በፌዴራል መንግሥትና በትግራይ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ያለው የጦርነት እንቅስቃሴ የሰላማዊ ሰዎችን ደኅንነትና ሰብዓዊ መብቶቻቸውን ከፍተኛ አደጋ ላይ የጣለ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ በጦርነቱ በቀጥታ ተሳታፊ ያልሆኑና ያልታጠቁ ንፁኃን ደኅንነት ጉዳይ ሥጋት እንዳሳደረበት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) አስታወቀ፡፡
በትግራይ ክልል መንግሥትና በፌዴራል መንግሥት መካከል ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. የተቀሰቀሰውን ጦርነት አስመልክቶ በማግሥቱ ጥቅምት 25 ቀን 2013 ዓ.ም. አስቸኳይ መግለጫ ማውጣቱን ያስታወሰው ኢሰመጉ፣ በግጭቶቹ አካባቢዎች ያለውን እንቅስቃሴ የሰላማዊ ሕዝብን ሕይወትና አካላዊ ደኅንነት አደጋ ላይ የማይጥል ሊሆን እንደሚገባ በድጋሚ አሳስቧል፡፡
ሰሞኑን በትግራይ ክልል ማይካድራ ከተማ ውስጥ በጦርነቱ ውስጥ ምንም ዓይነት ተሳትፎ ያልነበራቸው፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች በስለታማ መሣሪያዎች ተወግተው መገደላቸውን ባደረገው ቅድመ ምርመራ ማረጋጡን ኢሰመጉ ገልጿል፡፡ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈጸም ጭፍጨፋ በማንም ይሁን በምንም ምክንያት ሊኖረው እንደማይገባ አክሏል፡፡
የደረሰውን ጉዳት በቻለው መጠን ለማጣራት እየሠራ እንደሚገኝ ጠቁሞ፣ ተመሳሳይ ክስተት እንዳይፈጠር ሁሉም ወገን በከፍተኛ ትኩረት መከታተል እንዳለበትና አጥፊዎች ለሕግ እንዲቀርቡ መሠራት እንዳለበት አሳስቧል፡፡ በሌሎች አካባቢዎች የአላማጣ ከተማ ነዋሪዎችና የሕግ እስረኞች በአጠቃላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች፣ የትና በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ ስለማይታወቅ ደኅንነታቸው በከፍተኛ ሁኔታ እንዳሳሰበው አስታውቋል፡፡
በግጭቱ በሁሉም ወገኖች ጥቅም ላይ እየዋሉ ያሉት የአየር ጥቃት ለመፈጸም የሚያስችሉ መሣሪያዎች በአብዛኛው የሰው ልጆች ብቻ ያላቸውን ሁኔታዎችን የማመዛዘን አዕምሯዊ ብቃት የሚያንሳቸው በመሆኑ፣ ያልታጠቁ ሰላማዊ ሰዎችንና የሲቪል ንብረቶችን የጥቃቱ ዒላማና ሰለባ እንዳያደርጋቸው ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚሹ መሆናቸውንም አሳስቧል፡፡
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ባወጣው መግለጫ የኦሮሚያ ክልል ፍርድ ቤቶች የዋስትና መብት መረጋገጥ ላይ እየሰጡ ላሉት ውሳኔ ዕውቅና መስጠቱን አስታውቋል፡፡ የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበታ ልዩ ችሎት የዋስትና መብት ተፈቅዶላቸው ለአራት ወራት ያህል ሳይፈቱ በእስር የቆዩት አቶ ለሚ ቤኛና አቶ ዳዊት አብደታ ጉዳይን መርምሮ የዋስትና መብታቸውን ማረጋገጡ ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑን ገልጿል፡፡
ሰሞኑን በትግራይ ክልል ማይካድራ ከተማ ውስጥ በጦርነቱ ውስጥ ምንም ዓይነት ተሳትፎ ያልነበራቸው፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች በስለታማ መሣሪያዎች ተወግተው መገደላቸውን ባደረገው ቅድመ ምርመራ ማረጋጡን ኢሰመጉ ገልጿል፡፡ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈጸም ጭፍጨፋ በማንም ይሁን በምንም ምክንያት ሊኖረው እንደማይገባ አክሏል፡፡
የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተጠርጣሪዎችን የዋስትና መብት አረጋግጦ ከእስር እንዲፈቱ እንዳደረገው ሁሉ፣ የክልሉ መንግሥት ሥራ አስፈጻሚና የፍትሕ አካላት በተመሳሳይ መልኩ የሌሎችም ተጠርጣሪዎች የዋስትና መብት መከበሩን እንዲያረጋግጡ ጠይቋል፡፡
ለተጠርጣሪዎች ፍርድ ቤት የዋስትና መብት ፈቅዶላቸውና ሁኔታዎችን ካሟሉ በኋላ፣ ከእስር እንዲለቀቁ የተሰጠው ትዕዛዝ ታልፎ በእስር እንዲቆዩ ማድረግ ፍትሕን ማጓደልና ሰብዓዊ መብቶችን የሚጥስ ተግባር መሆኑን አስታውሶ፣ ሌሎች ዋስትና የተፈቀደላቸው ተጠርጣሪዎች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ከእስር እንዲለቀቁም ጠይቋል፡፡
ኢሰመኮ በተጨማሪ እንደገለጸው፣ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ደረጃ ያሉ የመንግሥት ኃላፊዎች አበረታች የሆኑ ዕርምጃዎችን በመውሰድ የተሻለ ተግባር እየፈጸሙ መሆኑን ጠቁሟል፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ተጠርጣሪዎችና ተከሳሾች በፍርድ ቤት ዋስትና ተፈቅዶላቸው መከልከላቸው ተገቢ አለመሆኑን በመግለጽ፣ አቶ ልደቱ አያሌውንና ሁሴን ከድር (ዶ/ር)ን በምሳሌነት ጠቅሷል፡፡ የዋስትና መብት በሕገ መንግሥቱና ኢትዮጵያ በተቀበላቻቸው የሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶች የተረጋገጠ መሠረታዊ መብት መሆኑን ኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ገልጸው፣ በሕግ በግልጽ ከተመለከቱ ሁኔታዎች በስተቀር የዋስትና መብት በተቀላጠፈ አሠራር ተግራዊ መደረግ የሚገባው መብት መሆኑን አስምረውበታል፡፡