ባለፈው ሁለት አመት ተኩል ገደማ በህወኃት አቀናባሪነትና ተሳትፎ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ከ1500 በላይ ዜጎች በግፍ መገደላቸውን ያስታወቀው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ፤ በህወኃት ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ መቀጠሉን ጠቁሟል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ሰሞኑን በህወኃት ላይ እየተወሰደ ባለው እርምጃና በድርጅቱ  የወንጀል ሴራዎች ዙሪያ ባጠናከረው መረጃ መሰረት፤ ህወኃት ባለፈው ሁለት ዓመት ተኩል በተለያዩ ከባድ ወንጀሎች ውስጥ ሲሳተፍ መቆየቱ ታውቋል፡፡
መንግስት በደህንነት ተቋማቱና ሌሎች መንገዶች ባከናወነው ምርመራ፤፤ህወኃት በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ከተከሰቱ ግጭቶች፣ አሰቃቂ የሰዎች ግድያና ጭፍጨፋ እንዲሁም የዜጎች መፈናቀል ጀርባ የህወሃት እጅ እንዳለበት ተረጋግጧል ብሏል፡፡
በ2009 እና 2010 ዓ.ም ከሱማሌ ክልል በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች በማፈናቀል ብቻ ሳይሆን በክልሉ በተፈፀሙ አሰቃቂ ጭፍጨፋዎችና ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶችም ቀጥተኛ ተሳታፊ እንደነበር መግለጫው ያመለክታል፡፡
በሱማሌ ክልል ተቀስቅሶ በነበረው ሁከትና ብጥብጥ፣ እስከ-2 ሚ. የሚደርሱ ዜጎች መፈናቀላቸውን ከዚያም በኋላ በተፈጠሩ ተደጋጋሚ ሁከቶች በመቶዎች መገደላቸውና መፈናቀላቸው አይዘነጋም፡፡ ከ850 ሺህ በላይ ዜጎች የተፈናቀሉበትን የጌድዮ ጉጂ ግጭትም በማቀነባበር የህወኃት ረጅም እጅ እንዳለበት መንግስት ይፋ ባደረገው መግለጫ አስታውቋል።
በተመሳሳይ፤ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ይከሰቱ ከነበሩ ግጭቶች፣ አሰቃቂ የዜጎች ግድያና ጥቃት ጀርባ የህወኃት የግጭት ነጋዴዎች ሚና የጎላ መሆኑን በምርመራ መረጋገጡን ነው የመንግስት  መለከታ፡፡
በቅርቡ በደቡብ ክልል፣ ኦሮሚያና ቤንሻንጉል ውስጥ ለተቀሰቀሰው ሁከትና ብጥብጥ እንዲሁም ለተፈጸመው አሰቃቂ  የዜጎች ግድያም የህወኃት ረዝም እጅ እንዳለበት ተረጋግጧል፡፡ ባለፈው ሁለት አመት ተኩል በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ለተፈጸሙ  ግድያዎች፣ ማፈናቀሎችና ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች በሙሉ የህወት ቡራኬና አቀናባሪነት የተከናወኑ መሆናቸውን መግለጫው ይጠቁማል፡፡
ባለፈው ታህሳስ ወር ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱን በመጣስ በትግራይ ክልል  ህገወጥ ምርጫ ያካሄደው ህወኃት፤ ሀገሪቱን ለመበታተንና ለማተራመስ የተለያዩ እቅዶችን ነድፎ ሲንቀሳቀስ እንደነበረ የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች መገኘታቸውም ነው የተመለከተው።
ዘንድሮ በ2013 በኦሮሚያ በቤንሻንጉልና በደቡብ ክልል፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በብሔር ማንነታቸው ተለይተው በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸው ይታወቃል፡፡ ባለፉት ሁለት ወራት እንኳ በቤንሻንጉል ከ160 በላይ ዜጎች፣ በደቡብ ክልክ ጉራፈርዳ ከ30 በላይ እንዲሁም በኦሮሚያ ወለጋ ከ35 በላይ ዜጎች በብሔር ማንነታቸው ተለይተው በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውና በ10 ሺዎች ተፈናቅለው ለሰብአዊ ቀውስ መዳረጋቸው አይዘነጋም፡፡
በህወኃት ላይ የሚወሰደው የህግ የበላይነትን የማስከበር እርምጃ ከተጀመረ በኋላም በማይካድራ በአንድ ጀንበር በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ማንነታቸው ተለይቶ በአሰቃቂ ሁኔታ ጭፍጨፋ እንደተፈፀመባቸው መንግስት ያረጋገጠ ሲሆን አለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናልም፤በትግራይ ውስጥ በመቶዎች በሚቆጠሩ ሰዎች ላይ የጅምላ ጭፍጨፋ ስለመካሄዱ ማስረጃ እንዳለው ገልጻል፡፡
በቀን ሰራተኝነት ጭምር የተሰማሩ ንፁሃን በማይመለከታቸው ጉዳይ በጅምላ ስለ መጨፍጨፋቸው በቂ ማስረጃ አለኝ ያለው አምነስት፤ አፋጣኝ ምርመራ ተደርጎ የወንጀሉ ፈጻሚዎች በአስቸኳይ ለህግ እንዲቀርቡ  ጠይቋል፡፡ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ የአይን ዕማኞች ማነጋገሩን በተጨማሪም በሳተላይት ምልከታትም በየቦታው በርካታ አስክሬኖች ወድቀው መታየታቸውን ነው በሪፖርቱ ያመላከተው፡፡
የህወኋት ልዩ ሃይል ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም ሉግዲ እና ባናት በመከላከያ ሰራዊት መመታቱን ተከትሎ፣ ወደ ኋላ በማፈግፈግ፣ በነጋታጋው ህዳር 1 ቀን 2013 በማይካድራ የጅምላ ጭፍጨፋ መፈፀሙን ነው አምነስቲ ያስታወቀው፡፡
የተገደሉ ሰዎች አስክሬንም ማይካድራ ከተማ ንግድ ባንክ አቅራቢያ በብዛት መገኘቱንና ድርጊቱም በህወኋት ልዩ ሃይሎች መፈፀሙን ነው አምነስቲ ያስታወቀው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *