በሰሜን ዕዝ ላይ ከተፈጸመው ጥቃትና ከተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የዋሉ፣ የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ መኮንኖችና የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞች፣ ከኅዳር 23 እስከ 25 ቀን 2013 ዓ.ም. ባሉት ቀናት ፍርድ ቤት ቀረቡ፡፡

በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት የቀረቡት ተጠርጣሪዎች፣ የመከላከያ መገናኛ ሬዲዮና ኔትወርክ ዘርፍ ሠራተኞች የነበሩ ከፍተኛ መኮንኖች፣ የዲጂታል ወያኔ (DW) ሚዲያ ጋዜጠኞችና ቀደም ብሎ የአውራምባ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የነበረውና በአውራምባ ታይምስ ኦንላይን አዘጋጅ፣ እንዲሁም በተለያዩ የንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች ናቸው፡፡

የመከላከያ ሬዲዮ፣ መገናኛና ኔትወርክ ዘርፍ ሠራተኛ እንደነበሩት የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን የገለጻቸው ተጠርጣሪዎች፣ ብርጋዴር ጄኔራል አብርሃ መውጫ፣ ኮሎኔል ገብረ ሕይወት ደስታ፣ ኮሎኔል ዮሐንስ በቀለ፣ ኮሌኔል ዘነበ ታመነና ሻለቃ ገብረ እግዚአብሔር ግርማዬ ናቸው፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ለመከላከያ ሠራዊቱ መጠቀሚያ የተዘረጋን የግንኙነት ኔትወርክ ለሌላ ተልዕኮ በማዘጋጀት፣ በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት እንዲፈጸም ምቹ ሁኔታ መፍጠራቸውን የሚያሳይ ማስረጃ ማግኘቱን፣ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ ምክንያቶች ሁከትና ግጭቶች ሲፈጠሩ፣ ግጭቱን ማስቆም ወይም የሚደርሰውን ጉዳት መከላከል እንዳይቻል የሬዲዮ መገናኛውን የማቋረጥ ሥራ ይሠሩ እንደነበር፣ ለመከላከያ ሠራዊቱ የተገዛን መሣሪያ ለፀረ ሰላም ኃይሎች ሲያስታጥቁ እንደነበር የሚያሳይ ማስረጃ ማግኘቱን፣ ከተፈቀደላቸው ውጪ የጦር መሣሪያ በቤታቸው በተደረገ ብርበራ መገኘቱንና ከወታደራዊ ባህሪ ባፈነገጠ ሁኔታ፣ ከመስከረም 30 በኋላ ‹‹መንግሥት የለም›› በማለት የሠራዊት አባላትን ለብጥብጥ ሲያነሳሱና ሲያስተባብሩ እንደነበር የሚያሳዩ መረጃዎችን ማግኘቱን፣ መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡

በተጠርጣሪዎቹ ላይ የምስክሮችን ቃል መቀበሉንና ሰፊ ሥራ መሠራቱን አስረድቶ፣ በተጠርጣሪዎቹ ምክንያት በአገር መሠረተ ልማቶች ላይ የደረሰን ጉዳት፣ በንብረት ላይ የደረሰን ጉዳት፣ በሰዎች ሕይወትና አካል ላይ የደረሰውን ጉዳት ለማጣራትና ተጨማሪ በርካታ ምርመራዎችን ለመሥራት ተጨማሪ 14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ጠይቋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በበኩላቸው ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡ መከራከሪያ ሐሳብ እንደገለጹት፣ መርማሪ ቡድኑ እንደገለጸው የመከላከያ ሬዴዮ መገናኛ ዘርፍ ሠራተኞች ናቸው፡፡ ነገር ግን በተገለጸው የወንጀል ድርጊት ውስጥ አልተሳተፉም፡፡ በመሆኑም የዋስ መብታቸው ተከብሮላቸው በውጪ ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ፣ የተጠርጣሪዎቹን ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ለመርማሪ ቡድኑ 12 ተጨማሪ የምርመራ ቀናት ፈቅዷል፡፡

ፍርድ ቤት የቀረቡት የዲጂታል ወያኔ (DW) ሚዲያ ጋዜጠኞች ሀብቱ ገብረ እግዚአብሔር፣ አብርሃ ሐጎስ፣ ፀጋዬ ሐጎስና ካሳ ማቴዎስን ጨምሮ አሥር ተጠርጣሪዎች ሲሆኑ፣ መርማሪ ቡድኑ እንዳስረዳው፣ ተጠርጣሪዎቹ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ ሲንቀሳቀሱና ሐሰተኛ ማስረጃ ሲያሠራጩ እንደነበር አስረድቷል፡፡ ከተጠርጣሪዎቹ መካከል አራት ተጠርጣሪዎች የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ስለተገኘባቸው አለመቅረባቸውንም መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ አስታውቆ፣ የምስክሮች ቃል መቀበሉንና የተለያዩ የሰነድ ማስረጃዎችን መሰብሰቡን ገልጿል፡፡ ከሞባይሎቻቸውና ኢሜይላቸው የተለያዩ ማስረጃዎችን ማግኘቱን ጠቁሞ፣ ሌሎች ማስረጃዎችን ለመሰብሰብና ተጨማሪ ምርመራ ለማድረግ 14 ቀናት ጠይቋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት አቤቱታ፣ መርማሪ ቡድኑ የወንጀል ተሳትፎውን በጥቅል ማቅረቡ ተገቢ ባለመሆኑ፣ የእያንዳንዳቸው የወንጀል ተሳትፎ ተለይቶ እንዲቀርብላቸው ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡ በውጪ ሆነው እንዲከታተሉም እንዲፈቀድላቸው አመልክተዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የመርማሪ ቡድኑን የምርመራ ሪፖርትና የተጠርጣሪዎቹን አቤቱታ ከሰማ በኋላ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ በዚህም መርማሪ ቡድኑ በተሰጠው ጊዜ መሥራት የሚገባውን ያህል ሠርቷል ብሎ እንደማያምን በመግለጽ፣ ተጠርጣሪዎቹ የተወሰኑት በኮሮና ቫይረስ መያዛቸውንና የኑሮ ሁኔታ በማገናዘብ እያንዳንዳቸው በአሥር ሺሕ ብር ዋስ ከእስር እንዲፈቱ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር፡፡ ነገር ግን በፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ቅር የተሰኘው የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ይግባኝ ጠይቆ የሥር ፍርድ ቤት ትዕዛዝን ማሳገዱን ሪፖርተር ለማረጋገጥ ችሏል፡፡

በሌላ የምርመራ መዝገብ ፍርድ ቤት የቀረበው ቀደም ብሎ ኅትመት ላይ የነበረው አውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅና የአውራምባ ታይምስ ኦንላይን አዘጋጅ ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ ነው፡፡ ጋዜጠኛ ዳዊትን በሚመለከት የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዳው፣ ተጠርጣሪው የተዛባ መረጃ በማሠራጨት ግጭት በመቀስቀስ ወንጀል ተጠርጥሮ ምርመራ እያደረገበት መሆኑን በማሳወቅ 14 የምርመራ ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡ ፍርድ ቤቱም አንድ ቀን በመቀነስ 13 የምርመራ ቀናትን ፈቅዷል፡፡

ቤቱ ሲበረበር 35 መትረየስ ሽጉጦች፣ አንድ ኮልት ሽጉጥና ሌሎች መሣሪያዎች አስቀምጦ መገኘቱን መርማሪ ቡድኑ የገለጸው አቶ ደፋር ተሰማ የተባለ ተጠርጣሪም ፍርድ ቤት ቀርቧል፡፡

እንደ መርማሪ ቡድኑ ሪፖርት ተጠርጣሪው ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ በማሰብ፣ ከፀረ ሰላም ኃይሎች ተልዕኮ ተቀብሎ፣ በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት በተፈጸመበት ዕለትና በተመሳሳይ ጊዜ፣ በኦሮሚያ አካባቢ ጥቃት ሊፈጽም ሲንቀሳቀስ በቁጥጥር ሥር ውሏል፡፡ የተለያዩ ምርመራዎችን እያደረገ መሆኑን ገልጾ ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

ተጠርጣሪው ለፍርድ ቤት እንደገለጸው፣ የተጠቀሰውን መሣሪያ ሌላ ሰው በእሱ ቤት አስቀምጦት ካልሆነ በስተቀር፣ እሱ እንዳላስቀመጠ ተናግሯል፡፡ የዋስትና መብቱ እንዲከበርለትም ጠይቋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ለመርማሪ ቡድኑ ዘጠኝ ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቅዶ ለታኅሳስ 2 ቀን 2013 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

የሕወሓት ቡድን በሚያደርግላቸው የገንዘብ ድጋፍ በማኅበራዊ ድረ ገጾች ግጭት ቀስቃሽ መረጃዎችን በማሠራጨት የተጠረጠሩ ሦስት ተጠርጣሪዎችንም መርማሪ ቡድኑ ፍርድ ቤት አቅርቦ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ጠይቆባቸዋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹም ቢኒያም ተመስገን፣ ሥዩም ገብረሚካኤልና አሉላ ኢሳያስ የሚባሉ መሆናቸውን ጠቁሞ፣ የምስክሮች ቃል መቀበሉንና ሞባይሎቻቸውንና ኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎችን ለምርመራ መላኩን ለፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡ ለተጨማሪ ምርመራም 14 ቀናት ጠይቋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በጠበቃ ታግዘው አቶ ቢኒያም ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት አቤቱታ እንደተናገሩት፣ መኪና አስመጪ እንጂ ከሕወሓት ቡድን ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌላቸው ገልጸዋል፡፡ ለፖሊስ አጋዥ ሆነው እንደሚሠሩ ጠቁመው፣ ላለፉት 27 ዓመታት ከቡድኑ ጉዳትና መጎሳቆል የደረሰባቸው እንጂ፣ ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌላቸው በድጋሚ በመግለጽ የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ክርክሩን ከሰማ በኋላ ለመርማሪ ቡድኑ ስምንት ተጨማሪ የምርመራ ቀናት ፈቅዷል፡፡

አብዱል ሰላም አብዱልአዚዝ በተባለ ተጠርጣሪ የምርመራ መዝገብ የተካተቱ አራት ተጠርጣሪዎችም ፍርድ ቤት የቀረቡ ሲሆን፣ ከሕወሓት ቡድን ተልዕኮ በመቀበል ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ ሲንቀሳቀሱ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ የተለያዩ የጦር መሣሪያዎቸን ይዘው መገኘታቸውንና በመሣሪያው ላይ ምርመራ እየተደረገ መሆኑንም አክሏል፡፡ የምስክሮችን ቃል መቀበሉን ጠቁሞ፣ ግብረ አበሮችን ለመያዝ ክትትል እያደረገ መሆኑን ገልጾ ተጨማሪ የምርመራ ቀናት ጠይቋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹም መርማሪ ፖሊስ ከገለጸው የወንጀል ድርጊት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌላቸው በመግለጽ፣ የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸውና በውጪ ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ጠይቀዋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ በድጋሚ ለፍርድ ቤቱ ባቀረበው መከራከሪያ፣ ተጠርጣሪዎቹ በተደጋጋሚ መቀሌ በመመላለስ የሽብር ተግባር ለመፈጸም ሥልጠና መውሰዳቸውንና የአገሪቱን መሠረተ ልማት ለማውደም ሲንቀሳቀሱ መያዛቸውን በማስረዳት፣ የጠየቀው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድት ጠይቋል፡፡

ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ ፖሊስ ከጠየቀው 14 ቀናት ውስጥ ዘጠኝ ቀናት ፈቅዷል፡፡

ተስፋዬ ተረፈ፣ አበበ መረሳና ሃምሳ አለቃ ሕይወት በርሄ የተባሉ ተጠርጣሪዎችም ፍርድ ቤት የቀረቡ ሲሆን፣ ፖሊስ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ ከኦነግ ሸኔና ከሕወሓት ቡድን ተልዕኮ ተቀብለው ሲንቀሳቀሱ መያዛቸውን ለፍርድ ቤቱ በማስረዳት 14 ቀናት የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት ጠይቀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም ሀፍቱ ካሰው፣ ተስፋዬ ተረፈና አበበ መርሳ በጠበቃ እንዲወከሉ በመጠየቃቸው የእነሱን አቆይቶ ሃምሳ አለቃ ሕይወት ላይ መርማሪ ቡድኑ የጠየቀውን 14 ቀናት ፈቅዷል፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *