የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም. በማይካድራ ከተማ ነዋሪዎች ላይ የተፈጸመውን ጭፍጨፋ በማውገዝ፣ በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል መሆኑን አስታወቀ፡፡ በተለይ የአማራ ብሔር ተወላጆች በብዛት በሚኖሩበት ልዩ ስሙ ‹‹ግንብ ሠፈር›› በሚባለው መንደር እስከ ወልቃይቴ ቦሌ ሠፈር ድረስ የሚገኙ ዜጎች፣ ግፍና ጭካኔ በተሞላበት መንገድ መጨፍጨፋቸውን ገልጿል፡፡ ይህ ድርጊት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰትና በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸመ የጦር ወንጀል ነው ሲል አውግዟል፡፡

ከኅዳር 5 እስከ 9 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ በማይካድራ ከተማ፣ በአብርሀጅራ፣ በሳንጃ፣ በዳንሻ፣ በሁመራና በጎንደር ከተሞች በጉዳዩ ላይ አደረግኩት ያለውን ምርመራና የደረሰበትን የመጀመርያ ደረጃ ሪፖርት ማክሰኞ ኅዳር 15 ቀን 2013 ዓ.ም. ይፋ  አድርጓል፡፡

ኢሰመኮ በጥቃቱ ሕይወታቸው ያለፈ፣ የአካልና የንብረት ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ብዛት ገና በትክክል ተጣርቶ ያልተረጋገጠ ቢሆንም፣ ከጥቃቱ በኋላ ከተቋቋመው የቀብር ኮሚቴ፣ ከምስክሮችና ከሌሎች የአካባቢው ምንጮች ሰበሰብኩት ባለው መረጃ መሠረት በትንሹ 600 ሰዎች እንደተገደሉና ትክክለኛው ቁጥር ሊያሻቅብ እንደሚችል ጠቁሟል፡፡

ጥቃቱ ጥቅምት 25 ቀን 2013 ዓ.ም. በትግራይ ክልላዊ መንግሥትና በፌዴራል መንግሥት መካከል ውጊያ መጀመሩን ተከትሎ የትግራይ ተወላጅ ባልሆኑ ሰዎች ላይ የተፈጸመ ነው ሲል ሪፖርቱ አስታውቋል፡፡

ማይካድራ በትግራይ ክልል፣ በምዕራባዊ ዞን፣ በሀፍታ ሁመራ ወረዳ የምትገኝ የከተማ አስተዳደር እንደሆነች የጠቆመው የኮሚሽኑ ሪፖርት፣ በከተማዋ ከ45 እስከ 50 ሺሕ የሚገመቱና በወልቃይት የተወለዱ ለረዥም ጊዜ የኖሩ የአማራ ብሔር ተወላጆች እንደሚኖሩባት አመልክቷል፡፡

የጥቃቱ ሰለባ የሆኑት ዜጎች በተለይም በሰፋፊ የሰሊጥና የማሽላ እርሻዎች   የጉልበት ሥራ ለመሥራት በአብዛኛው ከአማራ ክልል፣ የተወሰኑት ደግሞ ከሌሎች አካባቢዎች የመጡ እንደሆነ ኮሚሽኑ በሪፖርቱ ገልጿል፡፡

ጥቃቱ ከመከሰቱ ጥቂት ቀናት አስቀድሞ፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ወደ ማይካድራ ለመግባት ሲቃረብ፣ ሁሉም ከማይካድራ የሚያስወጡ ኬላዎችን በአካባቢው አስተዳደር፣ በሚሊሻና በፖሊስ ኃይሎች በመዘጋጀታቸው፣ በመከላከያ ሠራዊት ተሸንፎ እየሸሸ የነበረው የትግራይ ሚሊሻና ልዩ ኃይል ያጠቃናል በሚል ሥጋት እነዚህ ወገኖች ሸሽተው ወደ በረሃው የእርሻ ቦታ ‹‹በረኸት›› ወደምትባል የሱዳን አዋሳኝ ከተማ ለመውጣት እንዳልቻሉ ሪፖርቱ አሳይቷል፡፡

በከተማው አራት ዋና ዋና መውጫዎች በተቋቋሙ ኬላዎች ላይ በተሰማሩ ሚሊሻና ‹‹ሳምሪ›› የሚባል የትግራይ ተወላጆች መደበኛ ያልሆነ የወጣቶች ቡድን ተመልሰው ወደ ቤታቸው እንዲገቡ መገደዳቸውን፣ የትግራይ ተወላጅ የሆኑና ያልሆኑ ሰዎችን ለመለየት መታወቂያ ካርድ እየተመለከቱ ማጣራት እንዳደረጉ በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡

የዓይን ምስክሮችን ዋቢ አድርጎ በወጣው ሪፖርት ዓብይ ፀጋዬ የተባለን የአማራ ብሔር ተወላጅ ከቤቱ ፊት ለፊት በጥይት በመግደል፣ ቤቱንና አስከሬኑን በእሳት ማቃጠል ጥቃቱ እንደ ጀመረ ተገልጿል፡፡

ግለሰቡ በአንድ ወቅት በወታደርነትና በሚሊሻነት ሠርቶ ከአገልግሎት የተሰናበተ እንደሆነ፣ በቅርቡ በተፈጠረው የጦርነት ሥጋት በአካባቢው መስተዳደር ወደ ውትድርና አገልግሎት እንዲመለስ ተጠይቆ ፈቃደኛ አለመሆኑን ገልጾ ስለነበር በዚህ የተነሳ የጥቃት ዒላማ ሳይሆን እንዳልቀረ የአካባቢው ነዋሪዎች ማስረዳታቸው በሪፖርቱ ተካቷል፡፡

ይህንን የመጀመርያ ክሰተት ተከትሎ ‹‹ሳምሪ›› የሚባለው የወጣቶች ቡድን በአካባቢው ፖሊስና ሚሊሻ እየተደገፈ በየጎዳናውና ከቤት ቤት በመዘዋወር አማሮችንና ወልቃይቴዎች ያሏቸውን ሲቪል ሰዎች በከፍተኛ ግፍና ጭካኔ በዱላ በመደብደብ፣ በጩቤ በመውጋት፣ በገጀራና በፈራድ (ወይም ፋስ መጥረቢያ) በመምታትና በገመድ በማነቅ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ገድለዋል፣ ንብረት ዘርፈዋል፣ አውድመዋል ይላል የኮሚሽኑ ሪፖርት፡፡

‹‹ሳምሪ›› የሚባለው የወጣቶች ስብስብ በአንድ ቡድን በአማካይ ከ20 እስከ 30  ወጣቶች በመሆን፣ በየቡድኑ በግምት ከሦስት እስከ አራት በሚሆኑ መሣሪያ የታጠቁ ፖሊስና ሚሊሻዎች እየታጀቡ ጭፍጨፋውን ሲፈጽሙ፣ በየመንገዱ መታጠፊያዎች አድፍጠው ይጠባበቁ የነበሩት ሚሊሻዎችና ፖሊሶች ደግሞ ከጥቃቱ ለመሸሽ የሚሞክርን ሰው በተኩስ በመመለስ የአጥቂውን ቡድን ጭፍጨፋ በቀጥታ ይፈጽሙና ያስፈጽሙ እንደነበር ተገልጿል፡፡

የኢሰመኮ ሪፖርት  ከሞቱት ሰዎች ብዛትና በአቅም ማነስ ምክንያት የቀብሩ ሥነ ሥርዓት ሦስት ቀናት መውሰዱን፣ ሰዎች በጅምላ መቀበራቸውን፣ እንዲሁም በምርመራ ቡድኑ ጉብኝት ወቅት ገና ያልተቀበሩ በመንገድ የወደቁ አስከሬኖችም እንዳሉም ያመለክታል፡፡

በማይካድራ ከተማ የተፈጸመው ጥቃት ተራ ወንጀል ሳይሆን የታቀደና በጥንቃቄ ተቀነባብሮ የተፈጸመ እጅግ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት መሆኑን፣ አጥፊዎቹ ሆነ ብለው፣ አቅደውና ተዘጋጅተው በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በመግደላቸው የተጎዱትን ማቋቋምና አጥፊዎች ለሕግ እንዲቀርቡ የኮሚሽኑ ሪፖርት አሳስቧል፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *