በኢትዮጵያ እየጨመረ የመጣውን የፆታ ጥቃት ለማስቆም አስተዋጽኦ ያደርጋል የተባለውን ብሔራዊ የፆታ ጥቃት አድራሾች ምዝገባ ሥርዓት ሊጀምር መሆኑን የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ሚኒስቴሩ በአሥርና በአምስት ዓመት ዕቅዱ ካካተታቸውና በ2013 ዓ.ም. ከጀመራቸው ሥራዎች ብሔራዊ የፆታ ጥቃት አድራሾች ምዝገባ አንዱ ሲሆን፣ ይህም ከሕግ ቅጣት ተጨማሪ ሆኖ የድርጊቱን ፈጻሚዎች እስከ ሕይወት ፍፃሜያቸው በመከተል ለራሳቸው እንዲፀፀቱ፣ ለሌሎች ደግሞ መማሪያ እንዲሆን ያስችላል ተብሏል፡፡

የሚኒስቴሩ ሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አድነው አበራ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከፕላን ኮሚሽንና ከተለያዩ አካላት ጋር ሥርዓቱ እንዴት ሊዘረጋና ሊተገበር እንደሚችል በመነጋገር ተፈጻሚ የሚደረግ ነው፡፡ ዋና ዓላማውም ጥቃት አድራሾች በወንጀል ሕግ ብቻ ተቀጥተው መቆም ስለሌለባቸው፣ አንድ ጊዜ የፈጸሙት ጥቃት ሁልጊዜም እንደፈጸሙት በማስታወስ ድርጊቱን ከመፈጸም በፊት ቆም ብለው እንዲያስቡበት ለማድረግ ነው ብለዋል፡፡

ከአራት ሴቶች አንዷ በቅርብ በምታውቀው ሰው የወሲብ ጥቃት ይፈጸምባታል

 

ጥቃት አድራሾች የሕግ ሥርዓቱን ተከትሎ ፍርድ ከተፈረደባቸው በኋላ ተመዝግበው፣ ከአንዳንድ ማኅበራዊ አገልግሎቶች እንዲገለሉና ማኅበራዊ ቅጣት እንዲጣልባቸው፣ በሕይወታቸው ሙሉ የሚከተላቸው ጥፋት ውስጥ እንደሚገቡ አውቀው ስህተቱ ሁሌም ተከትሏቸው እንዳይሄድ ሲሉ ከድርጊቱ እንዲቆጠቡ ያስችላል ተብሎም ታምኖበታል፡፡

ፆታዊ ጥቃት ያደረሰም ሆነ ሌላ ወንጀል የፈጸመ ሰው ፍርድ ቤት ተፈርዶበት ቅጣቱን ከጨረሰ በኋላ እስከ አምስት ዓመት ምንም ዓይነት ጥፋት ካላጠፋ ከወንጀሉ ነፃ እንደሆነ ስለሚቆጠር፣ ቅጣቱን የጨረሱ የፆታ ጥቃት ፈጻሚዎች ከመዝገብ ሰነዱ ይሰረዛሉ ወይ? ተብለው የተጠየቁት አቶ አድነው፣ አንድ ሰው በአንድ ወንጀል የሚቀጣው አንድ ጊዜ ብቻ ቢሆንም፣ የፆታ ጥቃት የፈጸመ ሰው ከምዝገባ ሰንጠረዡ ዕድሜ ልኩን አይሰረዝም ብለዋል፡፡

የፆታ ጥቃት መፈጸማቸው በፍርድ ቤት ተረጋግጦ በብሔራዊ የፆታ ጥቃት አድራሾች ምዝገባ የሠፈሩ ሰዎች ከየትኞቹ ማኅበራዊ አገልግሎቶች ይታገዳሉ በሚለው ላይ፣ ከክልሎችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመምከር ይፋ የሚደረግ ይሆናልም ብለዋል፡፡

የምዝገባው ዓላማ ፆታዊ ጥቃትን ማስቆም ነው ያሉት አቶ አድነው፣ ስለምዝገባው ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ ለመስጠት እንደሚሠራም አስታውቀዋል፡፡ ሚኒስቴሩ ባለፉት ሦስት ወራት ካከናወናቸው ተግራት የፀረ ጥቃት ፖሊስ ለማቋቋም ዝግጅት መጀመር ሲሆን፣ ይህ ከዚህ በፊት ከነበረውና በየፖሊስ ጣቢያው የሴቶችና ሕፃናት ጉዳዩችን ከሚያየው የተለየና አዲስ መሆኑን አቶ አድነው ገልጸው፣ በሚቋቋመው የፀረ ጥቃት ፖሊስ ውስጥ የሚካተቱት በፆታ ጥቃት ላይ ልዩ ሥልጠና የወሰዱ ፖሊሶች ይሆናሉ ብለዋል፡፡

በፆታ ጥቃት ውስጥ በሚካተተው ወሲባዊ ጥቃትንና የፆታ ጥቃት አድራሾች ምዝገባ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሕግ ባለሙያው አቶ አዶናይ ሰይፉ ወሲባዊ ጥቃት፣ ኃይልን በመጠቀም በሌላ ሰው ላይ ያለፍላጎቷ/ቱ የሚፈጸም ማንኛውም የወሲብ ድርጊትና የወሲብ ድርጊትን የመሳሰሉ ለመልካም ፀባይ ተቃራኒ የሆኑ ድርጊቶችና  አስገድዶ መድፈር፣ የወሲብ ንግድ፣ ፆታዊ ትንኮሳ፣ ግብረ ሰዶምና የመሳሰሉትን ትንኮሳዎች እንደሚያካትት ያስረዳሉ፡፡ እነዚህ የወንጀል ድርጊቶች በወንዶችም በተለይም በሕፃናት ወንዶች ላይም እንደሚፈጸሙ ያክላሉ፡፡

ከአገር አገር ልዩነት ቢኖርም ከጥቂት አገሮች የተሰበሰቡ መረጃዎችን በመጥቀስ አቶ አዶናይ እንዳሉት፣ ከአራት ሴቶች አንዷ በቅርበት በምታውቀው ሰው ወሲባዊ ጥቃት ይፈጸምባታል፡፡ ወሲባዊ ጥቃት በማንኛውም ሰው፣ በማንኛውም ሥፍራ በማንም ሰው ላይ በቤተሰብ፣ በቅርብ ዘመድ፣ በባል፣ በወንድም፣ በጓደኛ፣ በመምህራን፣ በቢሮ ኃላፊዎች፣ በመሪዎችና በባለሥልጣናት፣ በሃይማኖት አባቶችና በማንኛውም የኅብረተሰብ ክፍል በቤት፣ በትምህርት ቤት፣ በሥራ ቦታ፣ በመንገድና በማንኛውም ቦታ ሊፈጸም ይችላል ይላሉ፡፡

ድርጊቱ በተጠቂዋ/ው ላይ ከሚያስከትላቸው እጅግ ሥር የሰደደ አካላዊና ሥነ ልቦናዊ/ስሜት ነክ/ጉዳቶች ወሲባዊና የሥነ ተዋልዶ ጤና ቀውሶችን፣ ለኤችአይቪ መጋለጥን፣ የራስን ሕይወት ማጥፋትን፣ ከማኅበረሰብ መገለልን፣ ወዘተ መጥቀስ እንደሚቻልም አክለዋል፡፡

የኢትዮጵያን የወንጀል ሕግ ጠቅሰው አቶ አዶናይ እንዳብራሩት፣ በግብረ ሥጋ ነፃነትና ንፅህና ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን (አንቀጽ 620-628)፣ ለተፈጥሮ በተቃራኒ ባህሪይ የሆኑ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ድርጊቶችን በተመለከተ (አንቀጽ 629-632)፣ የተለያዩ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን አንቀጽ 561-562፣ ጠለፋ አንቀጽ 587-590፣ ያለ ዕድሜ ጋብቻ አንቀጽ 647-648፣ አካል ላይ ጉዳት ማድረስ አንቀጽ 555-560፣ ግንኙነት ባላቸው ሰዎች መካከል የሚፈጸም ጥቃት አንቀጽ 564፣ በሴቶችና ሕፃናት መነገድ አንቀጽ 597-599፣ የዝሙት ተግባር አንቀጽ 635-638፣ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ሕፃናትን መጉዳት አንቀጽ 576፣ የልጅ የማሳደግ ግዴታን አለመፈጸም አንቀጽ 659 እና የመሳሰሉትን ለሴቶችና ሕፃናት መብትና ደኅንነት ጥበቃ የሚሰጡ ድንጋጌዎችን አስቀምጧል፡፡

አገሮች የወሲባዊ ወይም ወሲብ ነክ ጥቃቶችን ለመከላከልና ተፈጽሞም ሲገኝ ፈጻሚውን ለመቅጣት ከሚወስዷቸው በርካታ ዕርምጃዎች መካከል የወሲባዊ ጥቃት (አንዳንዶች የፆታ ጥቃት ይሉታል) አድራሾች ምዝገባ (National Sex Offenders Registry)፣ ወይም የመረጃ ምዝገባ ሥርዓት እንዲኖርና ወንጀለኛውን ከአንዳንድ ማኅበራዊ አገልግሎት ከተወሰነ ጊዜ እስከ ዕድሜ ልክ ድረስ ማገድን ይጨምራሉ፡፡

ይህን ሕግ በማውጣት ሥራ ላይ ያዋሉ በርካታ አገሮች ያሉ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ በአውስትራሊያ፣ በካናዳ፣ በአሜሪካ፣ በጃማይካና በህንድ (እ.ኤ.አ. ከመስከረም 2018 ጀምሮ)፣ በደቡብ አፍሪካ (እ.ኤ.አ. ከ2000 ጀምሮ) ይጠቀሳሉ፡፡

እንደ አሜሪካ ያሉ የተጠናከረና ዘመናዊ የሕግ ሥርዓት ያላቸው አገሮች እ.ኤ.አ. ከ1990ዎቹ መጀመርያ አንስቶ የወሲባዊ ጥቃቶችን ለመከላከልና ለመቀነስ የወሲባዊ ጥቃት ፈጻሚዎች መረጃ ምዝገባ ሥርዓትን ከፌዴራል ጀምሮ እስከ ታችኛው የአካባቢያዊ አስተዳደር ለመዘርጋት መቻላቸውን ያስታወሱት አቶ አዶናይ፣ በእነዚህ የሕግ ማዕቀፎች መሠረት የወሲባዊ ጥቃቶችን በመፈጸማቸው ፍርድ ቤት ቅጣት የጣለባቸው ወንጀለኞች የተወሰነባቸውን ቅጣት ፈጽመው ከእስር ከተለቀቁ በኋላ፣ በሚኖሩበት አካባቢ በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ በመቅረብ መጠሪያ ስማቸውን፣ ትክክለኛ የመኖሪያ አድራሻቸውን እንዲያስመዘግቡ፣ ያስመዘገቡትን መኖሪያም ለቀው ሲሄዱ አዲሱን አድራሻቸውን የማስመዝገብ ሕጋዊ ግዴታ እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡

ሕጉ ይህን አስገዳጅ ድንጋጌ በማስቀመጥም የእነዚህን ሰዎች ዱካ ለመከታተልና ተመሳሳይ ድርጊቶችን እንዳይፈጽሙ ለመቆጣጠር እንደሚያስችል፣ ከዚህ በተጨማሪም ሕጉ የፖሊስን የወንጀል ምርመራ ፈጣንና ውጤታማ እንደሚያደርገው አክለዋል፡፡

እ.ኤ.አ. ከግንቦት 1996 ጀምሮ ተፈጻሚ መሆን የጀመረውና የሜጋን ሕግ ተብሎ የሚጠራው ይኼው የአሜሪካ ሕግ ማዕቀፍ የወሲባዊ ጥቃቶችን በመፈጸማቸው ፍርድ ቤት ቅጣት የጣለባቸው ወንጀለኞችን ፎቶግራፎች፣ ስሞችና አድራሻዎች በይነ መረብ ወይም ኢንተርኔት በሌሎች ማኅበረሰባዊ መገናኛ ዘዴዎች ለሕዝቡ ይፋ ይደረጋል፡፡ እነዚህን መረጃዎች ለሕዝብ ይፋ በማድረግ አሜሪካ ብቸኛዋ ስትሆን፣ ሌሎች አገሮች ግን በሕጋቸው መሠረት መረጃዎቹን ማግኘት የሚችሉት የሕግ አስከባሪ አካላት እንደ ፖሊስ ዓቃቤ ሕግ ያሉት ብቻ ናቸው፡፡

ይህ ሕግ በተለይ በአሜሪካ የሲቪል መብቶችን የሚፃረር ነው በማለት ከበርካታ ወገኖች ቅሬታ ይቀርብበታል፡፡ እንዲያውም ጉዳዩን ያጠኑ በርካታ ተመራማሪዎች ሕጉ የወሲባዊ ጥቃቶችን ለመከላከል ወይም ለመቀነስ ይህ ነው የሚባል ተጨባጭ ማስረጃ ማቅረብ አይችልም ይላሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ በተቃራኒው እጅግ እየከፋ ሄዶ የነበረውን ይህን የወንጀል ድርጊት ለማስቆም ባይቻል እንኳን ለመቀነስ ተችሏል ሲሉ መረጃ በመጥቀስ ይሞግታሉ፡፡

የአንዳንድ አገሮች የምዝገባ ሕጎች የወሲባዊ ጥቃቶችን በመፈጸማቸው ፍርድ ቤት ቅጣት የጣለባቸው ወንጀለኞችን የልጅ አሳዳጊነት መብት፣ የፖለቲካዊ ተሳትፎ መብቶች፣ ለምሳሌ የመምረጥና የመመረጥ መብቶችና የመሳሰሉትን መብቶቻቸውን ለመጠቀም እንዳይችሉ ያደርጓቸዋል፡፡

እንዲህ ዓይነቱ የሕግ ማዕቀፍና አሠራር በእኛ አገር መታሰቡ መልካም መሆኑን የገለጹት አቶ አዶናይ፣ በተለይ በአፈጻጸም ወቅት በርካታ ፈተናዎች ሊያጋጥሙት ስለሚችሉ የማኅበረሰቡ ንቃተ ኅሊና ማለትም የማኅበረሰቡን ተቀራርቦ የመኖር ሁኔታን ጨምሮ ለወሲባዊ ጥቃት ያለን አነስተኛ አመለካከትና ግምት፣ የሕግ አስከባሪና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት አዕምሯዊና መዋቅራዊ ዝግጁነቶች፣ በሕገ መንግሥቱ ዕውቅና ከተሰጣቸው የዜጎች የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ጋር ሊኖር ከሚቻለው አለመጣጣም ጋር ከወዲሁ ማጤን ይገባል ብለዋል፡፡

ይህን ሕግና አሠራር ለማርቀቅና ለማስፈጸም ኃላፊነት የሚሰጣቸው የመንግሥት አካላት የሌሎች አገራትን ተሞክሮዎች በጥልቀት ማየትና መመርመር፣ ከተለያዩ የማኅበረሰብ አካላት ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶችን ማድረግ፣ እንደ ፖሊስ ላሉ የሕግ አስከባሪ አካላት ከወዲሁ የተለየ ሥልጠና መስጠት፣ አስፈላጊ የሆኑ የሰው ኃይል ሀብቶችና ብቁ ተቋማትን ማደራጀትና መፈጸም ይጠበቅባቸዋል ሲሉም የሕግ ባለሙያው አቶ አዶናይ ገልጸዋል፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *