አራቱ የዓለም ግዙፍ ኩባንያ ባለቤቶችና ሊቃነ መናብርት በአሜሪካ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ቀርበው ቃላቸውን ይሰጣሉ፣ ይመረመራሉ። ይህ የሚሆነው ነገ ረቡዕ በአሜሪካ ኮንግረስ ውስጥ ነው። ይህ በታሪክ ውስጥ ሆኖ የማያውቅ አጋጣሚ ነው። የፌስቡኩ ማርክ ዙከርበርግ፣ የጎግል አለቃ ሰንዳር ፒቻይ፣ የአፕል ኩባንያ ሊቀመንበር ቲም ኩክ እና የአማዞን ኩባንያ ሊቀመንበርና መሥራች የዓለም ቁጥር አንድ ቢሊየነር ጄፍ ቤዞስ ናቸው፤ ምክር ቤት ቀርበው በጥያቄ የሚፋጠጡት። ከአራቱ ኃያላን መሀል ጄፍ ቤዞስ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ሲቀርብ ይህ የመጀመርያው ይሆናል። ሌሎቹ ከዚህ ቀደም ቢቀርቡም በአንድነት አብረው ለጥያቄ ሲጠሩ ግን ይህ በታሪክ የመጀመሪያው ይሆናል።
“ደንበኞቻችን ለምርቶች ያላቸው ፍቅር ለዚህ አብቅቶናል፤ ትልልቅ ተግባር እንድንፈጽም ያደረገንም ይኸው ነው። 10 ሰዎች እያለን ምን መስራት እንደምንችል አውቅ ነበር፣ አንድ ሺህ ስንሆን ከዚያም 10 ሺህ ስንሆን ምን ማድረግ እንደነበረብን አውቅ ነበር፤ አሁን ከሚሊዮን በላይ ስንሆን ደግሞ ምን ማድረግ እንዳለብን አውቃለሁ”
ምክር ቤቱ ግዙፎቹን ኩባንያዎች ለጥያቄ የጠራቸው ከሚገባው በላይ ግዙፍ መሆናቸውና ይህም ግዝፈታቸው ምናልባት ሊያስከትል የሚችለውን የንግድ ተወዳዳሪነት አለመኖር ጉዳት ለመገምገም ነው። ምርመራው በዚህ ወቅት እንዲጠራ ያደረገው አንዱ ምክንያት በርካታ የዓለም ንግድ እየተብረከረከ ባለበት ሰዓት እነዚህ ኩባንያዎች ግን ከዕለት ዕለት እያበጡ መምጣታቸው የፈጠረው ጥያቄ ነው። አራቱ ግዙፍ የዓለም ኩባንያዎች የሚያንቀሳቅሱት ሀብት ከ5 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ይገመታል። በርካታ የንግድ ተቋማት በእነዚህ ግዙፍ ኩባንያዎች ላይ ቅሬታ አላቸው። ከእነዚህ መካከል የተወሰኑት ከነገ ጀምሮ በሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ይደመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል። ቁጥር አንድ ቢሊየነሩ ጄፍ ቤዞስ ለምክር ቤቱ የሚያቀርበውን ንግግር ከወዲሁ በማኅበራዊ ሚዲያ አጋርቶታል። “ደንበኞቻችን ለምርቶች ያላቸው ፍቅር ለዚህ አብቅቶናል፤ ትልልቅ ተግባር እንድንፈጽም ያደረገንም ይኸው ነው። 10 ሰዎች እያለን ምን መስራት እንደምንችል አውቅ ነበር፣ አንድ ሺህ ስንሆን ከዚያም 10 ሺህ ስንሆን ምን ማድረግ እንደነበረብን አውቅ ነበር፤ አሁን ከሚሊዮን በላይ ስንሆን ደግሞ ምን ማድረግ እንዳለብን አውቃለሁ” ብሏል ቤዞስ ቀደም ብሎ ባሰፈረው የመግቢያ ንግግሩ። “አማዞን መመርመር እንዳለበት ይሰማኛል። ሁሉም ግዙፍ ተቋም ሊመረመር ይገባል። የመንግሥትም ሆነ የግል ተቋማት ሊፈተሹ ይገባል። የእኛ ኃላፊነት እነዚህን መጠይቆች በአስተማማኝ ሁኔታ ማለፍ መቻል ይሆናል” ብሏል ቤዞስ