የአውሮፓ ኅብረት ለኢትዮጵያ የሚሰጠው የበጀት ድጋፍ፣ ፖለቲካዊ ተሰሚነት እንደሚያስገኝለት በማመን፣ ይኼንን ተሰሚነት በትግራይ ክልል ከተካሄው ጦርነት ጋር በተገናኘ ኢትዮጵያ ላይ ተፅዕኖ ለማድረግ ሊያውለው እንደሚችል ተጠቆመ፡፡

የልማት መረጃዎችንና ጥናቶችን በተለያዩ ጊዜያት የሚያወጣው ዴቬክስ ድረ ገጽ በአውሮፓ ኅብረት የልማት መምርያ ውስጥ የአፍሪካ ቀንድና የምሥራቅ አፍሪካ ኃላፊ ሃንስ ስቶስቦልን፣ ‹‹ከኢትዮጵያ ጋር ያለን የድጋፍ ግንኙነት እጅግ ሰፊ ነው፡፡ ይህ በግልጽ ባይጠቀስም እንኳን ለፖለቲካዊ ዓላማዎች ማሳኪያነት እንጠቀምበታለን፤›› ብለዋል ሲል አስነብቧል፡፡

እንደ ኃላፊው ገላጻ ከሆነ፣ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. ከ2014 እስከ 2020 ድረስ ባሉት ስድስት ዓመታት 966 ሚሊዮን ዶላር ዩሮ ተመድቦላታል፡፡ ከዚህ ውጭ የሆነ 400 ሚሊዮን ዩሮ ከአውሮፓ ኅብረት ትረስት ፈንድ የምታገኝ መሆኑን፣ ከዚህ ውስጥ በርከት ያለው ገንዘብ ለመንግሥት የበጀት ድጋፍ ለማድረግ ቀጥታ ወደ መንግሥት ግምጃ ቤት እንደሚገባም ተጠቁሟል፡፡

ምንም እንኳን ኃላፊው ይኼንን ቢሉም፣ በአውሮፓ ኅብረት ደረጃ እ.ኤ.አ. 2020 ከመጠናቀቁ በፊት ይጠየቃል ተብሎ የሚጠበቀውን የ90 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ ይሰጥ አይሰጥ የሚለው ከውሳኔ እንዳልተደረሰበት ግን አልሸሸጉም፡፡

ይሁንና ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ድጋፍ ከሚያደርገው የዓለም ባንክና የአውሮፓ ኅብረት አባል አገሮች ጋር የኅብረቱ ተቋማት ለኢትዮጵያ የሚደረገው ድጋፍ ለተረጂዎች የሚደርስ በመሆኑ፣ እነሱን ሳይጎዳ ይኼንን አቅማቸውን እንዴት በመንግሥት ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ እየተወያዩ እንደሆነ አክለዋል፡፡

እንደ ዴቬክስ ድረገጽ ተፅዕኖ ለማሳደር ያስችላል የተባለው አቅም መኖሩን የሚጠራጠሩ ቢኖሩም፣ ለዚህ ዓላማ መጠቀሚያ ማድረጉ አግባብነት አለው ብለው የማያምኑ አካላት አሉ ሲል በኢትዮጵያ በሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ላይ የተሰማሩ የግብረ ሰናይ ባለሙያን ጠቅሶ በኃላፊው ንግግር ላይ ጥያቄ ያነሳል፡፡ የዕርዳታ አድራጊዎች በፖለቲካው ውስጥ እምብዛም ተፅዕኖ የላቸውም የሚሉት እኚህ ባለሙያ፣ ኢትዮጵያ ቀጣናዊ ተሰሚነት ስላላትና ሌሎች እንደ ቻይናና የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ዓይነት ወዳጆች ስላሏት እንዲህ ያለ ተፅዕኖ ላይሠራ እንደሚችልም ያስገነዝባሉ፡፡

ከተለያዩ ወዳጅ የዓለም አገሮች የድጋፍና የሥጋት መልዕክቶች እንደነበሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሰኞ ኅዳር 21 ቀን 2013 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት የወቅታዊ ጉዳዮች ማብራሪያ ያስታወቁ ሲሆን፣ ትክክለኛ የወዳጅነት ሥጋት የገባቸው አገሮች ቢኖሩም በዚህ ውስጥ ተፅዕኖዎችን ለማሳደር የሚያስቡ እንደነበሩም አልሸሸጉም፡፡ ለዚህም በሰጡት ምላሽ ምንም እኳን ኢትዮጵያ ደሃ ብትሆንም፣ በሉዓላዊነቷ እንደማትደራደር በማስረገጥ፣ ከኢትዮጵያ ጋር ወዳጅ ሆኖ መቀጠል የሚፈልግ አገር ኢትዮጵያንም ማወቅ አለበት ብለዋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ለገንዘብ ሲባል ሉዓላዊ መብቷን አሳልፋ የምትሰጥ አገር አይደለችምና ይኼንን ዕወቁ፤›› ብለዋል፡፡

ካሁን ቀደም፣ በተመሳሳይ ለጋሽ አገሮች ለኢትዮጵያ የሚያደርጉትን የገንዘብ ድጋፍ በመጠቀም፣ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟ ላይ ለመደራደር የተደረጉ ሙከራዎች እንዳሉ አይዘነጋም፡፡ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ የሚያደርጉትን ድርድር ተከትሎ አሜሪካና የዓለም ባንክ በታዛቢነት ገብተው አሜሪካ ያዘጋጀችውን የስምምነት ሰነድ ኢትዮጵያ አልቀበልም በማለቷ ሳቢያ፣ ለኢትዮጵያ የሚሰጠው የገንዘብ ድጋፍ እንዲቆም ተደርጎ ነበር፡፡ ይኼንን በቅርቡ በምርጫ የተሸነፉት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢትዮጵያ ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር ሊጠቀሙ የሚችሉት አማራጭ እንደሆነ መናገራቸው አይዘነጋም፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *