የማኅበሩ መሥራችና የቦርድ ሰብሳቢ የሕግ ባለሙያዋ ወ/ሮ የትነበርሽ ንጉሤ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አካል ጉዳተኞች በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ገብተው መማር የጀመሩት በ1956 ዓ.ም. እንደነበርና በቁጥርም ሁለት እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡ እነዚህ ሁለት የአካል ጉዳተኞች በ1960 ዓ.ም. ተመርቀው በተለያዩ ቦታዎችና ኃላፊነቶች ላይ ሲያገለግሉ የነበረ ሲሆን፣ ባለፉት 50 ዓመታት ውስጥ ግን ከ400 በላይ አካል ጉዳተኛ የሕግ ምሩቅ ባለሙያዎች በዘርፉ ተሰማርተው በማገልገል ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የአካል ጉዳተኛ የሕግ ባለሙያዎች ዓቃቤ ሕግ፣ ተመራማሪ፣ መምህርና ጠበቃ ሆነው ከማገልገልና ከመሥራት ባለፈ፣ ማኅበር መሥርተው መንቀሳቀስ እንዳይችሉ ክልከላ እንደነበረባቸው የጠቆሙት ወ/ሮ የትነበርሽ፣ ባለሙያዎቹ ክስ መሥርተውና እስከ ሰበር ችሎት በደረሰ ክርከር ማኅበር መመሥረት እንዲችሉ የሚያስገድድ ውሳኔ በማግኘታቸው፣ ላለፉት ሦስት ዓመታት ሲንቀሳቀሱ ቆይተው በኢትዮጵያ የመጀመርያ የሆነውን የአካል ጉዳተኞች የሕግ ባለሙዎች ማኅበር ሊመሠረት መቻሉን ገልጸዋል፡፡

ማኅበሩን የመሠረቱት ስምንት አካል ጉዳተኛ የሕግ ባለሙያዎች ሲሆኑ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ምክትል ዋና ዓቃቤ ሕግ አቶ ፈቃዱ ፀጋ፣ ወ/ሮ የትነበርሽ ንጉሤ፣ ወ/ሮ ወሰንየለሽና ወ/ሮ ርግበ ከመሥራቾቹ ውስጥ ናቸው፡፡

ማኅበሩን ለመመሥረት ከባለፈው ዓመት ኅዳር 29 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ የተንቀሳቀሱ ቢሆንም፣ የዓለም ችግር የሆነው ኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ 19) በመከሰቱ፣ እስካሁን ቆይቶ ጥቅምት 13 ቀን 2013 ዓ.ም. ሊመሠረት መቻሉን አክለዋል፡፡ በምሥረታው ላይ ከኦሮሚያ፣ ከደቡብና ከድሬዳዋ የተገኙ አካል ጉዳተኛ የሕግ ባለሙያዎች ተወካዮች መገኘታቸውንና በየክልላቸው ባለሙያዎቹን የማሰባሰብና የማደራጀት ሥራ እንደሚሠሩም ገልጸዋል፡፡ በሌሎቹ ክልሎች ያሉ ባለሙያዎችም በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ሳይሳተፉ ቢቀሩም፣ የማደራጀትና የማሰባሰብ ሥራውን ግን እንደሚሠሩም አክለዋል፡፡

አካል ጉዳተኛ የሕግ ባለሙያዎች የተለያዩ ተግዳሮቶች ይገጥሟቸው እንደነበረ ጠቁመው፣ በማኅበር መደራጀታቸው እየተመካከሩ መብቶቻቸውን ከማስጠበቅ ባለፈ፣ የተጠናከረ የሕግ ድጋፍ ለማድረግም እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል፡፡ ወቅቱን የጠበቀና ትምህርት ሰጪ የሆነ ወርኃዊ ውይይት ከማድረግም በተጨማሪ፣ በአዳዲስ የሕግ ማዕቀፎችና ሌሎች የሕግ ጉዳዮች ላይ ውይይት በማድረግ፣ ለአካል ጉዳተኞች የአቅም ማጎልበቻ ሥራዎችን እንደሚሠሩም አክለዋል፡፡

አካል ጉዳተኛ የሕግ ባለሙያዎች በግለሰብ ደረጃ ከቢሮ ኃላፊነት እስከ ትልልቅ ተቋማት መሪነት የደረሱ ቢሆንም፣ በተቋም ደረጃ በመሰባሰብ ደግሞ ከፍ ያለ አገልግሎት ለመስጠት መለያቸው በሆነው አካል ጉዳተኛነት ስም ማኅበሩ መቋቋሙ እንዳስደሰታቸውም ሰብሳቢዋ ተናግረዋል፡፡ አካል ጉዳተኞች የጋራ የሆኑ ብዙ ነገሮች ስላሏቸው በንቃት በመሳተፍ ማኅበሩ አገራዊ ፋይዳ ያለው ሥራ እንደሚሠራም ገልጸዋል፡፡ በማኅበሩ ምሥረታ ላይ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ፣ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ተገኝተዋል፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *