የመገናኛ ብዙኃን ማሠራጫዎች ከዘመኑ ጋር እየዘመኑና ተጠቃሚዎችም በቀላሉ ለመጠቀም የሚችሉበት እየሆኑ መጥተዋል፡፡ በኢትዮጵያ በተለይም የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ተጠቃሚዎች አብዛኛዎቹ ወጣቶች በመሆናቸው ይታወቃል፡፡ በዚህ የማኅበራዊ ትስስር ገጽ በተለያየ መንገድ ትክክለኛ የሆነ መረጃም ሆነ ኃላፊነት የጎደለው መረጃም ግላዊ ሐሳብ ታክሎበት ይሠራጫል፡፡
በቅርቡ እንኳን ከመገናኛ ትስስር ገጾች መካከል በፌስቡክ አስቂኝ (Memes) እየተባለ የተለያዩ መልዕክት ያላቸው የግለሰብ ሐሳቦች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተከታይ እያፈሩ ይገኛሉ፡፡
አስቂኝ ገጾች ምንም እንኳን ፈገግ የሚያስብሉ ቢሆኑም፣ በአንድም ሆነ በሌላ በኩል የጎንዮሽ ጉዳት ሊያስከትሉ እንደሚችሉ ይታመናል፡፡ አስቂኝ ገጾች ብዙውን ጊዜ የሚጠቀሙት ፎቶዎች በማኅበረሰቡ ታዋቂ የሆኑ ሰዎችን ነው፡፡ ለፎቶዎቹ ባለቤቶችም ቢሆን ተፅዕኖ እያመጣባቸው መሆኑ የሚታይ እውነታ ነው፡፡ ምንም እንኳን አስቂኝ ገጾች የሚያስቁና የሚያስገርሙ ቢሆንም ከግለሰቦች በጎ ጎን በበለጠ ችግሮቹን አጉልተው የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ከበጎ ነገርና ከማሳቅ በበለጠ አብዛኛው በሚባል ደረጃ በጎ ባልሆነ ነገር አዘል ቀልድ የተሞላ ነው፡፡ በምሳሌነት ፌስቡክ ተነሳን እንጂ ቲውተር፣ ቴሌግራም፣ እንዲሁም በቅርቡ ኢትዮጵያውያን ታዳጊዎችና ወጣቶች ዘንድ ተወዳጅ የሆነው ‹ቲክ ቶክ›ም ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ዋናው ችግር በአስቂኝ መልክ የሚቀርቡት መልዕክቶች ተለምደው ሁልጊዜም እንደ መደበኛ የሕይወት አካልና በጎ ነገር የሚታዩበት እንዳይሆን ሥጋት የሆነባቸውም አሉ፡፡
መገናኛ ብዙኃን በወጣቶች ላይ አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ ተፅዕኖ ማሳደራቸው ቢታመንም በዋናነት ችግሮቹ የበዙ ናቸው፡፡ እነዚህ ችግሮች ግለሰቡ ጋ ሲመጣ ከሚኖረው መልዕክት ጋር ተያያዥ ነው፡፡ አንድ ሚዲያ የሚያሠራጨው ማንኛውም ዘገባ ከሁሉም ማዕዘን ሆነው የሚያዩ ጥቂቶች ናቸው፡፡
የመገናኛ ብዙኃን አጠቃቀም ላይ በኢትዮጵያ ብዙም እንዳልተሠራበት ይነገራል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ በቅርቡ የኢትዮጵያ ወጣት ወንዶች ክርስቲያን ማኅበር (ወወክማ) በሚዲያ አጠቃቀም የላቁ የኢትዮጵያ ወጣቶች ንቅናቄ መጀመሩን አሳውቋል፡፡ ዓላማው የወጣቶችን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ዴሞክራሲያዊና የዜግነት ተሳትፎ በትክክለኛው መንገድ ራሳቸው ወጣቶች በሚዲያ እንዲያራምዱ ለማድረግ ነው፡፡ በዚህ ብቻ ሳይወሰን ወጣቶች በጤና፣ በትምህርት፣ በፆታ እኩልነትና በአካባቢ ጥበቃ እንዲሁም በሰላምና ዴሞክራሲ ግንባታ ላይ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉም ያግዛል፡፡ ንቅናቄው በዋናነት ወጣቶች በመረጃ የዳበሩ፣ የሚያገኙትን መረጃ የሚፈትሹ፣ በሚዛናዊነትና በከፍተኛ ኃላፊነት መረጃን የሚቀበሉና የሚከፍሉ እንዲሆኑ የማድረግ ግብ አለው፡፡
የንቅናቄው አንዱ አካል የሆነው የሚዲያ አጠቃቀም የላቁ ወጣቶች በሚሠራጨው መረጃ ይዝናናሉ፣ ይመረምራሉ፣ ይፈጥራሉ፣ እንዲያውም መብታቸውን ተጠቅመው ሐሳብ ይገልጻሉ የሚለው ይገኝበታል፡፡ የወወክማ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳግማዊ ሰላምሳ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ወጣቶች ከመገናኛ ብዘኃን የሚያገኙትን መረጃ በምን መልኩ ማጣራት እንዳለባቸው፣ እንዲሁም ራሳቸው የሚያሠራጩትን መረጃዎች ኃላፊነት በተሞላበት መልኩ እንዲያሠራጩ የማድረግ እንቅስቃሴ ነው፡፡
ወጣቶች በሚዲያ አጠቃቀም የላቁ እንዲሆኑ ለማድረግ አንድን መልዕክት በአምስት ተደራራቢ ሌንሶች (ማሳያዎች) መመርመር አለባቸው የተባሉ ሲሆን፣ እነዚህም፣ የመረጃውን ይዘት፣ ግብ፣ አዘጋጅና አቅራቢ፣ ታዳሚው፣ እንዲሁም አቀራረብን የሚመለከቱ ናቸው፡፡ የሚሠራጩ መረጃዎችን ማጤንና መመርመር ባህል ማድረግ የንቅናቄ አንዱ ግብ ነው፡፡
ንቅናቄው ከጽንሰ ሐሳብ ጀምሮ በማኅበራዊ ትስስር ገጽ ብቻ የተወሰነ የመሰላቸው እንደነበሩ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ በሁሉም የሚዲያ አካላት ላይ የሚገኙ መረጃዎች ላይ ያተኮረ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
‹‹በሚዲያ አጠቃቀም የላቁ ወጣቶችን በኢትዮጵያ እንፍጠር›› የሚለው ንቅናቄ ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም. በይፋ መጀመሩን የወወክማ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳግማዊ ገልጸው፣ ወጣቶች የሚዲያ አጠቃቀማቸው በኃላፊነትና በዕውቀት ላይ በመመሥረት ያሉት ችግሮች መቀነስ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የሚዲያ አጠቃቀም የላቁ ወጣቶች ኢትዮጵያ ንቅናቄ ውስጥ ሕይወት ኢትዮጵያ፣ ማኅበረ ሕይወት ለማኅበራዊ ዕድገት የሚባሉትን ጨምሮ ዘጠኝ የሲቪል ማኅበራት ያሉበትና ከመንግሥት ተቋማት ጋር በትብብር ለመሥራት እንቅስቃሴ መጀመሩን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡