መልካም ስሙና ክብሩ የተጎዳበት (የሚጎዳበት) ማንኛውም የመንግሥት አስፈጻሚ አካል፣ ዘገባው በቀረበበት የመገናኛ ብዙኃን ላይ ያለ ክፍያ መልስ የመስጠት መብት ያለው ከመሆኑም ሌላ፣ በወንጀል ሕግ አንቀጽ 43 ድንጋጌ መሠረት በፍርድ ቤት ቅጣት የሚጣልበት በመሆኑ፣ የመረጃ ሕጉን የማክበርና የማስከበር ሕገ መንግሥታዊና ሞራላዊ ድርብ ኃላፊነት ስላለበት፣ መረጃ የመስጠት ግዴታ እንዳለበት የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም አሳሰበ፡፡

ተቋሙ በዋና ዕንባ ጠባቂ እንዳለ ኃይሌ ግዛው (ዶ/ር) ፊርማ ወጪ ባደረገው ምክረ ሐሳብ እንደገለጸው፣ የመንግሥት አስፈጻሚ አካል ለመገናኛ ብዙኃን መረጃ መከልከል አይችልም፡፡ መገናኛ ብዙኃን መንግሥታዊ አካላትንና የባለሥልጣናትን ወቅታዊ ሁኔታዎችን በመገምገምና ትርጉም ባለው ሁኔታ ተንትኖ ለሕዝብ መረጃዎችን አጠናቅሮ እንዳያቀርቡ መከልከል አይችልም፡፡ የተለያዩ ሐሳቦች እንዳያንሸራሽሩና እንዳያገኙ፣ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ የሕዝብ ዓይንና ጆሮ ሆነው የመሥራት ሙያዊ ግዴታቸውን እንዳይወጡ በሕግ ወይም በአስተዳደራዊ ውሳኔዎች ሰበብ እንቅፋት መፍጠር የሕግ መሠረት የለውም፡፡ በሕግ የተረጋገጠውንም የመረጃ ነፃነት መብት መጣስ መሆኑንም ገልጿል፡፡

አንድ የመንግሥት አስፈጻሚ አካል በመገናኛ ብዙኃን በቀረበ ፍሬ ነገር ዘገባ መልካም ስሙና ክብሩ ከተጎዳበት፣ ዘገባው በቀረበበት መገናኛ ብዙኃን ላይ ያለ ክፍያ መልስ መስጠት መብት እንዳለው የጠቆመው ዕንባ ጠባቂ ተቋም፣ መገናኛ ብዙኃኑም ያለ ክፍያ በነፃ ዕርማት የመሥራት (የማውጣት) ግዴታ እንዳለበት አስታውቋል፡፡ ያ ካልሆነ ግን ስሙና ክብሩ የተጎዳበት ባለሥልጣን በወንጀል ሕግ አንቀጽ 43 ድንጋጌ መሠረት ኃላፊ የሆነውን ሰው ወደ ፍርድ ቤት እንዲቀርብ በማድረግ ቅጣት እንዲወሰንበት ማድረግ እንደሚችልም ጠቁሟል፡፡

ተቋሙ ‹‹ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ ባለ ዕዳ አይቀበለውም›› እና ‹‹የሐሳብ ነፃነትና የመልካም ስም (ክብር) ተቃርኖ›› በማለት ባስተላለፈው ምክረ ሐሳብ እንዳስረዳው፣ የመረጃ ነፃነት መሠረታዊ የሰብዓዊ መብትና ለሁሉም መብቶች መከበር መሠረት ዓለም አቀፋዊ ዕውቅና ያገኘ ነው፡፡ በ1946 ዓ.ም. የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ በውሳኔ ቁጥር 59 (1) እንዳስታወቀው፣ መረጃ የማግኘት መብት መሠረታዊና ሰብዓዊ መብት ነው፡፡ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥትም በአንቀጽ 19 መደንገጉን ጠቁሞ፣ ኢትዮጵያ ፈርማ ባፀደቀቻቸውና የአገሪቱ የሕግ አካል ባደረገቻቸው የሲቪልና ፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን (ICCPR) አንቀጽ 19፣ እንዲሁም ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ (UDHR) አንቀጽ 19 መሠረት፣ ማንኛውም ሰው መረጃ የማግኘትና የመስጠት ነፃነት እንዳለው ተቋሙ አስታውሷል፡፡

የመረጃ ነፃነት ለማስፈጸም በታወጀው የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ ቁጥር 590/2000ም በግልጽ መደንገጉን ጠቁሞ፣ ማንኛውም የተፈጥሮና የሕግ ሰው ከማንኛውም መንግሥታዊ አካል መረጃ የማግኘት ነፃነት፣ የመጠየቅ፣ የማስተላለፍ፣ የመረጃውን ምንጭ የያዘ ሰነድ በማንኛውም የመንግሥታዊ አካል እጅ የሚገኝ መሆን አለመሆኑን ጠይቆ የማወቅ መብት እንዳለው ተቋሙ አስረግጦ ጠቁሟል፡፡ መንግሥታዊ ተቋማት በተቻለ ፍጥነትና በዝቅተኛ ወጪ መረጃውን ለጠየቀ አካል ተደራሽ ማድረግ እንዳለባቸው ገልጾ፣ የሕዝብን ጥቅም የሚመለከቱ መረጃዎችን በተለያዩ የተግባቦት ዘዴዎች ለሕዝብ ተደራሽ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለባቸውም አክሏል፡፡

የመንግሥት አካላት ግን በአዋጁ ከተደነገገው አግባብ ውጪ መረጃ የመስጠት ሥልጠናቸውን እንደሚገድብ ተደርጎ መተርጎም እንደሌለበት በአዋጁ አንቀጽ 12(3) በግልጽ ተደንግጎ ቢቀመጥም፣ ያንን ሲፈጽሙ እንደማይታዩ ተቋሙ ገልጿል፡፡

የመረጃ ነፃነት መሠረታዊ ግቡ የሕዝብ ተሳትፎንና ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤትነት ማረጋገጥና የአሠራር ግልጽነት፣ ተጠያቂነትና ውጤታማነት የሰፈነበት የመንግሥት አሠራርና መልካም አስተዳደርን ማጠናከር መሆኑ በአዋጁ መደንገጉን ተቋሙ አስታውቋል፡፡

የሕዝብን ጥቅም የሚመለከት መረጃ የማግኘት ልዩ መብት (ነፃነት) እና ሐሳብና መረጃን ያለ ቅድሚያ ምርመራ የማሠራጨት መብት በሕገ መንግሥቱ ተገቢውን ትኩረት ማግኘቱንም አስታውሷል፡፡ በአዋጅ ቁጥር 590/2000 አንቀጽ 4 (3) እና 14 (10ለ) ድንጋጌ መሠረት፣ ማንኛውም የመንግሥት አካላትና ባለሥልጣናት የመገናኛ ብዙኃን ማኅበራዊ ተግባራቸውን ለመወጣት ዜና ወይም መረጃ የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማሠራጨት፣ በልዩ ልዩ ጉዳዮች ላይ አስተያየት ወይም ትችት የማቅረብ ወይም በመንግሥት አካል ስለተከናወነ ወይም ሊከናወን በዝግጅት ላይ ስላለ ጉዳይ ሕዝብ በአስቸኳይ ሊያውቀው የሚገባ ከሆነ፣ መረጃውን በአፋጣኝ የማግኘት መብት ሰጥቷቸዋል፡፡ ያገኙትን መረጃ፣ አስተያይትና ሐሳብ በሕግ አግባብ በመረጡት የማሠራጫ ዘዴ ለሕዝብ ይፋ የማድረግ መብት እንዳላቸውም አክሏል፡፡ በመሆኑም የመንግሥት ባለሥልጣናት ለሕዝብ ክብር ሰጥቶ በሚመለከተው ጉዳይ ላይ የተጠየቀውን መረጃ ለመገናኛ ብዙኃን አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጥ እንደሚገባም አሳስቧል፡፡

መረጃ የመቀበልና የማሠራጨት መብት የግለሰብ መብት ወይም የሕዝብንና የአገርን ጥቅም ለመጠበቅ ሲባል በሕግ ገደብ የሚጣልበት መብት እንጂ፣ ፍፁማዊ መብት እንዳልሆነም ተቋሙ ገልጿል፡፡ በአዋጁ ከአንቀጽ 16 እስከ 26 ባሉት ድንጋጌዎች መጠበቅ ስለሚገባቸው መረጃዎች (ገደቦች) በዝርዝር መቀመጣቸውን ጠቁሞ፣ እነሱም ቢሆኑ ከሕዝብ ጥቅም አንፃር እየተመዘኑ ተግባራዊ ሊደረጉ እንደሚገባ አዋጁ ደንግጓል፡፡

መገናኛ ብዙኃን የሕዝብ ዓይንና ጆሮ በመሆን መንግሥታዊ አካላትንና ባለሥልጣናትን አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴ በትክክለኛ መረጃና ማስረጃ አስደግፈው ለሕዝብ ማቅረብ ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና ያገኘ መብት መሆኑንም ጠቁሟል፡፡ መንግሥታዊ አካላትን ወይም የባለሥልጣናትን ደካማ ጎንና ብልሹ አሠራር ጭምር ለሕዝብ ተደራሽ ማድረግም የመገናኛ ብዙኃን ተግባር መሆኑን ተቋሙ ገልጿል፡፡

መንግሥት የመረጃ ነፃነት መብትን የማክበር (Duty to Respect)፣ የመጠበቅ (Duty To Protect) እና የመፈጸም (Duty to Fulfill) ኃላፊነትና ግዴታ እንዳለበት ጠቁሞ፣ በሚተላለፈው መረጃና ሐሳብ ውስጥ ጣልቃ አለመግባት፣ ለመረጃ ነፃነት ጥበቃ የማድረግና በእጁ የሚገኙ መረጃዎችን የመስጠትና ዜጎች መረጃ ማግኘት እንዲችሉ ምቹ ሁኔታዎች የመፍጠር ኃላፊነትና ግዴታም እንዳለበትም አስታውቋል፡፡

መረጃ ከማሠራጨት ጋር በተያያዘ በግለሰብና በመገናኛ ብዙኃን ላይ ገደብ የሚጥለው የወንጀል ሕግ መሆኑን ጠቁሞ፣ በመገናኛ ብዙኃን እንዳይገልጽ በሕግ ወይም በግልጽ በተሰጠው ውሳኔ የተከለከለ ካልሆነ በስተቀር፣ በአስተዳደር ባለሥልጣኖች እውነተኛና ትክክለኛ ክርክሮች ወይም ውሳኔዎችን በተመለከተ መረጃ ለሕዝብ ይፋ ማድረግ በወንጀል የሚያስቀጣ ወይም ያልተከለከለ መሆኑን በወንጀል ሕግ አንቀጽ 47 መደንገጉን አስታውሷል፡፡ ያልተረጋገጠና ተገቢውን ጥረት ሳያደርጉ በሐሰተኛ መረጃ ወይም ጥላቻ አዘል ንግግርን ማሠራጨት መከልከሉንም አክሏል፡፡ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የአስተዳደር አካላትና ባለሥልጣናት እውነተኛና ትክክለኛ ክርክሮች በመገናኛ ብዙኃን መሠራጨት እንዳለባቸው ደጋግሞ አስታውቋል፡፡

ዘገባው የጥሬ ሀቅ ዘገባ ወይም ዜና ከመሆን ይልቅ ወደ ፖለቲካ አስተያየትና ትችትነት ያጋደለ ከሆነ፣ የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭት ሊባል እንደማይገባ፣ የጥላቻ ንግግርንና ሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትን ለመከላከል በወጣው አዋጅ ቁጥር 1185/2012 አንቀጽ 6(2) እና በፍትሐ ብሔር ሕግ አንቀጽ 2046 ድንጋጌዎች መሠረት በስም ማጥፋት እንደማያስጠይቀው መደንገጉን ተቋሙ ገልጿል፡፡

የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት ከተራ ዜጎች ይልቅ የመገናኛ ብዙኃን በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጡ መሠረታዊ ነፃነቶች (መብቶች)፣ መከበር፣ ለሰላም፣ ለእኩልነት፣ ለፍትሕና ለዴሞክራሲ የቆሙ መሆናቸውን በመረዳት፣ መገናኛ ብዙኃን ለመንግሥታዊ አካላት መረጃ እንዲያገኙ፣ ትክክለኛና ሚዛናዊ መረጃን እንዲያሠራጩ መፍቀድና ሕጋዊና ተቋማዊ ጥበቃ የመስጠት ኃላፊነት እንዳለባቸው ዕንባ ጠባቂ ተቋም አስታውቋል፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *