የፌደራል መንግስት በህወሃት ቡድን ላይ እየወሰደ ያለውን ህግ የማስከበር እርምጃ ተከትሎ፣ በትግራይ ክልል በየቀኑ በሺዎች እየተሰደዱ ሲሆን ሱዳን እስከ 2 መቶ ሺ ስደተኞች ለመቀበል ተዘጋጅቻለሁ ብላለች።
የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት፤ ግጭቱ ከተጀመረ ወዲህ  ባሉ 7 ቀናት ውስጥ የተፈጠሩ ሰብአዊ ቀውሶችን በተመለከተ ከትናንት በስቲያ ባወጣው ሪፖርት ዜጎች በክልሉ ግጭቶችን  እየሸሹ በሁለት አቅጣጫዎች ወደ ሱዳን እየተሰደዱ ነው ብሏል፡፡
እስከ ትላንት ድረስ ከ10 ሺህ በላይ ዜጎች ወደ ሱዳን ጋዳሪፍ ግዛት መሰደዳቸውን  ያስታወቀው ሪፖርቱ፤ የሱዳን መንግስት በበኩሉ፤ ከጥገኝነት ጠያቂዎቹ ጋር የታጠቁ ሃይሎች ድንበር እንዳያቋርጡ ጥብቅ ክትትልና ፍተሻ እያደረገ መሆኑ ተጠቁሟል።

ሱዳን እስከ 200 ሺ ስደተኞችን ለመቀበል ዝግጁ መሆኗን ገልጻለች

ግጭቱ የሚቀጥልና በአጭሩ የማይቋጭ ከሆነ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ 20 ሺ ገደማ ዜጎች ሊሰደዱ እንደሚችሉ የጠቆመው ሪፖርቱ፣ ጦርነቱ የሚራዘም ከሆነም በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ 100 ሺ ገደማ ስደተኞች ወደ ሱዳን መሰደዳቸው አይቀርም ብሏል – የተባበሩት መንግስታት ሪፖርት፡፡ በአሁኑ ወቅት በጦርነት ቀጠና ውስጥ በምትገኘው ትግራይ፤ የነዳጅ ዋጋ በ3 እና በ4 እጥፍ መጨመሩን፤ እንዲሁም የመድሃኒትና መሰረታዊ የምግብ አቅርቦት እጥረት እየተፈጠረ መምጣቱን የትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ የተመለከተው ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡ በአካባቢው የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡ መረጃዎች እንዳይገኙ እንቅፋት መሆኑን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ እንቅስቃሴዎች በመገደባቸው ሳቢያ ዜጎች በክልሉ  ያሉበትን ሁኔታ ዓለማቀፍ የረድኤት ሰራተኞች ማጣራትና ድጋፍ ማድረግ መቸገራቸው ተመልክቷል፡፡
በግጭት ውስጥ ያሉት የፌደራል መንግስትና የህወሓት ቡድን በንፁሃን ዜጎች ጉዳት እንዳይደርስ የበለጠውን ትኩረት እንዲሰጡና የከፋ ማህበራዊ ቀውስ እንዳይፈጠር ጥረት እያዲያደርጉ የተባበሩት መንግስታት አሳስቧል፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *