መንግሥት በትግራይ ክልል ሲያከናውን የነበረውን የሕግ ማስከበር ዘመቻ፣ የመጨረሻ መዳረሻ የነበረችውን የመቀሌ ከተማ ስለተቆጣጠረ የተፈናቀሉ ዜጎች በአስቸኳይ ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ እንዲያደርግ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጠየቀ፡፡
ቀደም ሲል በተለይ በሲቪል ሰዎች ላይ ማንኛውም ጉዳት እንዳይደርስ ጥንቃቄ እንዲደረግ አጽንኦት የሚሰጡ ምክረ ሐሳቦችና ጥሪዎችን ማቅረቡን በማስታወስ፣ በቀጣይ የሚደረጉ የመልሶ ግንባታ ተግባራት በፌዴራል መንግሥቱ ሰብዓዊ መብቶችን የማክበርና የመጠበቅ ግዴታ የሚመራ እንዲሆን ኮሚሽኑ አሳስቧል፡፡
በግጭቱ ምክንያት የተጠፋፉ ቤተሰቦች እንዲገናኙና ሰብዓዊ ዕርዳታ ተደራሽ እንዲሆን፣ የተቋረጡ የቴሌኮሙዩኒኬሽን፣ የውኃና የኤሌክትሪክ ኃይልን ጨምሮ መሰል መሠረታዊ አገልግሎቶች ወደ ነበሩበት እንዲመለሱም ኮሚሽኑ ጠይቋል፡፡
የተፈናቀሉና የተሰደዱ ሰዎች ወደ መደበኛ መኖሪያቸው እንዲመለሱና የተጠፋፉ ቤተሰቦች እንዲገናኙ የሚያስችለው፣ የሎጂስቲክስና የሰብዓዊ ዕርዳታ መሠረተ ልማት እንዲደራጅም አሳስቧል፡፡
ኮሚሽኑ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥና ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋም የሰብዓዊ መብቶች ጥሰትና ያስከተለውን ሰብዓዊ ቀውስ የሚመመረምር ገለልተኛና ግልጽ የሆነ አሠራር በመተግበር፣ ተዓማኒና አካታች የሆኑ የዕርቅና የፍትሕ ሒደቶች በጊዜ እንዲደራጁ ጠይቁል፡፡
በትግራይ ተወላጆች ላይ ብሔርን መሠረት ያደረገ መድልኦና መገለል ስለመድረሱ፣ ቅሬታዎች በከፍተኛ ደረጃ እየቀረቡለት እንደሆነና ይህም እንዳሳሰበው አስታውቋል፡፡ ከዚህ ባለፈ በተወሰኑ ሰዎች ላይ ከሥራ አስገዳጅ የዕረፍት ጊዜ በማስወሰድና ለሥራ፣ ለሕክምናና ለትምህርት የሚደረጉ ጉዞዎችን በመከልከል የሚገለጽ መሆኑን መረዳቱን ገልጿል፡፡
ምንም እንኳ ይህንን የሚፈቅድ የመንግሥት ፖሊሲም ሆነ የሕግ ማዕቀፍ አለመኖሩ የሚታወቅ ቢሆንም፣ የተወሰኑ ተጠርጣሪዎችን ለመከታተል በተነደፈ የፀጥታ ጥበቃ ዕርምጃ ተለጥጦ አላስፈላጊ ማኅበረሰባዊ ተፅዕኖ እየፈጠረ እንደሆነ፣ ኮሚሽኑ ጉዳዩን ከሚመለከታቸው ኃላፊዎች ጋር ባደረገው ውይይት መልካም ምላሽ ማግኘቱን ገልጿል፡፡
ኮሚሽኑ በመግለጫው መንግሥታዊ አካላት በሙሉና በተለይም የኤርፖርት ደኅንነት ሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች፣ ያለ በቂ ሕጋዊ ምክንያት ማናቸውንም ተጓዦችን ከጉዞ እንዳይከለክሉ አሳስቧል፡፡
የግጭቱ ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆኑ ተጎጂዎችን መልሶ የማቋቋም አገር አቀፍ ኃላፊነት መጠነ ሰፊ ሥራ ከመሆኑም ባሻገር፣ ተገቢውን ቅንጅትና የገንዘብ አቅም የሚጠይቅ እንደሆነ በመግለጽ በተለያዩ ማኅበረሰቦች መካከል የነበረውን መተማመን መልሶ ለማምጣትና ዘላቂ ሰላም ማስፈን አማራጭ እንደሌለው ጠቁሟል፡፡