በኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል ሰላም፣ ፍትሕ፣ ብሔራዊ መግባባት፣ አንድነትና ዕርቅ ማስፈንን ዓላማ አድርጎ ጥር 28 ቀን 2011 ዓ.ም. በአዋጅ ቁጥር 1102/2011 የተቋቋመው ‹‹ዕርቀ ሰላም ኮሚሽን›› የአገርን ገጽታ የሚያጎድፍ ግድያ፣ ጥቃት፣ መፈናቀልና ስደት እንዲቆም ጠየቀ፡፡

ኮሚሽኑ ሰሞኑን ባደረገው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ ባወጣው መግለጫ እንደገለጸው፣ ድንበር በመጠበቅ ላይ በነበረው የሰሜን ዕዝ መከላከያ ሠራዊት ላይ የደረሰው ጥቃት የማይገባና ሊፈጸም አይደለም መታሰብ የለበትም፡፡ አገርን ከጠላት የሚታደግ አለኝታ የመከላከያ ሠራዊት ላይ የተፈጸመው ጥቃትና የደረሰው የሕይወት ማጥፋት ድርጊት፣ እንዳሳዘነው ኮሚሽኑ በመግለጫው አስታውቋል፡፡

በማይካድራ በንፁኃን ዜጎች ላይ በተፈጸመው ጥቃት ውድ ሕይወታቸውን ባጡና የአካል ጉዳት በደረሰባቸው ወገኖች ላይ አስፈላጊው ማጣራት ተደርጎ፣ አጥፊው በሕግ እንዲጠየቅ ኮሚሽኑ ለመንግሥት ጥሪውን አስተላልፏል፡፡

መንግሥት ከወቅቱ ሁኔታ ጋር በተያያዘ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን፣ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚፈጸመው ብሔርንና ሃይማኖትን፣ ማንነቶችንና መሰል ጉዳዮችን መሠረት ያደረገ ጥቃት፣ ነገ ዛሬ ሳይባል እንዲቆም ማድረግ እንዳለበትም ኮሚሽኑ አሳስቧል፡፡ ከኢትዮጵያ ባህል ፍፁም ያፈነገጠ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃም የተወገዘና የኢትዮጵያን ስምና ገጽታ የሚያጎድፍ ግድያ፣ ጥቃትም ሆነ ስደትና መፈናቀል እንዲቆም ባወጣው መግለጫ ጠይቋል፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *