የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ከወገንተኛነት ዜና ጥንቅርና ያለ በቂ መረጃ ከመዘገብ አባዜ መውጣት እንዳላባቸው ተጠየቀ፡፡

ባለፈው ሳምንት፣ ‹‹የሰላም ጋዜጠኝነት በኢትዮጵያ፣ ዴሞክራታይዜሽንና የሚዲያ ሚና›› በሚል ርዕስ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የውይይት መድረክ አዘጋጅቶ ነበር፡፡

በውይይቱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ሙላት ዓለማየሁ (ዶ/ር) ባቀረቡት ጽሑፍ፣ በኢትዮጵያ ጋዜጠኞች አብዛኛውን ጊዜ ከአንድ ዓይነት ዕሳቤና ምንጭ የተቀዱ ይመስል ዘገባዎቻቸው ሕዝብን ማዕከል ያደረጉና ተገቢ የሆነ ማጣቀሻ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ሲያጠናቅሩ አይታዩም፡፡ የበሰለ ዜና ማስደመጥም እንደሚሳናቸው አመልክተዋል፡፡

በአገሪቱ ከ60 በላይ ቋንቋዎች ለጋዜጠኝነት ሥራ እንደሚውሉ የጠቆሙት ጽሑፍ አቅራቢው፣ አብዛኞቹ ሚዲያዎች ግን ለኅብረተሰቡ ሚዛናዊ ዜና ማድረስ የተሳናቸው፣ ከዚያም ሲያልፍ የተጋነኑና ‹‹እኛ›› እና ‹‹እነሱ›› በሚሉ የጥላቻ ንግግሮች የተሞሉ ዘገባዎችን እንደሚያስተጋቡ አስረድተዋል፡፡

በውጫዊና በውስጣዊ ጫና ምክንያት ከሚመጣው ወገንተኝነት በተጨማሪ፣ ለሙያው ሥነ ምግባር ተገዥ ካለመሆን የተነሳ እየታየ ያለው ሚዛናዊ ያለመሆን ችግር በአጭሩ መቀጨት እንዳለበት የገለጹት ዶ/ር ሙለታ፣ ችግሩ በዚህ ከቀጠለ በማኅበረሰብ ደረጃ መተማመንን አይኖርም ብለዋል፡፡ በአገር ደረጃ ደግሞ ሚዲያው ለሚታሰበው የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መወጣት ያለበትን ሚና ሳይጫወት፣ መሀል ላይ ይቀራል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው ድንቁ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በጋዜጠኞች የሚታየውን የሚዛናዊነት ችግር በተለይ ሰሞኑን በአገሪቱ ከተከሰተው ችግር ጋር አያይዘው ሲገልጹ፣ ጋዜጠኞች አንድም ከሙያ ክህሎትና ሥነ ምግባር የተነሳ፣ በሌላ በኩል ደግሞ እየተደረገ ያለው ነገር ትክክል ነው ብሎ ለአንዱ ወገን ብቻ ሚዛን ከመስጠት የመነጨ ነው ብለዋል፡፡

በሌላው ተቋም ውስጥ እንደሚታየው ለሕግ ተገዥ ያለ መሆን ችግር በሚዲያው ዘርፍ መስተዋሉ የተለየ አለመሆኑን በመጠቆም፣ በርከት ያሉ ሚዲያዎች አሁን ካሉበት ፖለቲካን እንደ ዋና አጀንዳ ይዞ ከማራገብ በመቆጠብ በሌሎች ኅብረተሰቡን ሊጠቅሙ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ሊያተኩሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግሥት ለሚዲያው ዘርፍ የተሻለ ነፃነት ሰጥቷል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ቀደም ሲል ሲታይ የነበረው ጋዜጠኞችን ማዋከብ በእጅጉ ቀንሷል ሲሉም አክለዋል፡፡

በሚዲያው ዘርፍ ለመሰማራት ፈቃድ የሚጠይቁ አካላት ሐሳቦቻቸው ምንም እንኳን በጥሩ ቋንቋና ቃላት ተሸፍነው የሚመጡ ቢሆንም፣ ፈቃድ ከወሰዱ በኋላ ግን አቅጣጫቸውን እየቀየሩ የማይታወቅና ከተፈቀደው አሠራር ውጪ ሆነው ይገኛሉ ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ እንዲህ ዓይነት ችግሮች በጊዜ ሒደት ሊፈቱ እንደሚችሉ አስረድተዋል፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *