የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ – ኢሰመጉ በትግራይ ክልል እና አዋሳኝ አካባቢዎች ያለው የጦርነት እንቅስቃሴን ጨምሮ፣ በተለያዩ የሐገሪቱ አካባቢዎች ያለው የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ከፍተኛ ሥጋት አሳድሮበታል፡፡ ኢሰመጉ በየሳምንቱ ከሚያከናውነው የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ዳሰሳ እንደተረዳው ሰዎች ደህንነታቸው ተጠብቆ በማንኛውም ቦታ በሕይወት የመኖር ሰብዓዊ መብታቸው በልዩ ልዩ ምክንያቶች እየተገፈፈ ነው፡፡ በተጨማሪም፤ ወቅታዊ የሐገሪቱን ሁኔታዎች ተከትሎ
ጋዜጠኞች እና የብዙኃን መገናኛ ባለሙያዎች እስር፣ እንግልት እና ወከባ እየደረሰባቸው መሆኑን፤ ባደረገው ዳሰሳ ለማረጋገጥ ችሏል፡፡
ኮንሶ ዞን እና አዋሳኝ አካባቢዎች፤ በደቡብ ብሔር፡ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት፣ በኮንሶ ዞን፣ በአሌ፣ ቡርጂና ደራሼ ልዩ ወረዳዎች እንዲሁም በቀድሞው ሰገን አካባቢ ሕዝቦች ዞን ጉማይዴ አካባቢ መካከል ባሉ አዋሳኝ አካባቢዎች፣ ለዓመታት ሲንከባለል በመጣ የመዋቅር ማስተካከያ ጥያቄ መነሻነት እና በሌሎችም አስተዳደራዊ እና ፖለቲካዊ ምክንያቶች የተነሳ ተደጋጋሚ ጥቃቶችና ግጭቶች እየተከሰቱ የሰላማዊ ሰዎች ሞት፣ አካል ጉዳት እና መፈናቀል መድረሱ ይታወቃል፡፡ በቀድሞው የሰገን ሕዝቦች ዞን አስተዳደር ውስጥ ተጠቃለው የነበሩት ወረዳዎች ፈርሰው በዞን እና ልዩ ወረዳነት ሲዋቀሩ፤ የወረዳ መዋቅር ጥያቄ በማቅረባችን ምክንያት ለተለያዩ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ተዳርገናል የሚል ተደጋጋሚ አቤቱታዎችም ለኢሰመጉ ሲቀርቡ ቆይተዋል፡፡ ኢሰመጉ በቅርብ ጊዜ እንኳን መስከረም 9 ቀን 2013ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ችግሩ ዘላቂ መፍትሔ እንዲሰጠው መጠየቁ ይታወሳል፡፡
ኢሰመጉ፤ አሁን በድጋሚ የተከሰተውን ችግር የሥፋት መጠን ለማወቅ በቅርበት ክትትል እያደረገ ቢሆንም፤ የአካባቢው ሰላም በዘላቂነት አለመጠበቁ ግን የመስክ ምርመራ ሥራ ለማድረግ ከፍተኛ እንቅፋት ፈጥሮበታል፡፡ ይሁንና፤ እስከአሁን ባደረገው ክትትል ከሰሞኑ በኮንሶ ዞን፣ በአሌ፣ በቡርጂ፣ በደራሼ ልዩ ወረዳዎች እና በጉማይዴ ከተማ ውስጥ በሚገኙ አዋሳኝ ቀበሌዎች ላይ ከህዳር 04 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ዳግም ባገረሸው ግጭት፤ የሰው ህይወት መጥፋቱን፣ በአካል ላይ ቀላልና ከባድ ጉዳት መድረሱን፣ ንብረት መውደሙን እና በርካታ ሰዎች ከመኖሪያ ቀያቸው መፈናቀላቸውን ኢሰመጉ የተቀበላቸውን አቤቱታዎች እና መረጃዎች መሠረት ባደረገ የቅድመ-ምርመራ ሥራ ለማረጋገጥ ችሏል፡፡
ሙሉውን ከታች በተያያዙት ዶክመንቶች ይመልከቱ።
ሁሉም ሰብዓዊ መብቶች ለሁሉም!
selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *