አለማቀፍና አገር አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፣ በህወኃትና በፌደራል መንግስት መካከል በተቀሰቀሰው ጦርነት ንፁሃን እንዳይጐዱ፣ ሁሉም አካላት ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በበኩሉ፤ ጦርነቱ ቆሞ ሠላማዊ ውይይት እንዲጀመር አሳስቧል፡፡
የጦርነቱ አካባቢ በሆነው የትግራይ ክልል የዜጎች ደህንነትና የሰብአዊ እርዳታ አገልግሎት አቅርቦትን ሁሉም አካላት ሊያረጋግጡ እንደሚገባ ያሳሰበው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን፤ የግጭቱ ባህርይና ሁኔታም በእጅጉ አሳሳቢ ነው ብሏል፡፡


በጦርነቱ መሃል ሠላማዊ ዜጐች ምንም አይነት ሰብአዊ ጉዳት እንዳይደርስባቸው፣ ሁሉም ወገኖች ኃላፊነት እንዳለባቸው ያስገነዘበው ኮሚሽኑ፤ ትግራይን ከሌላው የኢትዮጵያ ክልል የሚያገናኙ መንገዶችም አለመዘጋታቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ብሏል፡፡ በትግራይ ክልል በርካታ የሌሎች ሀገራት ዜጐች በስደተኝነት እንደሚገኙ በመጠቆምም፣ ጉዳት እንዳይደርሰባቸው አስፈላጊው ጥንቃቄ እንዲደረግ አሳስቧል፡፡
በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሠመጉ)፤ ግጭቱ የሠላማዊ ዜጐችን ደህንነት አደጋ ላይ የማይጥልና በሲቪል ንብረቶች ላይ ውድመት የማያደርስ መሆኑን ሁሉም ወገኖች እንዲያረጋግጡ ጥሪ አቅርቧል፡፡ በጦርነቱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እንዳይፈጸም ከማረጋገጥ ጐን ለጐን፣ ሁሉም ወገኖች  ለሰላማዊ ንግግር እድል እንዲሰጡም ኢሠመጉ አሳስቧል፡፡

ለአንድ ሳምንት የሚቆይ ፀሎትና ምህላ እንዲደረግ ታዝዟል

“የተለያዩ ወገኖችም ግጭቶችን ከማባባስ ሊቆጠቡ ይገባል” ያለው ኢሠመጉ፤ ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የሲቪል ማህበራት፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦችና መላው ኢትዮጵያውያን፣ ግጭቱ እንዳይባባስና ልዩነቶች በሠላማዊ ውይይት እንዲፈቱ ግፊት ያደርጉ ዘንድ ኢሠመጉ ጠይቋል፡፡
ሁሉም የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎችና መገናኛ ብዙኃን፣ ህዝብን ለግጭት የሚያነሳሱና ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት የሚዳርጉ የሐሰት ዜናዎችን፣ የተሳሳቱ የተዛቡና የተበከሉ መረጃዎችን ከመናገርና ከማሠራጨት እንዲቆጠቡም ኢሠመጉ አሳስቧል፡፡
አለማቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች አምነስቲ ኢንተርናሽናል በበኩሉ፤ በጦርነቱ ሁለቱ ወገኖች ለአለማቀፍ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች ተገዢ እንዲሆኑና የሰላማዊ ሰዎችን መብት እንዲያስከብሩ አሳስቧል፡፡ በሁለቱ አካላት የተጀመረው ጦርነት ሰላማዊ ሰዎችን አደጋ ላይ የሚጥል፣ የሀገሪቱን የሰብአዊ መብት ይዞታም እንዲያሽቆለቁል የሚያደርግ ነው ብሏል – አምነስቲ፡፡
የፌደራል መንግስትና የትግራይ አስተዳደር፣ በጦርነቱ የዘጉትን የስልክና ኢንተርኔት አገልግሎት እንዲከፍቱ የጠየቀው ተቋሙ፤ ሰዎች እርስ በእርስ እንዲገናኙ ያደርጉ ዘንድም አሳስቧል፡፡


ጦርነቱ በእጅጉ አሳስቦኛል ያለው የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤው፤ ጦርነቱ አውዳሚና ዜጐችን ለከፋ የሰብአዊ ጉዳት የሚዳርግ በመሆኑ በአስቸኳይ ቆሞ ችግሮች በውይይት እንዲፈቱ ጥሪ አቅርቧል።
ሁሉም ወገኖች ቅድሚያ ለሀገር እንዲሰጡ ያሳሰበው ጉባኤው፤ የፌደራልና የትግራይ ክልል ባለስልጣናት፤ ከሁሉም በፊት ቅድሚያ ለሀገሪቱ ሠላምና መረጋጋት በመስጠት፣የጀመሩትን የእርስ በእርስ ወታደራዊ ግጭት ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲያቆሙ ነው በአጽንኦት ያሳሰበው፡፡
የብልጽግና እና የህወኃት ፓርቲ አመራሮችም በመካከላቸው የተፈጠረውን ልዩነት በመነጋገር ሊፈቱ እንደሚገባ ያሳሰበው በየደረጃው የሚገኙ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎች፣ እናቶች፣ ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ መገናኛ ብዙኃን ችግሩ በሠላማዊ መንገድ እንዲፈታ ጥረት እንዲያደርጉና ለሚደረገው ጥረትም ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቋል፤ ጉባኤው በመግለጫው፡፡
ወጣቶችም ግጭቶችን ከሚያባብሱ ድርጊቶች እንዲቆጠቡም ነው ጉባኤው ያሳሰበው፡፡ ከጥቅምት 26 ቀን ጀምሮም፣ ሁሉም ቤተ እምነቶች፣ ለአንድ ሳምንት የሚቆይ ፀሎትና ምህላ እንዲያደርጉ ጉባኤው ጠይቋል፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *