በኢትዮጵያ የሚታየው የዴሞክራሲ ዕጦት መነሻው ከታችኛው የትምህርት ደረጃ ጀምሮ  የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር ትምህርት በተግባር አለመሰጠቱ ነው የሚል ሐሳብ አላቸው፡፡ ለዚህም ተማሪዎችን በማሳተፍ ለውጥ ለማምጣት ያስችላል ያሉትን  ‹‹አዲስ ተማሪ አዲስ አፍሪካ አዲስ ዓለም›› ፕሮጀክት ነድፈው መንቀሳቀስ ከጀመሩ ዓመት ሆኗቸዋል፡፡ አቶ ስምኦን ከበደ ተሰማ የቮት ለኢትዮጵያዬ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ ከምሕረት ሞገስ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡

ሪፖርተር– ቮት ለኢትዮጵያዬ የተሰኘውን ድርጅት 2011 .የመሠረቱት በልጅዎ አማካይነት ነው ይባላል፡፡ ቢያብራሩልን?

አቶ ስምኦን፡- ልጄ ወደፊት ምን መሆን ትፈልጊያለሽ ስላት ጠቅላይ ሚኒስትር አለችኝ፡፡ ምላሽዋ አስደነገጠኝ፡፡ በወቅቱ የኬጂ 3 (አፀደ ሕፃናት) ተማሪ ነበረች፡፡ ሴቶች መሆን አይችሉም ወይ አለችኝ፡፡ መሆን ይችላሉ፣ ነገር ግን ህልምና ምኞትሽን ለማሳካት ትጉህ፣ ታታሪና ተመራማሪ መሆን አለብሽ አልኳት፡፡ በእኔ በኩል ባለንበት በሚያስፈራና በሚያስደነግጥ ሁኔታ ልጆቻችንና የልጅ ልጆቻችን የመንግሥትን አሠራር፣ የኢትዮጵያን ታሪክና የጨዋ ሥነ ምግባር በጭፍን እየረሱ በመጡበት ዘመን ልጄና ሌሎችም ልጆች እንደ አንድ ጠቅላይ ሚኒስትር መደራደርን፣ ትልልቅ ሥራዎችን መሥራት፣ የተለያዩ ኃላፊነቶችን መምራት፣ መወከልና በጀት ማስተዳደር ላይ ክህሎት ያላቸው ልጆች ማፍራት አለብኝ በሚል ነው ቮት ለኢትዮጵያዬ የተሰኘውን መንግሥታዊ ያልሆነና ዴሞክራሲ ማስፈን ላይ ያነጣጠረ ድርጅት የመሠረትኩት፡፡ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ባልተለመደበት አገርና አኅጉር ውስጥ እየኖርን ልጆቻችንን በሰላማዊ መንገድ ወደ ሥልጣን ማምጣት እንዴት ማለማመድ እንችላለን የሚለውን ለመመለስ፣ ቮት ለኢትዮጵያዬ በጎ አድራጎት ድርጅት እየሠራ ይገኛል፡፡ ለዚህም ዳሰሳ አድርጌያለሁ፡፡

ሪፖርተር– የዳሰሳው ውጤት ምን አሳየ?

አቶ ስምኦን፡- እያንዳንዱ ችግር በትምህርት ይፈታል ብዬ አምናለሁ፡፡ በመሆኑም በዳሰሳዬ ያየሁት የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር ትምህርትን ነው፡፡ የዚህ ትምህርት ዋና ዓላማው ዴሞክራቲክ የሆነ ማኅበረሰብ መፍጠር፣ መገንባትና ማሳደግ ነው፡፡  የሥነ ዜጋ ትምህርቱ ለዜግነታቸው ኃላፊነት የሚሰጡ፣ መረጃ ያላቸው፣ ያወቁ፣ ጠንካራ ተሳትፎና ንቁ ተማሪዎችን መቅረፅ ሲገባው ይህንን እያደረገ አይደለም፡፡ ተማሪዎች አጥጋቢ ውጤት የሚያመጡበት ትምህርት ነው፡፡ ይህንን ትምህርት ሚኒስቴርም በጥናት አረጋግጦታል፡፡ በትምህርቱ ጥሩ ውጤት ቢያመጡም በተግባር ሲታይ የወረደ ሥራ ነው የሚሠሩት፡፡ የራሳቸውን መብት የማያስከብሩ፣ የሰው መብት የሚጋፉ፣ ጥያቄዎቻቸውንና ፍላጎታቸውን ወክለው በአግባቡ የማይሳተፉ፣ ሥነ ምግባራቸው እጅግ የወረደ ናቸው፡፡ የትምህርቱ 11 ምዕራፍ ጠንካራ ይዘት አለው፡፡ ችግሩ በተግባር አለመለማመዳቸው ነው፡፡ ተማሪዎችን ስለዴሞክራሲ ለማስተማር ስለ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ በተግባር እስካላሳየን አስተማርን ማለት አይቻልም፡፡ ጠንካራ ሥነ ምግባር ማለት አንድ ወጣት ዕውቀትን በመሻትና በመመራመር የተላከበትን ትምህርት የመቅሰም ተልዕኮ ኃላፊነት በሚገባ ከቻለም፣ በአንፀባራቂ ሁኔታ አጠናቆ በውሳኔና በኢኮኖሚ ራሱን በመቻል፣ ጠንካራ የሥራ ባህል በማዳበር፣ ተቸግሮ ላስተማረው ሕዝብና አገር ቀጥተኛ ለውጥ በማምጣት አገር ወዳድነቱን ሲያስመሰክር ብቻ ነው፡፡

ይህ ማለት ሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር ትምህርት ውስጥ ዕውቀትን መሻት፣ ኃላፊነት ስሜት፣ ራስን መቻል፣ ጠንካራ የሥራ ባህልና አገር መውደድ አምስቱን ምዕራፎች በመተግበር ሥነ ምግባሩ ሲቀረፅ ነው፡፡ ዴሞክራሲ በሕዝብ የተወከለ መንግሥት ማለት ነው፡፡ ግን ይህ በበቂ አይገልጸውም፡፡ ሦስት ዋና እሴቶች መኖር አለባቸው፡፡ እኩልነት፣ ደኅንነትና ነፃነት አብረው መኖር አለባቸው፡፡ እነዚህም አሉ ተብሎ ሥርዓቱን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ዘርግተናል ብለን መቀመጥ አንችልም፡፡ በተለያዩ ደረጃዎች መደገፍና ባህል ማድረግ አለብን፡፡ ለዴሞክራሲ ሕይወት ለመስጠት መዝራት፣ መኮትኮትና ማሳደግ አለብን፡፡ ለዚህም ተማሪዎችን ከሥር ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ እስካላለማመድን ድረስ ተረካቢ ዜጎች ላይ ምንም ዓይነት የዴሞክራሲ እሴት ልናዳብር አንችልም፡፡ ስለዚህ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ሊተገበር የሚችለው ድምፅ በመስጠት ነው፡፡ ይህንን ክፍል ውስጥ ቁጭ ብሎ ንድፈ ሐሳብ በመማር ተማሪዎች ሊለማመዱት አይችሉም፡፡ በመራጭነት፣ በአስመራጭነትና በተመራጭነት ተሳታፊ በመሆን የሚሆናቸውን መሪ መምረጥ የሚችሉበትን መለማመድ አለባቸው፡፡ ይህ ዋና የሲቪል ማኅበረሰብና የዜግነት ኃላፊነት ነው፡፡

ሪፖርተር፡– ቮት ለኢትዮጵያዬ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ጽንሰ ሐሳብን በትምህርት ቤት በተግባር ለማምጣት ምን ዓይነት አካሄድ ይከተላል?

አቶ ስምኦን፡- ሦስት ዓላማዎች አሉን፡፡ አንደኛው ልጆች ከታችኛው የትምህርት ደረጃ ጀምሮ ጠንካራ የዴሞክራሲ መሠረት ገንብተው ተሳትፎን የሚያጠናክሩ ሰላማዊ ዜጎች መፍጠር ነው፡፡ ሁለተኛው ሴቶችን በየትምህርት ቤቱ በሚገኙ ክበባት ውስጥ ወደ ሥልጣን በማምጣት፣ የሴቶችን የአመራር ብቃትና ውሳኔ ሰጪነት ከልጅነት ጀምሮ  እንዲያዳብሩት፣ ወንዶች ልጆችም የሴቶችን ተፅዕኖ ፈጣሪነት እያዩ እንዲያድጉ ማድረግ ነው፡፡ ተማሪዎች የትምህርት ቤት ክበባትን ለመምራት በትምህርት ቤት ውስጥ በሚያደርጉት የምርጫ ውድድር አሸናፊና ተሸናፊዎች ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግርን እንዲለምዱ ማስቻል ሦስተኛው ነው፡፡

ሪፖርተር፡– ይህንን በቮት ለኢትዮጵያዬ ፕሮጀክት እንዴት ልትተገብሩት ትችላላችሁ?   

አቶ ስምኦን፡- አዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ከሚፈቅዳቸው 11 ክበባት በፕሮጀክታችን አራት ክበባት በማቋቋም ለተማሪዎች የዋናውን ምርጫ ሒደት በትክክል ማሳየት በሚችል መንገድ እናለማምዳለን፡፡ ሥልጣን ላይ መጥተው በክበባቱ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት፣ መደራደር፣ አብሮ መሥራትና፣ ጠንካራ ግንኙነት መፍጠር፣ የኃላፊነት ስሜትና የአመራር ጥበብ፣ ውሳኔ ሰጪነት፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት፣ ራስን መግለጽ፣ ስብሰባ መምራትና ንግግር መለማመድ አለባቸው፡፡ በዚህ መንገድ ካልሆነ በስተቀር የዴሞክራሲ ሥርዓትን አዳብረው ሊያድጉ አይችሉም፡፡ በዚህ ሁኔታ በክበባቱ ውስጥ ገብተን ዴሞክራሲን እንዲተገብሩት እንሠራለን፡፡

ሪፖርተር– በትምህርት ቤቶች የሚሰጠው መደበኛ ትምህርት ነው፡፡ እናንተ ለምታራምዱት ዓላማ ተጨማሪ ጊዜ ያስፈልጋል፡፡ እንዴት ልትሄዱበት አስባችኋልየእናንተን ፕሮጀክትስ እንዴት ወደ ትምህርቱ ታካትቱታላችሁ?

አቶ ስምኦን፡- የሠለጠኑት አገሮች ልጆቻቸውን ከልጅነት ጀምሮ ነው ምርጫን በየትምህርት ቤት የሚያለማምዱት፡፡በፕሮጀክታችን የምርጫ ወረቀት ተዘጋጅቶ፣ ለዕጩ ተወዳዳሪ ጥሪ ተደርጎ መራጮች ተመዝግበው፣ ዕጩዎች ብቁ ነን ብለው ወጥተው፣ ሚስጥራዊነቱ በተጠበቀ መንገድ ከልጅነታቸው ጀምሮ መምረጥ እንዲችሉ እናደርጋለን፡፡ ለዚህም ከትምህርት ሰዓት ውጪ ያለውን ጊዜ ነው የምንጠቀመው፡፡

ሪፖርተር– ምርጫውን የሚያካሂዱት ማንን ለምን ለመምረጥ ነው?

አቶ ስምኦን፡- በፕሮጀክታችን የምንሠራው በአራቱ ክበባት ማለትም የጤናና የሰውነት ማጎልመሻ፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ የአካባቢ ጥበቃና የአርት ክበባት ናቸው፡፡ በአራቱም አዳዲስ አሠራርና ሐሳብ ነው ያመጣሁት፡፡ በዚህ ዘርፍ ከሚመለከታቸው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ጋርም ተነጋግረናል፡፡ የነበረው አሠራር አስተማሪዎች ጎበዝ ተማሪዎችን መርጠው ዕጩ ያደርጋሉ፡፡ በፍላጎት የሚመጡም አሉ፡፡ ነገር ግን እኛ የምንሠራውና መቀየር አለበት የምንለው ክበባቱን የሚመራ ተማሪ፣ ሌሎችን አሳምኖና ተመርጦ መምጣት አለበት ነው፡፡ የሚፈለገው ተማሪዎቹ ራሳቸው እንችላለን፣ እናውቃለን፣ እንለውጣለን ብለው በዕውቀት ላይ ተመሥርተውና ተመርጠው፣ ከትምህርቱ ጎን ለጎን በየክበባቱ ሥራቸውን በኃላፊነት እንዲወጡ በተግባር ማለማመድ ነው፡፡ ለምሳሌ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የህዳሴ ግድብ በመገንባቱ ምንም ውኃ ወደ ዓባይ ወንዝ አይገባም ብለው የተናገሩት የእኛ ዲፕሎማሲ እጥረት ማሳያ ነው፡፡ የእኛና የልጆቻችን ራስን የመግለጽ ችሎታ ማነስ ያመጣብን ነው፡፡ ግብፆች በናይል ዙሪያ ከታች ከልጆች ጀምሮ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ሥራ ስለሠሩና ስለሚሠሩ ነው፣ ትራምፕን በተሳሳተ መረጃ ሊያሳምኑ የቻሉት፡፡ የራሳችንን ሀብት በተመለከተ እንኳን መግለጽ የማይችል ትውልድ እየተፈጠረ ነው፡፡በምክንያት የሚያምን ሳይንሳዊ የሐሳብ ሙግት  ማድረግ፣ ጠንካራ ግንኙነትና መደራደር የሚችል ትውልድ ከልጅነት ከትምህርት ቤት ጀምሮ ማሳደግ አለብን፡፡

በክበባቱ የምናደርገው ተማሪዎች በፍላጎት መጥተው በክበባት ስም ጉልበታቸው እንዳይበዘበዝ ጥንቃቄ አድርገን ተመዝግበው፣ ተከራክረውና ተመርጠው ክበባትን እንዲመሩ በማለማመድ ወደ ቀጣዩ ኃላፊነት ዴሞክራሲያዊነቱ በተጠበቀ መንገድ እንዲሸጋገሩ ማድረግ ነው፡፡ አገራችን ቀጣይነት ያለው ልማት ሊኖራት የሚችለው ማስረከብና መረከብ፣ መምራትና መመራት፣ ማመንና ማሳመን፣ መሸነፍና ማሸነፍ የሚችል ትውልድ ስንፈጥር ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ለተማሪዎች ከልጅነታቸው ጀምሮ በተግባርም ማስተማር አለብን፡፡ፕሮጀክታችን ልጆች ከልጅነታቸው ጀምሮ ከግለኝነትና ከስሜታዊነት በፀዳ መንገድ መሸነፍን በፀጋ የሚቀበሉ፣ ማሸነፍ ለአገልጋይነት ብቻ መሆኑን አውቀው ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ለማስተናገድ የማይቸገሩ ንቁ ዜጎች የሚፈጥር ነው፡፡ አልፎ አልፎ ለሚከሰቱ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ለውጦች በቀላሉ የሚላመዱ ዜጎችን ማፍራት ነው፡፡ ለሚከሰቱ ግጭቶችና ቅራኔዎች በውይይት የመፍታት ደንብና ሥርዓት የሚማሩበት ነው፡፡ ያለንን የተንኮታኮተ ዴሞክራሲ መጠገን የምንችለው ተማሪዎችን ከሥር በመራጭነት፣ በአስመራጭነትና በተመራጭነት በማለማመድ ወደ ዴሞክራሲ ሥርዓት ማምጣት ስንችል ነው፡፡ በመንግሥት በኩል የተጀመረውን ጠንካራ ጥረት የምንደግፈው ሆኖ ተማሪዎችን ከታች የዴሞክራሲ ሥርዓት እሴቶችን ማስተማር ብንጀምር በኢትዮጵያ የተንሰራፋውን ችግር መቅረፍ እንችላለን ብዬ አምናለሁ፡፡

ሪፖርተር– ፕሮጀክታችሁን ለመተግበር ከመንግሥት ተቋማት ጋር መጣመር ግድ ስለሚል፡፡ ከማን ጋር እየሠራችሁ ነው?

አቶ ስምኦን፡- ከመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ጋር ጠንካራ ግንኙነት እየፈጠርን ነው፡፡ከሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴርና ከአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ጋር ሆነን በአዲስ አበባ ከየካ፣ ከንፋስ ስልክ ላፍቶና ከአዲስ ከተማ ክፍላተ ከተሞች አሥር ትምህርት ቤቶች መርጠን ሥራ ለመጀመር ተዘጋጅተናል፡፡ ፕሮጀክቱን አምና ጥር መጨረሻ ላይ ለመጀመር ተፈራርመን በመጋቢት ወር ኮሮና ወረርሽኝ መጥቶ ተራዘመ፡፡ አሁን ኮቪድ እያለ ትምህርት ሲከፈት ከምርጫ በፊትና በኋላ ወረርሽኙን ለመከላል ሊደረጉ የሚገቡ ዘዴዎችን ተከትለን፣ ቫይረሱን ተከላከልን እንሠራለን ብለናል፡፡ ክበባቱ ራሳቸው የሚያስመርጡት የፓርላማ (የተወካዮች ምክር ቤት) ምርጫ አለ፡፡ ይህንን አብረን እናደርጋለን፡፡ የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ለአሸናፊ ተመራጮች ላፕቶፕ እንደሚሸልም ቃል ገብቶልናል፡፡ ተወዳዳሪዎቹ ከፍተኛ ፉክክር አድርገው በመከራከር፣ በኋላም ተመርጠው ነው ክበባቱን መምራት የሚችሉት፡፡ ለመመረጥ መከራከሪያ ይዘው መጥተው ተማሪዎችን ማሳመን አለባቸው፡፡ ለውድድሩ ሦስት ሴቶችና ሦስት ወንዶች የሚወዳደሩ ሲሆን፣ ለእያንዳንዱ ክበብ አንድ ወንድና አንድ ሴት ሥልጣን ይይዛሉ፡፡ በአንድ ትምህርት ቤት ውስጥ 30 ተወዳዳሪዎች ይኖሩናል፡፡ ይህንን የመፍትሔ ሐሳብ ተማሪዎች ላይ አልጣልንም፡፡ በአራት ትምህርት ቤቶች የዳሰሳ ጥናት ለማድረግ አስበናል፡፡ ቮት ለኢትዮጵያዬ ያመጣው አዲስ ተማሪ፣ አዲስ አፍሪካ፣ አዲስ ዓለም በሚባለው ፕሮጀክታችን ተማሪዎች ከዚህ ቀደም ምርጫ አድርገው እንደሚያውቁ ጠይቀን አናውቅም ብለዋል፡፡ አምና በሠራነው ዳሰሳ ከ90 በመቶ በላይ ተማሪዎች የክበባት መሪዎች በምርጫ ቢለዩ እንደሚፈልጉ አሳውቀዋል፡፡ ከ55 በመቶ በላይም ራሳቸው ዕጩ ሆነው መወዳደር ይፈልጋሉ፡፡ በሃይማኖት ብንሄድ እንኳን ልጅ ሊሄድበት በሚገባው መንገድ አሠልጥነው፣ በሚያረጅበት ጊዜ እንኳን ከዚያ ፈቀቅ አይልም ይላል፡፡ ተማሪዎቹ በጣም ቀና ናቸው፡፡ ለውጥ ማምጣትና ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆን የሚፈልጉ ናቸው፡፡ እነሱ የሚፈልጉት መስመር የሚያበጅላቸው ብቻ ነው፡፡

ሪፖርተር፡– ሐሳቡን ይዘው ሲነሱ የገጠመዎት ፈተና አለ?

አቶ ስምኦን፡- የለም፡፡ ከፍተኛ ድጋፍ አግኝቼበታለሁ፡፡ ርዕሳነ መምህራን ሐሳቤን አድንቀውታል፡፡ተግባራዊ መሠረት ሲያገኝ የሚያሸልም ሐሳብ ይሆናል ያሉኝም አሉ፡፡ ሐሳቡን ለምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ወስጄላቸው ነበር፡፡ ሐሳቡ መልካም ነው ብለውኛል፡፡ ግን እሳቸው ይኼንን መሥራት ስለማይችሉ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር እንድሠራበት በጠቆሙኝ መሠረት ተቀባይነት አግኝቶ፣ ከዓለም አቀፍ ዕርዳታ ለጋሾች ጋር እንድሠራ ድጋፍ ጽፈውልኛል፡፡ የዴሞክራሲ ተሳትፎ እጥረት እኛንም አፍሪካንም እያጠፋ ነው፡፡ ዜጎች ለጥያቄዎቻቸውና ለፍላጎቶቻቸው ግጭቶችና አመፆች በመፍጠር ኢሞራላዊና ሰብዓዊ ያልሆኑ ድርጊቶችን በመፈጸም እንደ ነጥብ ማስያዣ እየቆጠሩ ያሉት፣ ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎን ባለማወቃቸው ነው፡፡ ኢትዮጵያ በሥልጣኔ ፈር ቀዳጅ እንደነበረች ሁሉ  ራሳችን በራሳችን ዴሞክራሲን ባህል በማድረግ ለአፍሪካ ማስተማር አለብን፡፡ የቮት ኢትዮጵያዬ አንዱ ዓላማም እስከ 2030 ይህንኑ በአፍሪካ አገሮች መተግበር ነው፡፡

ሪፖርተር– ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎን ለማምጣት የመነሻው ቁልፍ ትምህርት ቤት ውስጥ ነው ብለዋል፡፡ ትምህርት ቤት ከአፀደ ሕፃናት እስከ 12 ነው፡፡ ከየትኞቹ ክፍል ተማሪዎች ነው ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎን በተግባር የምታስጀምሩት?

አቶ ስምኦን፡- የምንሠራው ከአምስተኛ እስከ 12ኛ ክፍል ባሉ ተማሪዎች ላይ ነው፡፡ በታቀደና በተደራጀ መንገድ ያልተደረገ ምርጫ ውዝግብ አለው፡፡ ስለሆነም በዕድሜያቸው ጠንከር ከሚሉበት ከአምስተኛ ጀምረን እስከ 12 ክፍል ያሉትን እናሳትፋለን፡፡ ለተማሪዎች ሥልጠና እንሠጣለን፡፡  ዕጩዎችን ባህሪያቸውን እንዲያስተውሉ፣ የሚያነሱትን ሐሳብስ፣ አካታች አጀንዳ ይዘዋል ወይ? ተግባራዊ መሆን የሚችል ሐሳብ ነው? የሚሉትንና በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ እናሠለጥናቸዋለን፡፡ ተመረጡም አልተመረጡም በመምራት ክህሎት፣ ባለው ሀብት በመጠቀም፣ መረጃ በመሰብብና በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ሥልጠና እንሰጣለን፡፡ ሥልጠናው በታቀደና በተደራጀ መንገድ ሆኖ አገራዊውን ምርጫ እንዲመስል ለመምህራንም ሥልጠና እንሰጣለን፡፡ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ እንዲያካሂዱ እናግዛቸዋለን፡፡ ለዚህም ምርጫ ቦርድም እንዲያግዘን ጥሪ ማድረግ እፈልጋለሁ፡ ለፕሮጀክቱ የመግባቢያ ስምምነት የፈጸምን ቢሆንም፣ በምንሠራባቸው ትምህርት ቤቶች መሠረት እየጣልን ራሳቸው እንዲያስቀጥሉት ነው የምናደርገው፡፡

ሪፖርተር፡– ይህንን በክልሎች መቼ ትጀምራላችሁ?

አቶ ስምኦን፡- አሁን በአዲስ አበባና ዙሪያዋ በ20 ትምህርት ቤቶች የሙከራ ፕሮጀክት ይዘን እንሠራለን፡፡ ከኦሮሚያ ሦስት፣ ከአማራ ሁለት፣ ከትግራይ ሁለት፣ ከደቡብ ሁለት፣ እንዲሁም ከሲዳማ ክልሎች አንድ አድርገን የምንቀጠል ይሆናል፡፡ ሁሉንም በአንዴ ብንጀምር መቆጣጠር የማንችለው ሆኖ ያለ ውጤት እንዳይቀር በሒደት የምንሠራው ይሆናል፡፡ ሐሳባችንን በእነዚህ ላይ ተግብረንና የውጤት ግምገማ አድርገን እንቀጥላለን፡፡ ዴሞክራሲን ማስተማር መንግሥት ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ተግባር ነው፡፡ ያለንን ነባራዊ ሁኔታና የተፍረከረከ ዴሞክራሲ መጠገንና ማከም የምንችለው ተማሪዎችን ከትምህርት ቤት ጀምሮ ዴሞክራሲን በማለማመድ ነው፡፡ በክልሎች የሚፈጠሩ ዴሞክራሲያዊ ያልሆኑ ዕይታዎችና ድርጊቶችን ለመፍታት የክልል ትምህርት ቢሮዎች ፕሮጀክቱን ወደ ራሳቸው በመውሰድ እንዲተገብሩ ጥሪ እናቀርባለን፡፡ ፕሮጀክቱ ያለውን የዴሞክራሲ ዕጦት ችግር ሊቀርፍ የሚችል ነው፡፡

ሪፖርተር፡– ፕሮጀክቱ አካል ጉዳተኞችን ለማሳተፍ ምን ያህል ተጉዟል?

አቶ ስምኦን፡- ቲሻየር ሆም ኢትዮጵያ የፕሮጀክቱን ዓላማ ከደገፉት አንዱ ድርጅት ነው፡፡  ድርጅቱ በየትምህርት ቤቱ ለአካል ጉዳተኞች የማያመቹ የምርጫ ቁሳቁሶች ችግር ካለ እንድናሳውቃቸውና እነሱም እንደሚተባበሩን ነግረውናል፡፡ ለአካል ጉዳተኞች በሙሉ ምርጫን የመለማመድና ዴሞክራሲያዊ ዜጋን የማፍራት ዕድል እንሰጣለን፡፡ በምንሠራባቸው ትምህርት ቤቶች አካል ጉደተኞች ካሉና ዕጩ ሆነው መወዳደር ከፈለጉ እንዲሳተፉ ቅድሚያ እንሰጣለን፡፡

ሪፖርተር፡ በተለያዩ ዘመናት ተመሳሳይ ትምህርት ተሰጥቷል፡፡ ለምን ወደ ዴሞክራሲ ሊያስጠጋን አልቻለም?

አቶ ስምኦን፡- በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ‹‹ሞራል ኢዱኬሽን››፣ በደርግ ‹‹ፖለቲካ ኢዱኬሽን›› ተብሎ የራሳቸውን ፍላጎት ሲያስተምሩበት ነበር፡፡ ስለዴሞክራሲ እናስተምር ካልን በተግባር ማውረድ አለብን፡፡  በተለይ በክልል የተግባር ትምህርቱን አውርዶ የሚፈጠሩ ችግሮችንና የሴችን ተሳታፊነት ችግር መቅረፍ እንችላለን፡፡ በክልል ያሉ ሴቶችን አመራር ቦታ ማምጣት የምንችለው ከልጅነት ጀምሮ ስናለማምዳቸው ነው፡፡ ካደጉ በኋላ ሥልጣን ላይ ብናመጣ አስተዳደጋቸው በራሱ ይጎትታቸዋል፡፡ የዴሞክራሲ አካል የሆነው ሰላም የሚመጣውም ከታች ጀምሮ በትምህርት ቤት ከሠራንበት ነው፡፡ ይህ እንዲሆንም ለሰላም ሚኒስቴር ጥሪ ማቅረብ እንፈልጋለን፡፡ ፕሮጀክታችን ለግዙፍና ለውስብስብ ፕሮጀክቶች ግብዓት በመሆን፣ ፕሮጀክቶችን ለማስጠበቅና ለማስቀጠል የሚችሉ ብዙ ዜጎችን የሚቀርፅ ነው የሚሆነው፡፡ ለዚህም በኢትዮጵያ ያሉ ተማሪዎችን በሙሉ እናሳትፋለን፡፡ አልፈንም ወደ ሌሎች የአፍሪካ አገሮች እንዘልቃለን፡፡ ከዚህ በኋላ ቀጣሪዎች የሚፈልጉትም ራሳቸውን የሚገልጹ፣ ማሳመን የሚችሉ፣ ስብሰባ የሚመሩ፣ የሚያደራጁ፣ ማቀናጀትና ለውጥ መፍጠር የሚችሉ ዜጎችን ነው፡፡ የእኛ ፕሮጀክት ተማሪዎችን ለዚህ ብቁ ያደርጋቸዋል፡፡

ምንጭ፡  ሪፖርተር

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *