ቅዱስ ሲኖዶስ ለሰባት ቀናት ጸሎተ ምሕላ እንዲደረግ ውሳኔ አስተላለፈ

አዲስ አበባ የራሷ ሀገረ ስብከት እንዲኖራትም ተወስኗል

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቤተ ክህነት፣ በምዕራብ ወለጋ ጥቅምት 22 ቀን 2013 ዓ.ም. በንፁኃን ዜጎች ላይ የተፈጸመውን ግድያ አወገዘች፡፡

ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ፣ ምንም ዓይነት የፖለቲካ አመለካከት የሌላቸውን ንፁኃን መግደል ነውር ነው ብለዋል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ 39ኛ ዓመታዊ ጉባዔውን እያካሄደ ባለበት ወቅት ጭካኔ የተመላበትን ድርጊት መፈጸሙ እንደተሰማ አስታውሰው፣ በደቡብ ክልል ቤንች ሸኮ ዞን ጉራፈርዳ ወረዳና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በንፁኃን ላይ የተፈጸመው ግድያ ሌላ ሐዘን መጨመሩ፣ ቤተ ክርስቲያኗን እጅግ ያሳዘነ ድርጊት በመሆኑ ሊወገዝ የሚገባው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

እንደ እግዚአብሔር ሐሳብ ሁሉም የዚህ ዓለም እንግዳ መሆኑን በመገንዘብ ተከባብሮ በወንድማማችነትና በአንድነት፣ በፍቅር መኖር እንዳለበትም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በተያያዘ ዜና የቤተ ክርስቲያኒቱ ቅዱስ ሲኖዶስ 39ኛ ጠቅላላ ምልዓተ ጉባዔ፣ በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ከኅዳር 1 እስከ 7 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ ለሰባት ቀናት ጸሎተ ምሕላ እንዲደረግ ውሳኔ አስተላለፏል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ ለ12 ቀናት ያደረገውን ጉባዔ ጥቅምት 23 ቀን ሲያጠናቅቅ ባሳለፈው ውሳኔ፣ በኢትዮጵያ እየታየ ካለው ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋ እግዚአብሔር ምሕረቱን እንዲያወርድ ምዕመናኑ ጸሎተ ምሕላ እንዲያደርጉ መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ በጉባዔው የተለያዩ ውሳኔዎችን ያስተላለፈ ሲሆን፣ በነባሩ ድንጋጌ ‹‹የቅዱስ ፓትርያርኩ ልዩ ሀገረ ስብከት›› የነበረችውና በረዳት ሊቀ ጳጳስ ትመራ የነበረችውን አዲስ አበባ ጉዳይ ተመልክቶ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡ በአዲሱ ድንጋጌ መሠረት አዲስ አበባ ከተማ በሊቀ ጳጳስ የሚመራ ሀገረ ስብከት እንዲኖራት ስምምነት ላይ መደረሱን፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ዮሴፍ አስታውቀዋል፡፡

የከተማዋ ሀገረ ስብከትን ለማዋቀርም ከሕግ ባለሙያዎች ጋር በመመካከርና ሕጉን አሻሽለው በግንቦት ወር ለሚካሄደው ረክበ ካህናት እንዲያቀርቡ፣ ሦስት ብፁዓን አባቶችን መመደቡንም ገልጸዋል፡፡

በሌላኛው ውሳኔውም በቤተ ክርስቲያኒቱና በክርስቲያን ወገኖች ላይ የደረሰው ግፍና መከራ እንዲቆም፣ በየምክንያቱ በክርስቲያንነታቸው ምክንያት የታሰሩ ካህናትና ምዕመናን ጉዳያቸው እየታየ ከታሰሩበት እንዲፈቱ፣ የመንግሥት የበታች ባለሥልጣናትም ለጥፋተኞች ከሚያደርጉት ድጋፍ እጃቸውን እንዲሰበስቡ ጉባዔው አጥብቆ አሳስቧል፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *