የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዲና ሙፍቲ (አምባሳደር) በትግራይ ክልል ‹‹የሕግ ማስከበር ሥራ›› ሲካሄድ የነበረው ወታደራዊ ዕርምጃ በመገባደዱ፣ የቀረው የፖሊስ ሥራ በመሆኑ፣ በአካባቢው ሰብዓዊ ዕርዳታ ለመስጠት የሚፈልጉ ድርጅቶች አገልግሎቱን ማቅረብ እንዲችሉ መንገዶች እንደተከፈቱላቸው አስታወቁ፡፡

ቃል አቀባዩ ዓርብ ኅዳር 25 ቀን 2013 ዓ.ም. በሰጡት መግጫ እንዳስታወቁት፣ አሁን በሁሉም አካባቢዎች ለመንቀሳቀስ ለሚፈልጉ የሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያደርጉ ድርጅቶች መንገዶችን በመክፈት እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ ተችሏል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) እና የኢትዮጵያ መንግሥት ባደረጉት ስምምነት መሠረት፣ የተመድ የሰብዓዊ ዕርዳታዎች ማስተባሪያ ቢሮ ወደ አካባቢው ተጉዞ የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጎቶችን ለማወቅ የሚያስችሉትን ግምገማ አድርጓል ብለዋል፡፡ ይኼ ቡድን ያየውን በተመለከተም ሪፖርት ያዘጋጀ መሆኑንና ሪፖርቱም በቅርቡ ይፋ ይደረጋል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በትግራይ ክልል ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. መንግሥት በአገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መፈጸሙንና የጦር መሣሪያዎች ዝርፊያም ለማድረግ መሞከሩን በማስታወቅ፣ በትግራይ ክልል ወታደራዊ ዕርምጃ እንዲወሰድ ማዘዙን በወቅቱ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ ጦርነቱ በተካሄደባቸው አራት ሳምንታት ውስጥ የመከላከያ ሠራዊቱ የትግራይ ክልል ዋና ከተማ የሆነችውን መቀሌን የተቆጣጠረ ሲሆን፣ በወንጀል ይፈለጋሉ የተባሉ ከ167 በላይ ግለሰቦችም እየተፈለጉ ናቸው፡፡

ዲና (አምባሳደር) አክለውም፣ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ዓለም ኢትዮጵያ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል እየወሰደች ያለውን የሕግ ማስከበር ዕርምጃ እንዲረዳው ለማድረግ የተደረጉ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ውጤታማ ነበሩ በማለት፣ በርካታ አገሮች ይኼ ዕርምጃ የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ መሆኑን እንደተረዱና የሚያሳስባቸው ጉዳይ የሰብዓዊ ዕርዳታ መዳረስ ብቻ እንደነበረም ተናግረዋል፡፡

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኰንን፣ በቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ እንዲሁም በራሳቸው የተመሩ ልዑካንን ወደ ተለያዩ አገሮች በመሄድ፣ እንዲሁም በድረ ገጽ ግንኙነትና አዲስ አበባ መቀመጫቸውን ያደረጉ አምባሳደሮችን በመጥራትና ማብራሪያ በመስጠት የተከናወነ ነው ሲሉ ዲና (አምባሳደር) ተናግረዋል፡፡

በእነዚህ የውጭ ግንኙነቶች እየተወሰደ ያለው ዕርምጃ በአነስተኛ ጉዳት የተፈጸመ እንደሆነ፣ መንግሥት ዜጎችን ለመመለስ እየሠራ እንደሚገኝ፣ እንዲሁም አዲስ ከተቋቋመው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር ድርድሮችን እያደረገ እንደሆነና ‹‹ከወንጀለኛ ጋር ቡድን›› ድርድር ማድረግ እንደማይቻል ለማሳወቅ ያለሙ እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *