ባለፉት ወራቶች የሳይበር ደህንነት ማስገንዘቢያ መርሃ ግብሮች ሲካሄዱ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡ በተለይም የጥቅምት ወር ይህን የግንዛቤ ስራ ለማካሄድ በተደጋጋሚ ጥቅም ላይ ስትውል ተመልክተናል፡፡ ይህን በማከናወን ሂደት ግዙፉ የጎግል ኩባንያ በቀዳሚነት የሚጠቀስ ድርጅት ሲሆን በአሰራር ፕሮቶኮሉም የበይነ-መረብ ተጠቃሚዎች ደህንነታቸው በተጠበቀ መልኩ ስራቸውን እንዲያከናውኑ ትልቅ እገዛ ያደርጋል፡፡ እነዚህ የምትመለከቷቸው የጎግል የደህንነት ማሻሻያ አማራጮች በኢንተርኔት ላይ የሚኖረንን እያንዳንዷን እንቅስቃሴ ከማስጠበቅ አልፎ ለስራችን መሳካትም ትልቅ ሚና ሊኖራቸው ስለሚችል በሚገባ ማየቱ ጠቃሚ ነው፡፡
፩. በአይነታቸው የተለዩ እና ለመገመት አስቸጋሪ የሆኑ የይለፍ ቃሎችን ለመፍጠር የጎግልን የይለፍ ቃል አስተዳደር (password manager) መጠቀም የመጀመሪያው የጥንቃቄ መንገድ ነው፡፡
፪. በዴስክቶፕ እና በሞባይል የኦፕሬቲንግ ስርዓቶች የሚጫኑ የድር ማሰሻ (web browser) መተግበሪያዎች ምንግዜም የመጨረሻው ማዘመኛ (up-to-date) የተደረገላቸው መሆን አለባቸው፡፡ ይህ ደግሞ የምንጠቀማቸውን የኦንላይን ቴክኖሎጂዎች ከደህንነት ስጋት ውጭ ያደርጋቸዋል፡፡
፫. ስልካችን ጠፍቶ ቢገኝና በፍፁም የማናገኝበት ሁኔታ ቢፈጠር በጎግል አካውንታችን አማካኝነት ( myaccount.google.com.) በመግባት ከየኛውም ቦታ ሆነን ስልካችንን መቆለፍ እና ሚገኝበትን አካባቢ መረዳት እንችላለን፡፡
፬. የበይነ መረብ አገልግሎት ስንጠቀም የግል መረጃዎቻችንን የሚያጠምዱ የተለያዩ ድረ ገፆች ሊያጋጥሙን ይችላሉ፡፡ እነዚህ የመረጃ አጥማጆች በተከታታይ የሚቀርቡልንን ጥያቂዎች በንቃት መከታተል አንደኛው የመጠበቂያ መንገድ ሲሆን፤ ከዚያ በለፈም በመተግበሪያችን (browser) ላይ ሊጫኑ ወይም (extended) ሊደረጉ የሚችሉ መሳሪያዎችን በማከል ችግሩን ማስቀረት አንችላለን፡፡ በዚህ አንፃር የጎግል ሳይቶች ያልሆኑ (non-Google site) አድረሻዎች ላይ የይለፍ ቃል ስናስገባ ማስጠንቀቂያ የሚልክልን እንደ (Password Alert extension) ያለ መሳሪያ በመተግበሪያችን ላይ መቀላቀል እንችላለን፡፡
፭. አንዳንድ ጊዜ የመረጃ መንታፊዎች ወይም ሃካሮች የኛኑ የመጠቀሚያ ስም (username) እና የይለፍ ቃል በአካውንታችን ላይ በማስገባት አጠቃላይ መረጃችንን ሊሰርቁና ሊያጠቁን ይችላሉ፡፡ ይህ ሊሆን የሚችልበት ምክንያት የተለያየ ቢሆንም አብዛኛውን ጊዜ ግን የጠነከረ የይለፍ ቃል ሳይኖር ሲቀርና የተለያዩ ማዘመኛዎች ሳናደርግ ስንቀር ነው፡፡ አነዚህ የአጠቃቀም ክፍቶች ብዙዎቻችን ላይ የሚስተዋሉ ቢሆንም ካዛ ባለፈ በስራቸው ላይ ከፍተኛ ስጋት ያለባቸው ሰዎች ግን በጎግል አካውንት ላይ (security.google.com) በመግባት የሁለተኛ ደረጃ ማረጋገጫ (2-Step Verification) በማስቻል እያንዷንዷን እንቅስቃሴያቸውን መመልከት ይኖርባቸዋል፡፡
፮. አሁን አሁን ከየትኛውም የማህበረሰብ ክፍል በላይ የፖለቲካ መሪዎች እና የማህበረሰብ አክቲቪስቶች ለሳይበር ጥቃት እጀግ ተጋላጭ እየሆኑ መምጣቸው የሚታወቅ ነው፡፡ ታዲያ አንደዚህ አይነት ግለሰቦችና ሌሎች ከፍተኛ የሳይበር ስጋት ያለባቸው አካላት ጎግል የሚያቀርበውን የላቀ የጥበቃ መርሃ-ግብር (Advanced Protection Program) መጠቀም ይችላሉ፡፡ ይህ ፕሮግራም መረጃ አጥማጆችን በሚገባ ለመከላከል የሚጠቅም ሲሆን በታመኑ መተግበሪያዎች ላይ የኔትወርክ አጠቃቀችንን ለመገደብ እና አካውንታችንን አጭበርብረው ለሚጠቀሙ ሃከሮችም ጥሩ መፍትሄ ነው፡፡
፯. አብዛኛውን ጊዜ በስልካችን የምናወርዳቸው ምንጫቸው ያልታመነ መተግበሪያዎች ለየትኛውም የሳይበር ጥቃት በቀላሉ ሊያጋልጡን ይችላሉ፡፡ ከጎግል ፕለይ ያወረድናቸው መተገበሪያዎች እንኳን አልፎ አልፎ መሰል ስጋት ስለሚኖርባቸው የጎግል ፕለይ ጥበቃ ላይ (Google Play Protect) የደህነት ፍተሻ መድረግ እጅግ ተመራጭ ይሆናል፡፡
፷. በጎግል የበይነ መረብ አጠቃቀማችን ላይ እያንዷንዷን እንቅስቃሴያችንን በየጊዜው ለመፈተሸና ለመከታተል የጎግልን (Security Checkup) በቀላሉ መጠቀም እንችላለን፡፡ ይህ ሲስተም የጎግል አካውንታችንን ደህንነት ለመተንተን እና ያጋጠሙ ችግሮችንም በቀላሉ ለመፍታት የሚያገለግለን ነው፡፡
፱. ምንግዜም ቢሆን የህዝብ ወይም ነፃ የዋይፋይ ኔትወርኮችን ስንጠቀም በምላሹ ሊኖር ስለሚችለው የደህንነት ስጋት መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ የዋይፋይ ኔትወርኩ የይለፍ ቃል የታከለበት ቢሆንም እንኳን መረጃዎቻችንን አሳልፎ እንዳይሰጥ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
፲. ከእነዚህ ጥንቃቄዎች በተጨማሪ በጎግል አካውንታችን ላይ የደህንነት ቁልፍ (security key) በማዋቀር አጠቃላይ የበይነ መረብ አንቅስቀሴያችንን ማስጠበቅ እንችላለን፡፡
ምንጭ፡ Gadgets Africa