቹ ተሳትፎ ተለይቶ እንዲቀርብላቸው ያቀረቡትን የመጀመሪያ መቃወሚያ በሚመለከት ዓቃቤ ሕግ በሰጠው ምላሽ፣ የቀረበው ክስ ተከሳሾቹ ወንጀሉን በማደራጀትና በመምራት አንዱ ወገን በሌላው ላይ እንዲነሳሳ ማድረጋቸውንና ለአመፅ በተነሱ ግለሰቦች አማካይነት 14 ሰዎች እንዲገደሉ አድርገዋል በሚል እንጂ፣ በቀጥታ ተከሳሾች ገድለዋል የሚል ክስ አለመቅረቡን በመግለጽ ምላሽ መስጠቱን ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡

በመሆኑም ተከሳሾቹ በቀጥታ ግድያ ፈጽመዋል የሚል ተደራራቢ ክስ ባላቀረበበት ሁኔታ ሰዓት፣ ቦታና የገዳይ ማንነት ተለይቶ እንዳልቀረበ በመግለጽ፣ በተከሳሾች የቀረበው መቃወሚያን እንዳልተቀበለው ፍርድ ቤቱ አሳውቋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ተከሳሾቹ ስልጤ ሠፈር ሄደው አንዱ ብሔር በሌላው ብሔር ላይ እንዲነሳሳ ሲቀሰቅሱ እንደነበር ከመግለጽ ባለፈ፣ የትኛው ብሔር በየትኛው ላይ እንዲነሳሳ እንዳደረጉ አለመግጹን በሚመለከት ዓቃቤ ሕግ የሰጠውን ምላሽም አስታውሷል፡፡

ዓቃቤ ሕግ በምላሹ እንዳብራራው ተከሳሾቹ በኮልፌ ቀራዮ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ስልጤ ሠፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሄደው፣ በሕገወጥ ግንባታ ምክንያት ቤታቸው የፈረሰባቸውን ነዋሪዎች፣ ‹‹ይህንን ያደረገው ታከለ ኡማ ነው፡፡ እናንተን አስነስቶ ከሶማሌ የተፈናቀሉ ኦሮሞዎችን ለማስፈር ነው፤›› በማለት ሌሎች ብሔሮች በኦሮሞ ተወላጆች ላይ እንዲነሱ ያነጣጠረ ቅስቀሳ መሆኑን ጠቅሶ ከማቅረቡ አንፃር፣ ተከሳሾች ያቀረቡት መቃወሚያ ተቀባይነት እንደሌለው ፍርድ ቤቱ አስታውቋል፡፡

ተከሳሾቹ (እነ አቶ እስክንድር ነጋ) የፌስቡክ አካውንቶችን ለማኅበራዊ ሚዲያዎችና ለሌሎች መገናኛ ዘዴዎች፣ እንዲሁም ለአባሎቻቸውና ለደጋፊዎቻቸው በመስጠት ስም ማጥፋታቸውን በሚመለከት ዓቃቤ ሕግ በክሱ የገለጸ ቢሆንም፣ የፌስቡክ ስሜያና ሚዲያዎቹ ግን በግልጽ ተጠቅሰው እንዳልቀረቡ በመግለጽ፣ ያቀረቡትን መቃወሚያ በሚመለከትም ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ሰጥቶበታል፡፡ እንደ ፍርድ ቤቱ ገለጻ፣ ዓቃቤ ሕግ በክሱ በደፈናው ከመግለጽ ባለፈ በሰጠውም ምላሽ፣ ‹‹ራሳቸው ተከሳሾቹ ሐሰተኛ የፌስቡክ አካውንት ተጠቅመው፣ ስም የማጥፋትና ጥላቻ የማስረፅ ሥራ ሠርተዋል፤›› የሚል ክስ አይደለም ማለቱን እንዳልተቀበለው ገልጿል፡፡ በመሆኑም ክሱን አሻሽሎ እንዲያቀርብም ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

የባልደራስ ለእውተኛ ዴሞክራሲ (ባልደራስ) አባልና ተከሳሽ የሆነችው አስካለ ደምሌን በሚመለከት ዓቃቤ ሕግ፣ ከሌሎቹ ተከሳሾች (ከአቶ እስክንድር፣ አቶ ስንታየሁና ወ/ሮ ቀለብ) ተልዕኮ ተቀብላ ለሌሎች ተልዕኮ ስለመስጠቷ የገለጹ ቢሆንም፣ ለማንና እንዴት እንደሰጠች በግልጽ ባለማስቀመጡ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 119(1) ድንጋጌ መሠረት አሻሽሎ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

ዓቃቤ ሕግ በክሱ አካቷቸው የነበሩትና እነ አቶ እስክንድር በተደጋጋሚ ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌላቸውና የማይታወቁ ሰዎች እንደሆኑ ሲገልጿቸው የነበሩት፣ አቶ አሸናፊ አወቀና አቶ ፍትዊ ገብረ መድኅን የተባሉት ተከሳሾችን በሚመለከትም ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

ተከሳሾችን በአድራሻቸው አፈላልጎ እንዲያቀርብ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰጥቶት የነበረው የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ምላሽ መስጠቱን ጠቁሞ፣ ተከሳሾቹ ከመከሰሳቸውና በክሱ ላይ ስማቸው ከመጠቀሱ በስተቀር ምንም ዓይነት አድራሻ እንደሌላቸው ገልጾ፣ የኢሚግሬሽን የዜግነትና ወሳኝ ኩነቶች ኤጀንሲ ከአገር ስለመውጣታቸው እንዲያጣራለት ጠይቆ፣ በተጠቀሰው ስም መረጃ ሊያገኝ አለመቻሉን መግለጹን ፍርድ ቤቱ ተናግሯል፡፡

ዓቃቤ ሕግ አስተያየት ተጠይቆ በሰጠው ምላሽ የተከሳሾቹን አድራሻ መጠቆሙን ገልጾ፣ በጥቆማው መሠረት ይዞ ለማቅረብ ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡

ተከሳሾቹ በጠበቆቻቸው አማካይነት ባቀረቡት መከራከሪያ ፖሊስ በአግባቡ ፈልጎ ተከሳሾቹን ሊያገኛቸው እንዳልቻለ ለፍርድ ቤቱ ማስታወቁን ገልጸው፣ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበው አስተያየት ተከሳሾቹ የተፋጠነ ፍትሕ የማግኘት ሕገ መንግሥታዊ መብታቸቸውን የሚጋፋና (የሚያሳጣ) በመሆኑ፣ ክሳቸው እንዲቋረጥ ወይም የጋዜጣ ጥሪ ተደርጎ ወደ ቀጣይ ሥነ ሥርዓት መግባት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ በመጨረሻም በሰጠው ትዕዛዝ፣ አሸናፊና ፍትዊ የተባሉትን ተከሳሾች በሚመለከት ፖሊስ በአድራሻቸው ፈልጎ ሊያገኛቸው እንዳልቻለ መግለጹን በመጠቆም፣ ዓቃቤ ሕግ ተከሳሾቹ በተገኙበት በማንኛውም ጊዜ ክሱን ማንቀሳቀስ እንደሚችል በመግለጽ ክሳቸው እንዲቋረጥ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

ዓቃቤ ሕግ እንዲያሻሽል ውሳኔ የተሰጠባቸውን ክሶች አሻሽሎ ታኅሳስ 13 ቀን 2013 ዓ.ም. እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

 

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *