ባለፈው ሚያዚያ ወር ላይ ፋውስቲን ሩኩንዶ ከማያቀው ስልክ በዋትስአፕ በኩል ጥሪ ደርሶት ነበር። ስልኩን አንስቶ ለመነጋገር ሲሞክር ምንም ድምጽ አልነበረም፤ ከዚያም ዘጋው።
መልሶ ለመደወል ቢሞክርም ማንም ሰው ስልኩን አላነሳም። የሆነው ግን ከእሱ እውቅና ውጪ ስልኩ ተጠልፎ ነበር።
እንግሊዝ ውስጥ ሊድስ በምትባለው ከተማ ውስጥ የሚኖረው ፋውስቲን ጉዳዩ ስላሳሰበው የተደወለለትን ስልክ ቁጥር በይነ መረብ ላይ መባስገባት ከየት እንደሆነ ለማጣራት ሞክሯል። የጥሪ ኮዱ ከስዊድን እንደሆነ ያሳያል።
ሁኔታውን ለመርሳት ቢሞክርም በተደጋጋሚ ይደወልለት ስለነበር ከእራሱ አልፎ ለቤተሰቡም ደህንነት ሰግቶ እንደነበር ያስታውሳል። ነገሮች ከተቀየሩ ብሎ ሌላ ስልክ እስከመግዛት ደርሶም ነበር። ነገር ግን የስልክ ጥሪው ሊቆም አልቻለም።
”በጊዜ ብዛት ከስልኬ አንዳንድ መረጃዎች እየጠፉ እንደሆነ ማስተዋል ጀመርኩ። ለጓደኞቼ ስነግራቸው እነሱም ተመሳሳይ ነገር እንዳጋጠማቸው ነገሩኝ።”
”የስልክ ቀፎ መቀየሬ እንዳልረዳኝ የገባኝ የሚደውሉት ሰዎች አንዴ ስልክ ቁጥሬ ስላላቸው እንደሆነ ሳውቅ ነበር።”
ፋውስቲን በቅርቡ ‘ሲቲዝን ላብ’ ከተባል ካናዳ ቶሮንቶ ውስጥ ከሚገኝ ድርጅት የስልክ ጥሪ ይደርሰዋል። ባለፉት ስድስት ወራት ድርጅቱ ከፌስቡክ ጋር በመተባበር ዋትስአፕን በመጠቀም የሰዎችን መረጃ ስለሚበረብሩ ተቋማት ምርመራ የሚያደርግ ነው።
ድርጅቱ እንዳስታወቀው በምርመራው ከ20 በላይ በሆኑ ሃገራት የሚገኙ ከ100 በላይ የሚሆኑ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እና ጋዜጠኞች በዚሁ ተግባር ኢላማ ተደርገው ነበር።
ፋውስቲን ሩኩንዶ ደግሞ የሩዋንዳ መንግሥትን አጥብቀው ከሚተቹ የመብት ተሟጋቾች መካከል ግንባር ቀደም የሚባል ነው።
የዋትስአፕ ጥሪዎችን በመጠቀም የሰዎችን መረጃ የሚበረብረው ሶፍትዌር እስራኤል ውስጥ በሚገኝ ‘ኤንኤስኦ ግሩፕ’ በሚባል ድርጅት ተዘጋጅቶ ለተለያዩ የዓለም መንግሥታት እንደሚሸጥ መረጃዎች ይጠቁማሉ። በመንግሥታት የሚቀጠሩት የስልክ ጠላፊዎቹ ይህንን ሶፍትዌር በመጠቀም ጋዜጠኞችን፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን፣ አክቲቪስቶችን እና የፖለቲካ ተቀናቃኞቻቸውን የግል መረጃ ይበረበራሉ ተብሏል።
ፋውስቲን የሩዋንዳ መንግሥት ተቺዎችንና ጋዜጠኞችን ወደ እስር ቤት መወርወር ሲጀምር ነበር እ.አ.አ. በ2005 አገሩን ለቆ ወደ እንግሊዝ የተሰደደው። ለሁለት ወራት በመንግሥት ታፍና ተወስዳ በእስር የቆየችው ባለቤቱም እንግሊዝ የገባችው ከሁለት ዓመት በኋላ ነበር።
ዋትስአፕን ገዝቶ በባለቤትነት እያስተዳደረው የሚገኘው ፌስቡክ ‘ኤንኤስኦ ግሩፕ’ የተባለውን ድርጅት በፍርድ ቤት ለመክሰስ እያሰበ ነው። መቀመጫውን እስራኤል ያደረገው ይህ ድርጅት ግን ምንም የሰራሁት ስህተት የለም በማለት ይከራከራል።
ዋትስአፕ ከሌሎች የተንቀሳቃሽ ስልክ መተግበሪያዎች በተሻለ መልኩ ደህንነቱ የተጠበቀ በመሆኑ በ180 አገራት እስከ 1.5 ቢሊዮን የሚደርሱ ሰዎች እንደሚጠቀሙት ይገመታል።
‘ኤንኤስኦ ግሩፕ’ የሚያመርተው ‘ፔጋሰስ’ የተባለው ሶፍትዌር ከየትኛውም ቦታ ማንም ሰው ሳያውቅ ከተጠቃሚዎች ስልክ ጠቃሚ መረጃዎችንና የግል ሰነዶችን ለጥቃት ፈጻሚው ያደርሳል።
ፌስቡክ እንደሚለው የዋትስአፕ ተጠቃሚዎች ከእውቅናቸው ውጪ በተለያዩ ማስታወቂያዎች አማካይነት ሶፍትዌሩ በስልካቸው ውስጥ እንዲቀመጥ ይደረግና የስለላ ሥራው ይቀላጠፋል። በጣም የሚያሳዝነው ደንበኞች ምንም ሳያውቁ የጥቃቱ ሰለባ ሆነውብኛል ብሏል ፌስቡክ።
አክሎም የእስራኤሉ ድርጀት እ.አ.አ ከ2018 እስከ 2019 ባለው ጊዜ ውስጥ በቆጵሮስ፣ በእስራኤል፣ በብራዚል፣ በኢንዶኔዢያ፣ በስዊድን እና በኔዘርላንድስ ስም በተመዘገቡ የስልክ ቁጥሮች የተለያዩ የዋትስአፕ አካውንቶችን ከፍቷል።
”ከባለፈው ሚያዝያ እና ሰኔ ጀምሮ ደግሞ በቀላሉ ተጠቃሚዎች ስልክ ላይ በመደወል ብቻ ጥቃቶችን መፈጸም ችሏል” ከዚህ በተጨማሪም ድርጅቱ ለጋዜጠኛ ጃማል ኻሾግጂ ገዳዮች ስላለበት ቦታ መረጃ የሚሰጥ ሶፍትዌር ሸጦላቸው ነበር የሚል ክስም ቀርቦበታል።
ነገር ግን ‘ኤንኤስኦ ግሩፕ’ ለቢቢሲ በሰጠው ምላሽ እየተባሉ ካሉት ጉዳዮች ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌለውና ክሶቹ ተቀባይነት እንደሌላቸው ገልጿል።
”የዚህ ድርጅት ዋነኛ አላማው መንግሥታዊ የደህንነት ተቋማትና ህግ አስከባሪ ድርጅቶች ሽብርን እንዲዋጉና ከባድ ወንጀሎችን እንዲቆጣጠሩ የሚረዱ ቴክኖሎጂዎችን ማቅረብ ነው” ብሏል።
ምንጭ፦ ቢቢሲ

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *