ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ግለሰቦች የተለያዩ ጥቅሞች ለማግኘት ሲሉ የሃሰት አካውንት በመክፈት ድብቅ አጀንዳቸውን ሲያራምዱ ማስተዋል እየተለመደ መጥቷል፡፡ ይህ ደግሞ ከፍተኛ ተከታይ በሚኖራቸው የተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ ትስስር ገፆች ላይ እጅግ ጎልቶ ይታያል፡፡አብዛኞቹ እነዚህ ያልተረጋገጡ የሚዲያ ምንጮች ለገቢያቸው መደለብ ሲሉ ብቻ የተሳሳቱ መረጃዎችን ለማህበረሰቡ በማቅረብ ብዙዎችን ለአደጋ ማጋለጣቸው የአደባባይ ሚስጥር ከሆነ ቆይቷል፡፡

ኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ጋር ተያይዞም እነዚህ የተሳሳቱ የመረጃ ቅብብሎች ከመቼውም ጊዜ ባላይ እየጨመሩ የመጡ ሲሆን በዚህ ጉዳይ የተሰሩ አብዛኞቹ ጥናቶችም ከወረርሽኙ እኩል ህዝቡን እያሸበሩት የሚገኙት ጉዳዮች እነዚሁ ያልተረጋገጡ የመረጃ ምንጮች እንደሆኑ አሳይተዋል፡፡ ከሰሞኑ በእንግሊዝ የተደረገው ተመሳሳይ ጥናት እንዳመለከተው ካልተረጋገጡ የማህበራዊ ትስስር ገፆች የሚገኙ ዘገባዎችን ዋና የመረጃ ምንጫቸው ያደረጉ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች የሴራ ትንተና (conspiracy) የበዛባቸውን መረጃዎች በይበልጥ እያመኑ መምጣታቸውንና በዚህም የተለያዩ የመንግስታትን የጤና መመሪያዎች እየጣሱ እንደሚገኝ በጥናቱ ይፋ አድርጓል፡፡

በእንግሊዝ መቀመጫቸውን ባደረጉ ኪንግ ኮሌጅ እና Ipsos Mori የምርምር ማዕከል የተሰራው ይህ የዳሰሳ ጥናት በጥቅሉ 2,000 ሰዎችን በጥናቱ አሳትፎ የተለያዩ መጠይቆችን ለተሳታፊዎቹ አቅርቦ ነበር፡፡ ይህ የምርምር ቡድን ካቀረባቸው መጠይቆች መካከል የኮሮናቫይረስ በላብራቶሪ ውስጥ የተፈጠረ ነው የሚለው እንደኛው ጥያቄ ሲሆን ከተሳታፊዎቹ 30 በመቶ የሚሆኑት በዚህ የሴራ ትንተና የሚያምኑ እና በዚህም የተነሳ እርምጃዎችን እየጣሱ እንደሚገኝ በጥናቱ ታይቷል፡፡ ከዚህ ባለፈ በጥናቱ እንደተገለፀው ተመሳሳይ ቁጥር ያላቸው የጥናቱ ተሳታፊዎች በኮሮናቫይረስ ህይወታቸውን የሚያጡ ሰዎች ትክክለኛ ቁጥራቸው እንዳይታወቅ መንግስታት ይደብቃሉ የሚለውን መጠይቅ በስፋት እንደሚያምኑ በጥናቱ ተዳሷል፡፡

13 በመቶ የሚሆኑ የጥናቱ ተሳታፊዎች ወረርሽኙ የአለም ሰዎችን በክትባት ለመቆጣጠር የተዘየደ ሴራ ነው ብለው የሚያምኑ ሲሆን፤ 8 በመቶ የሚሆኑት የጥናቱ ተሳታፊዎች ደግሞ የኮሮናቫይረስ ምልክቶች በአንድም ይሁን በሌላ ከ5G ራዲዬሽን ጋር የጠበቀ ግንኙነት አላቸው ብለው የሚያምኑ ናቸው፡፡ በዚህ የዳሰሳ ጥናቱ ለመታዘብ እንደተቻለው ብዙ ሰዎች መሰል የኮኒስፓይሪሲ ዘገባዎችን በስፋት እንዲቀበሉ ያደረጋቸው ይፋዊ የጤና ምክሮችን የሚያገኙበት የመረጃ ምንጭ ከመፈለግ ይልቅ ብዙ ያልታመኑ የማህበራዊ ሚዲያ አማራጮችን ዋና የመረጃ ምንጭ በማድረጋቸው ነው፡፡ በተለይም ከፌስቡክ እና ከዩቲዩብ የሚገኙ ያልታመኑ የመረጃ ምንጮች ለእነዚሁ የተዛቡ የኮኒስፓይሪሲ ዘገባዎች ዋና መደላድል ናቸው፡፡

ወረርሽኙን ከመከላከል እኩል መረጃዎች የሚሰራጩበትን ሁኔታ በሚገባ መከታተል ያስፈልጋል የሚሉት የጥናቱ ዋና መሪ ዶ/ር ዳንኤል አሊንግቶን ቤት የመቀመጥ መመሪያዎችን እና ሌሎች  እርምጃዎችን በምናስተላልፍበት መጠን ግልፅና ጥራት ያላቸው መረጃዎችን ለሰዎች እንዲደርስ ማድረግ ቀዳሚ ስራ ሊሆን ይገባል ይላሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይ እንደ ቲቪ እና ራዲዮ ያሉ የመረጃ ማስተላለፊያ መንገዶች ትልቅ ሚና የሚኖራቸው ቢሆንም ወጣቱ የሚመርጣቸው የማህበራዊ ትስስር ገፆች ለአደጋው መባባበስ ትልቅ እድል እንደሚፈጥሩ በጥናቱ ተዳሷል፡፡ ለምሳሌ በዚህ እይታ በጥናቱ ከተሳተፉ አጠቃላይ ሰዎች 45 በመቶ (ብዙዎቹ ከ16 እስከ 24 እድሜ) የሚሆኑት ዋና የመረጃ ምንጫቸው ያልታመኑ ዩቲዩብ ቻናሎች ሲሆን፤ ሌሎች 40 በመቶውን የሚሸፍኑት ደግሞ (ብዙዎቹ ከ30 በታች) ዋና የመረጃ ምንጫቸው ከፌስቡክ እንደሆነ በጥናቱ ተመልክቷል፡፡

ምንጭ፡ bigthink.com

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *