አምነስቲ ኢንተርናሽናል በትግራይ ክልል ውስጥ  በርካታ ሰዎች የተገደሉበት ጥቃት መፈጸሙን የሚያመለክቱ ማስረጃዎች እንዳገኘ ገለጸ።

የሰብአዊ መብቶች ተቆርቋሪው ድርጅት እንዳለው በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ በምትገኘው ማይካድራ ከተማ ውስጥ በተፈጸመው በዚህ ጥቃት ቁጥራቸው በመቶዎች ሊቆጠሩ የሚችሉ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ በስለት ተገድለዋል።

ድርጅቱ ከማይካድራ ከተማ የወጡና በየቦታው ወድቀው የሚታዩ አስከሬኖችን የሚያሳዩ አሰቃቂ ፎቶግራፎችንና ቪዲዮዎችን በመመርመር ምስሎቹ የቅርብ ጊዜና ስፍራውም ማይካድራ መሆኑን ለማረጋገጥ መቻሉን ገልጿል።

ጨምሮም በጥቃቱ የተገደሉት ሰዎች ተዋጊዎች ሳይሆኑ ሰላማዊ ሰዎች መሆናቸውን ጠቅሶ፤ ግድያውን ማን እንደፈጸመው ለማረጋገጥ አለመቻሉን አመልክቷል። ነገር ግን ያነጋገራቸው እማኞች ከፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ጋር የሚዋጉትን የህወሓት ታማኝ ኃይሎች ጥቃቱን እንደፈጸሙ ይከሳሉ።

በአገር መከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ ተፈጸመ የተባለውን ጥቃት ተከትሎ ለወራት በውዝግብ ውስጥ የቆዩት የፌደራል መንግሥት እና የትግራይ ክልል አስተዳደር ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ወደ ግልጽ ጦርነት መግባታቸው ይታወሳል።

በአሁኑ ሰዓት ወደ ጦርነት የተሸጋገረው በፌደራል መንግሥቱና በትግራይ ክልል መስተዳደር በኩል የነበረው ቅራኔ እየተባባሰ የመጣው ባለፈው ዓመት ሊካሄድ የታቀደው ምርጫ በኮሮናቫይረስ ስጋት ምክንያት እንደማይካሄድ ከታወቀ በኋላ በትግራይ የተናጠል ምርጫ በመደረጉ ሳቢያ ነው።

በማይካድራ ከተማ የተፈጸመውን ግድያ በተመለከተ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያወጡትን መግለጫ ተከትሎ የትግራይ ክልል ባለስልጣናት በድርጊቱ የህወሓት ኃይሎች እጃቸው አለመኖሩን ገልፀው ነበር።

“በርካታ ቁጥር ያላቸውና እየተካሄደ ካለው ወታደራዊ ጥቃት ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የሌላቸው ሰላማዊ ሰዎች ላይ ግድያ መፈጸሙን አረጋግጠናል። በትግራይ ውስጥ ያለው የግንኙነት ዘዴ ዝግ በመሆኑ የዚህ አሰቃቂ ድርጊት ትክክለኛ መጠን በጊዜ ሂደት የሚታወቅ ይሆናል” ሲሉ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምሥራቅና ደቡብ አፍሪካ ዳይሬክትር የሆኑት ዴፕሮስ ሙቼና ተናግረዋል።

አምነስቲ ኢንትርናሽናል በማይካድራ ስለተፈጸመው ነገር ለማረጋገጥ ከጥቃቱ በኋላ ወደስፍራው የሄዱ እማኞችን ያነጋገረ ሲሆን በከተማዋ ውስጥ በየቦታው የወደቁ አስከሬኖችንና ከጥቃቱ ቆስለው የተረፉ ሰዎችን እንደተመለከቱ ተናግረዋል።

አብዛኞቹ አስከሬኖችም የተገኙት በከተማዋ ማዕከላዊ ክፍል ውስጥ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሚገኝበት አካባቢና በአቅራቢያ ወደ ምትገኝ የሁመራ ከተማ የሚያመራውን መንገድ ተከትሎ መሆኑን የአይን እማኞችና የተገኙት ምስሎች አመልክተዋል።

አምነስቲ ኢንትርናሽናል በመግለጫው ላይ ግድያውን ማን እንደፈጸመው ለማረጋገጥ ባይችልም፤ ያነጋገራቸው የአይን እማኞች ግን በፌደራሉ ሠራዊት ሽንፈት የገጠማቸው “ለህወሓት ታማኝ የሆኑ ኃይሎች ለግድያው ተጠያቂ እንደሆኑ ይናገራሉ” ብሏል።

“የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ይህንን ግልጽ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት በጥልቀት፣ በገለልተኝነትና በግልጽ መርምረው ተጠያቂዎቹን ለፍርድ ማቅረብ አለባቸው” ሲሉ የአምነስቲ ዳይሬክተር ዲፕሮስ ሙቼና ጠይቀዋል።

ጨምረውም “የህወሓት ባለስልጣናትና አዛዦችም በስራቸው ላሉ ኃይሎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ሆን ተብሎ የሚፈጸም ጥቃት ተቀባይነት የሌለውና የጦር ወንጀል መሆኑን ግልጽ ማድረግ አለባቸው። በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም ወገኖች በሚያካሂዱት ዘመቻ ዓለም አቀፍ ሕግጋትን ማክበር ይጠበቅባቸዋል። የሰላማዊ ሰዎች ደኅንነትና ጥበቃ ቀዳሚ ጉዳይ መሆን አለበት” ብለዋል።

ከሳምንት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በትግራይ ውስጥ በሚገኘው የአገሪቱ ሠራዊት ላይ ጥቃት መፈጸሙን በመግለጽ ወታደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ትዕዛዝ ከሰጡ በኋላ በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች ውጊያ እየተካሄደ መሆኑ ይታወቃል።

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *