በትግራይ ክልል ያለውን ወታደራዊ ግጭት በመሸሽ በሺዎች የሚቆጠሩ የክልሉ ነዋሪዎች ወደ ጎረቤት አገር ሱዳን መሰደድ መቀጠላቸው ተገለጸ፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የስደተኞችና የሰብዓዊ ዕርዳታ አስተባባሪ ተቋም ሰሞኑን እንዳስታወቀው፣ በርካታ ኢትዮጵያውያን በትግራይ ካለው ወታደራዊ ግጭት ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ለማዳን፣ መኖሪያ ቀዬአቸውን ለቀው ወደ ሱዳን በመሰደድ ላይ መሆናቸውን አስታውቋል፡፡

በሱዳን የሚገኘው የዚህ ተቋም አስተባባሪዎች ከሱዳን መንግሥትና ሌሎች አጋር ሰብዓዊ ተቋማት ጋር በመሆን ስደተኞቹ በሱዳን መጠለያ እንዲያገኙ፣ ዕለታዊ ምግብና ውኃ በማቅረብ ላይ እንደሚገኝም አስታውቋል፡፡ እስከ ሐሙስ ኅዳር 3 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ ባሉት ጥቂት ቀናት ብቻ ከሰባት ሺሕ በላይ ነዋሪዎች ከትግራይ ክልል ወደ ሱዳን መግባታቸውን ያስታወቀ ሲሆን፣ አብዛኞቹም ሴቶችና ሕፃናት እንደሆኑ ጠቁሟል፡፡

 

ሱዳን ላልታጠቁ ስደተኞች በሯን ከፍታለች

 

ስደተኞቹ ሱዳንና ኢትዮጵያን በሚያዋስኑት ከሰላና ገደሪፍ አካባቢዎች በሚገኙ የስደተኛ ካምፖች ጊዜያዊ መጠለያ እንዲያገኙ መደረጉንም ገልጿል፡፡

በ24 ሰዓት ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ከትግራይ ክልል ወደ ሱዳን መግባታቸውን ያመለከተው ተቋሙ፣ በትግራይ ክልል እየተካሄደ ያለው ወታደራዊ ግጭት እየተባባሰ በመሆኑ የስደተኞች ቁጥር በእጅጉ ሊያሻቅብ እንደሚችልም አስታውቋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በትግራይ ክልል በሚገኙ አራት የስደተኞች መጠለያ ካምፖች 96 ሺሕ ኤርትራዊያን ተጠልለው የሚገኙ መሆኑን ገልጾ፣ በክልሉ ከአንድ መቶ ሺሕ በላይ የሆኑ ነዋሪዎች ጦርነቱ ከሚካሄድባቸው አካባቢዎች ተፈናቅለው መሸሻቸውን አስታውቋል፡፡

በትግራይ ክልል የተጠለሉ ኤርትራዊያን ስደተኞች ሁኔታና በዚያው ክልል ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ ኢትዮጵያውያን ሁኔታ እንዳሳሰበው በመግለጽ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ሰብዓዊ ዕርዳታ የሚሰጡ ተቋማት በትግራይ ክልል መንቀሳቀስ የሚችሉበትን ሁኔታ እንዲያመቻችም ጠይቋል፡፡

የሱዳን መንግሥት ቀደም ብሎ ከኢትዮጵያ በሚያዋስነው ድንበር ላይ ስድስት ሺሕ ተጨማሪ ጦር በማሥፈር ድንበሩን ዘግቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ የብሔራዊ ደኅነነት አማካሪ አድርገው በቅርቡ የሾሟቸውን አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን ወደ ሱዳን መላካቸው ይታወሳል፡፡

አቶ ገዱ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይን መልዕክት ለሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ካደረሱ በኋላ፣ የኢትዮጵያ አዋሳኝ የሆኑ የሱዳን ድንበሮች ክፍት እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡

የሱዳን መንግሥት ባወጣው መግለጫ በትግራይ ያለውን ሁኔታ ሸሽተው የሚመጡ ኢትዮጵያውያንን ሱዳን እንደምትቀበል፣ ነገር ግን የጦር መሣሪያ የታጠቁ ስደተኞችን ወደ ድንበሯ እንደማታስገባ አስታውቋል፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *