በደቡብ ክልል በኮንሶ ዞን ሰገን ዙሪያ ወረዳ፣ ካራት ዙሪያ ወረዳና ኮልሜ ክላስተር አካባቢዎች በተከሰተ ግጭት 102 ሰዎች ሲሞቱ፣ 83,131 ዜጎች ከቀዬአቸው መፈናቀላቸውን፣ የኮንሶ ዞን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ፡፡

የግጭቱ ምክንያት፣ ቀደም ብሎ ‹‹ሰገን አካባቢ ሕዝቦች ዞን›› ተብሎ በአዋጅ ከፀደቀ በኋላ፣ እንደገና በአዋጅ ፈርሶ ልዩ ወረዳ ይሁን በሚሉ ጥያቄ አቅራቢዎች መካከል በተነሳ ግጭት መሆኑን የቢሮ ኃላፊው አቶ ሠራዊት ዲባባ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

አቶ ሠራዊት ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በዋነኝነት ከሰገን ዞን መፍረስ ጋር ተያይዞ፣ የልዩ ወረዳ ጥያቄ አቀንቃኝ ኃይልና መቀመጫውን ደራሼ ልዩ ወረዳ ያደረገው ፀረ ሰላም ኃይል አማካይነት ግጭት መቀስቀሱን ገልጸዋል፡፡

በዚህም በሦስቱ የኮንሶ አቅጣጫዎች ከ2,436 ቤቶች በላይ የተቃጠሉ ሲሆን፣ 82 ሰዎች ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ተናግረዋል፡፡ በደራሼ ወረዳ የኩስሜ ብሔረሰብ በሚኖርበት መንደር አንድና መንደር ሁለት በሚባሉት አካባቢዎች በተከሰተው ግጭትም ከ8,000 በላይ ዜጎች ተፈናቅለው ካራት ዙሪያ በአይዴ ቀበሌ ተጠልለው እንደሚገኙ አቶ ሠራዊት ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የደራሼ ወረዳ አስተዳደር አቶ አመኑ ቦጋለ በበኩላቸው፣ ከኮንሶ ዞን ሰገን ዙሪያ ወረዳ አካባቢ ወደ ደራሼ የተፈናቀሉ እንደሚገኙ ገልጸው፣ ከደራሼ ወረዳ ወደ ኮንሶ ዞን የተፈናቀሉ ዜጎች እንዳሉ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ በአጠቃላይ ከኮንሶ ዞን የተፈናቀሉትንና በኩስሜ ብሔረሰብ አካባቢ የተነሳውን ግጭት ጨምሮ 52,000 ነዋሪዎች የተፈናቀሉ ሲሆኑ፣ በዞንና ከክልሉ መንግሥት ጋር በመሆን ወደ አካባቢያቸው ለመመለስ እየተሠራ መሆኑን የወረዳው አስተዳዳሪ ተናግረዋል፡፡

ቤትና ንብረታቸውን ላጡ ዜጎች ጊዜያዊ መጠለያ የተዘጋጀ ሲሆን፣ ዘላቂ ዕርዳታ በፌዴራልና በክልል መንግሥት እየተደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የተነሳው ግጭት መንስዔ ባለፉት ሁለት ዓመታት የነበረው መዋቅርና መልካም አስተዳደር ጥያቄ ውሎ አድሮ የግጭት መንስዔ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የደቡብ ክልል የፀጥታ ቢሮ ኃላፊው አቶ ዓለማየሁ ባውዲ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በኮንሶ ዞንና በቀጣናው በተወሰኑ ቡድኖች ምክምያት ግጭት መፈጠሩን ገልጸው፣ የግጭቱ ማዕከል የሆነው በኮንሶና አሌ ልዩ ወረዳ ነው፡፡

በአስተዳደር ወሰን ጥያቄ ምክንያት ከዚህ ቀደምም ግጭት የተነሳ ሲሆን፣ በተወሰኑ ፀብ ጫሪ ቡድኖች ምክንያት መቀስቀሱን ጠቁመዋል፡፡ በተመሳሳይ ደራሼ፣ ኮንሶ፣ ቡርጂና አማሮ ልዩ ወረዳ የሚዋሰኑበት አካባቢ የከተማ አስተዳደር ጥያቄና ‹‹ልዩ ወረዳ እንሁን›› ጥያቄ ያለ ሲሆን፣ ያላግባብ ከጥያቄው ይዘት ውጪ የግል ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ያነሱት ግጭት መሆኑን አቶ ዓለማየሁ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በዚህ ሁኔታ በአስተዳደር ወሰንና በመዋቅር ምክንያት ለተነሱ ጥያቄዎች መንግሥት በአግባቡ መልስ መስጠቱን የጠቆሙት የፀጥታ ቢሮ ኃለፊው፣ የአሁኑ ግጭት የተከሰተበት ምክንያት በክልሉ የተለያዩ አለመረጋጋቶች በመኖራቸው የነበረው መከላከያ ሠራዊት ለሕግ ማስከበር መውጣቱን ተከትሎ መሆኑ ገልጸዋል፡፡

መነሻው የሕዝብ ጥያቄ ቢሆንም የኦነግ ሸኔና ሕወሓት ቡድን መንግሥትን አጣብቂኝ ውስጥ ለማስገባት ሕዝቡን ለፀብ በመገፋፋታቸው ነው ብለዋል፡፡

አቶ ዓለማየሁ፣ የክልሉ መንግሥት በፍጥነት ጣልቃ ገብቶ የፀጥታ መዋቅሩንና ኅብረተሰቡን በማሳተፍ የጥፋት ሥራ እንዲቆም መደረጉን ተናግረዋል፡፡

የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር እየተለየ ሲሆን ግጭት በተነሳበት ቀጣናዎች የተፈናቀሉ ዜጎች ብዛት 64,000 መሆኑን የፀጥታ ቢሮው ኃላፊ አስረድተዋል፡፡ በሥጋት የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ አካባቢያቸው የመመለስ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡ በግጭት ቀጣናው የሟቾች ቁጥር 50 ሲሆኑ፣ 40 የሚሆኑ ደግሞ ከባድ ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱን የፀጥታ ቢሮ ኃላፊው ቢገልጹም፣ የኮንሶ ዞን ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ ግን የሟቾች ቁጥር ከ100 በላይ መሆናቸውንና የአካል ጉዳት የተደረሰባቸው ከ80 በላይ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡

የደራሼ የፀጥታ ቢሮ ኃላፊን ጨምሮ 15 የሚደርሱ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሲሆን በዘላቂነት አጥፊ ሥራ ላይ የተሰማሩ በቁጥጥር ሥር በማዋል የሕግ ማስከበሩ ሥራ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *