በእስር ቤት ውስጥ ሰቆቃና ግፍ ለተፈጸመባቸው ካሳ ሊጠየቅ ነው
ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ እስር ቤቶች ውስጥ ለስቃይ እና ለእንግልት የተዳረጉ የቀድሞ እስረኞች መንግሥትን ካሳ እንጠይቃለን አሉ።
የ32 ዓመቱ ሰይፈ ግርማ በሽብር ወንጀል ተከሶ ለሦስት ዓመታትን በእስር አሳልፏል።
በቆይታውም ከፍተኛ የማሰቃየትና የማስፈራራት ተግባራት ይፈፀምበት እንደነበረ የሚናገረው ሰይፈ እግሩ ላይ የሚገኘውን ትልቅ ጠባሳና በግራ ትከሻው ላይ ያለው ጉዳት ማዕከላዊ እስር ቤት ውስጥ በነበረበት ወቅት የደረሰበት እንደሆነ ያስረዳል።
”ጨለማ ቤት ውስጥ ታስሬያለሁ። ምርመራዎች የሚካሄዱት በጉልበት ሲሆን፤ ደድብደባ፣ ውስጥ እግር ገልብጦ መግረፍ እና አጸያፊ የሆኑ ስድቦችን እንሰደብ ነበር። ምርመራዎች የሚካሄዱት ሌሊት ላይ ሲሆን መርማሪዎች መጠጥ ጠጥተው የሚመጡበት ጊዜ አለ” ይላል ሰይፈ።
ይህ የሰይፈ ታሪክ ብቻ ሳይሆን ባለፉት አራት ዓመታት ብቻ በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች በቁጥጥር ስር ውለው ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰት እንደተፈጸመባቸው የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ይናገራሉ።
አብዛኛዎቹ ደግሞ መንግሥትን በመቃወምና ዴሞክራሲያዊ የሆኑ ለውጦች ይምጣ በማለት ሰልፍ የወጡ ናቸው።
ከእነዚህም መካከል ሌላኛው ዮናስ ጋሻው ይገኝበታል።
የሽብር ክስ ተመስርቶበት የነበረው ዮናስ፤ ፍርድ ቤት በቀረበበት ወቅት ሱሪውን በማውለቅ የደረሰበትን ድበደባ ለማሳየት በመሞከሩ ብዙዎች ያስታውሱታል።
በእስር ላይ በነበረበት ወቅት የደረሰበትን ጉዳት ሲያስረዳ ”በደረሰብኝ ድብደባ ምክንያት ዛሬ በክራንች ነው የምሄደው፣ በጀርባዬ መተኛት አልችልም። ሽንት ቤት እንኳ በሰው ድጋፍ ነው የምሄደው” የሚለው ዮናስ ”በቁሜ የሞትኩ ያህል ቢሰማኝም ይህንን ለውጥ በማየቴ ደስተኛ ነኝ” ይላል።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ በወርሃ ሰኔ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፊት ቀርበው በእስረኞች ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይፈጽም እንደነበረ አምነው ይቅርታ መጠየቃቸው ይታወሳል።
ወደ ስልጣን ከመጡ ሰባት ወራትን ያስቆጠሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ፤ እየወሰዷቸው ያሉት የለውጥ እርምጃዎች በበርካቶች ዘንድ ተስፋን ያጫሩ ከመሆኑ በተጨማሪ ከሰብአዊ መብት ጥሰትና ሙስና ጋር በተያያዘ ወደ 70 የሚጠጉ ከፍተኛ የመንግሥት ሃላፊዎችን በጥጥር ስር እንዲውሉ አድርገዋል።
የሰብአዊ መብት ተከራካሪ እና የህግ ባለሙያ የሆኑት አቶ አምሃ መኮንን በመቶዎች ለሚቆጠሩ በሽብር ወንጀል ተከሰው እስር ቤት ለነበሩ ዜጎች ጠበቃ በመሆን አገልግለዋል።
አቶ አምሃ በጠቅላይ ሚኒስትሩ መሪነት እየተከናወኑ ያሉ ጥፋተኛ ናቸው የተባሉ አመራሮችን ለህግ የማቅረቡ ሥራ ገና የመጀመሪያ እርምጃ ነው ይላሉ።
”በማህበረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ቂም ተፈጥሯል። መንግሥት በአፋጣኝ መልስ ሊሰጥባቸው የሚገቡ ቅሬታዎች አሉ። ይህንን ጥያቄ ለመመለስ የመጀመሪያው እርምጃ መሆን ያለበት ደግሞ ግልጽ ውይይት መጀመር ነው። ሃገራዊ እርቅ ያስፈልገናል” የይላሉ የሕግ ባለሙያው።
”በተጨማሪም ተጎጂዎች ካሳ የሚያገኙበትን መንገድን ለማመቻቸት እየሰራን ነው። ጉዳያችን በሃገር ውስጥ ፍርድ ቤቶች መልስ የማያገኝ ከሆነ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤቶች ድረስ ለመሄድም ተዘጋጅተናል። እስከመጨረሻው እንታገላለን። መታገላችንን አናቆምም” በማለት አቶ አምሃ አቋማቸወን ገልፀዋል ቢቢሲ እንደ ዘገበው።

 

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *