ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ በርካታ ሐሰተኛ ምስሎች በማኅበራዊ ሚዲያው ላይ እየተጋሩ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል ላይ በከፈተው ወታደራዊ ዘመቻና ይህንኑ ተከትሎ እየወጡ ባሉ ዘገባዎች በርካታ ሰዎች ሐሳዊ መረጃዎችን ያጋራሉ፥ ይጋራሉ። ማኀበራዊ ሚዲያውም በዚህ ተሞልቷል።

የቢቢሲ <ፋክትቼክ ቡድን> አንዳንዶቹን ሐሳዊ ምሥሎች ነቅሶ አውጥቷቸዋል።

ምሥሎቹ በጭራሽ ከዚህ ጦርነት ጋር ተያያዥ አይደሉም። አንዳንዶቹ እውነት እንዲመስሉ ሆን ተብለው በልዩ ጥበብ የተቀናበሩ መሆናቸውን ተገንዝቧል።

ከእነዚህም መካከል በስፋት የተጋሩ የተጭበረበሩ 4 ፎቶዎች የሚከተሉት ናቸው።

1ኛ፦ የሚሳይል መቃወሚያ (ሚሳይል ዲፌንስ ሲስተም)

በማኀበራዊ ሚዲያው በርካታ ሰዎች ሩሲያ ሰራሽ ኤስ-400 (S-400) የሚሳይል መቃወሚያ (ሚሳይል ዲፌንስ ሲስተም) ምሥልን አጋርተዋል። ምሥሉን የተጠቀሙት ደግሞ የትግራይ ክልል ከኢትዯጵያ መንግሥት የሚሰነዘርበትን የአየር ጥቃት የሚከላከልበት አድርገው ነው።

ከዚህም ባሸገር የሩሲያ ሰራሽ እሳት (አረር) የሚተፋ መሣሪያ (flamethrower system) አገልግሎት ላይ አንደዋለ አድርገው አሰራጨተዋል፤ አጋርተዋል፤ ተጋርተዋል።

ከእነዚህ ሐሳዊ ምሥሎች ስርም እንዲህ የሚል የምሥል ማስታወሻን አስፍረዋል፦ “ይህ የምትመለከቱት ፎቶ እንደሚያመለክተው ኢትዮጵያ እንደ አገር እንኳ እኛ በክልል ደረጃ ያለን የጦር መሣሪያ እንደሌላት ነው” ይላል።

“ትግራዊያን ራሳቸውን ከአየር ጥቃት ለመከላከል እየተጠቀሙበት ነው” ሲልም ያክላል።

ከመሣሪያው ፎቶ አጠገብ ደግሞ የትግራይ ልዩ ኃይል አባል የደንብ ልብስ የለበሰ የሚመስል ሰው ቆሞ ይታያል።

ቢቢሲ እንዳረጋገጠው ይህ ምሥል ተቀናብሮ የተሠራ ነው። ከመሣሪያው ፎቶ ጋር የትግራይ ልዩ ኃይል አባል ፎቶ ሆን ተብሎ ተጨምሮበት የታተመ ነው።

ለዚህም በቂ ማስረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል።

ከአካባቢው ካሉ የምሥል ጥላዎች በተቃራኒ የቅንብር ፎቶዎቹ ጥላ ወደ ተቃራኒ አቅጣጫ ማሳየቱ አንዱ ለፎቶ ሐሳዊነቱ ማሳያ ነው። አንዳንዶቹ የአካባቢው ምሥሎችም ከሌላው ጨለም ያሉ ናቸው። የብርሃን ምጣኒያቸው ልዩነትም ይህን ያሳብቃል።

ከዚህም ባሸገር በአንደኛው ፎቶ ላይ ወታደሩ ከከባቢያዊ ምሥሎች በተለየ የሱ ፎቶ ምጣኔ የተለጠጠ ሆኖ ይታያል።

የፎቶው ምንጭ በተደረገ የኦንላይን ፍተሻ ከየት እንደሆነ ተደርሶበታል። በደቡብ ሩሲያ አስትራካን ክልል ወታደሮች ልምምድ ከሚያደርጉበት ሥፍራ የተወሰደ ነው።

በሩሲያ ቋንቋ የተደገፈ ቪዲዯ ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነው። በመስከረም ወር የተወሰደው ይህ ተመሳሳይ ምሥል ተመሳሳይ የአየር መቃወሚያ አገልግሎት ላይ ሲውል ያሳያል።

ኤስ-400 (S-400) የአየር መቃወሚያ ሲስተም እጅግ ዘመናዊ የሚባል ከምድር ወደ አየር ተምዘግዛጊ የሚሳይል ሲስተም ሲሆን ከሩሲያ ሌላ ጥቂት የውጭ አገራት እጅ ውስጥ ካልሆነ እንደ ኢትዯጵያ ያለ አገር በእጁ የሚያስገባው መሣሪያ አይደለም።

ኢትዮጵያ ይህን መሣሪያ ከሸመቱ አገራት ተርታ የለችበትም።

“ኢትዮጵያ ኤስ-300 ዝርያዎችንም ሆነ ኤስ-400 መቃወሚያዎች ገዝታ አታውቅም። የአካባቢው አገራትም ይህ የላቸውም” ይላሉ ጀስቲን ብሮንክ። ጀስቲን በሎንዶን የሮያል ዩናይትድ ሰርቪስ ኢንስቲትዩት ባልደረባ ናቸው።

2ኛ፦ ተመትቶ ወደቀ የተባለው ተዋጊ ጄት

 

ብዙዎች የፌስቡክ ተጠቃሚዎች አንድ በትግራይ ክልል ተመትቶ ወደቀ የተባለ የጦር ጄት ምስል በስፋት ተጋርተውታል።

አንደኛው የፌስቡክ ገጽ ላይ “የትግራይ ልዩ ኃይል ከሰማይ ጥቃት እየደረሰበት ነው፤ ልዩ ኃይሉ የኢትዮጵያን የጦር ጄት አውድሞታል። ሌሎች ልዩ ኮማንዶ አባላትንም ገድሏል፣ ጦርነቱም እንደቀጠለ ነው” ይላል።

ነገር ግን የቢቢሲ ምርመራ እንደሚያስረዳው ይህ ምሥል ከቶውኑም ከኢትዮጵያ አይደለም።

በሪቨርስ ኢሜጅ የፍለጋ ዘዴ ተመሳሳይ ምሥሎች ሌሎች ቦታዎች ተገኝተዋል።

በሐምሌ 2018 በኢራኑ ፕሬስ ቲቪ ሪፖርት ላይ የሳኡዲ የጦር ጄት በየመን መመታቱን የሚያሳይ ምሥል እንዲሁም በግንቦት 2015 የትዊተር ሰሌዳ ምሥል ሚግ 25 ፕሌን በሊቢያ ዚንታን ከተማ አቅራቢያ ያሳያል።

3ኛ፦ የተጭበረበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን አደጋ ፎቶ

አንዳንድ ሰዎች ከተከሰከሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የመንገደኞች አውሮፕላን ፎቶን ከሰሞኑ ጦርነት ጋር አስተሳስረው ሲጠቀሙበት ነበር።

ይህም ከዚህ ቀደም መንገደኞችን ጭኖ ወደ ናይሮቢ ሲያቀና ቢሾፍቱ አቅራቢያ የተከሰከሰውንና ከ150 ሰዎች በላይ የሞቱበትን ቦይንግ 737 ማክስ 8 ምሥል ጋር የተያያዘ ነው።

ይህን ምሥል የተጠቀሙበት ከጎረቤት አማራ ክልል የመጡ ወታደሮች ሬሳ በትግራይ የተገደሉ በማስመሰል ነው።

ነገር ግን ሌሎች ይህ ምሥል ምንም ከዚህ ውጊያ ጋር የሚያይዘው ነገር እንደሌለ ተረድተው ይህንኑ አጋልጠዋል።

በዚህም የተነሳ ብዙዎች ይህንን ምሥል እየሰረዙት ይገኛሉ።

4ኛ፦ ሚኒስትሯ ወታደሮችን ጭምብል አጥልቁ ብለዋል?

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሪፓብሊክ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሚኒስትር የሆኑት ወ/ሮ ሊያ ታደሰ በትዊተር ሰሌዳቸው ላይ ወታደሮች የአፍ እና አፍንጫ ጭንብል እንዲያጠልቁ ሲያበረታቱ የሚያሳይ ምሥል (ስክሪንሾት) በማኅበራዊ ሚዲያ ተጋርቷል።

ይህ ምሥል ሚኒስትሯ የኮቪድ ጥንቃቄ መመርያዎችን ለወታደሮች ያስተላለፉ ተደርጎ በማስመሰል ነው የተሰራጨው።

ከዚህ ሐሳዊ ምሥል ጋር የተጻፈው መልእክት እንዲህ ይነበባል፡ “ርቀታችንን ጠብቀን ሳኒታይዘር እና ማስካችንን በጥንቃቄ በማድረግ ጦርነቱ በሰላም እንዲጠናቀቅ የበኩላችንን አስተዋጽኦ እንድናበረክት ለማሳሰብ እወዳለሁ።”

ይህ የሚኒስትሯ የትዊተር ሰሌዳ መልዕክት የተፈበረከ እንጂ እውነት አይደለም።

በሚኒስትሯ የትዊተር የግል አካውንት ሰሌዳ ዝርዝርም ላይ የሚገኝ አይደለም።

ትክክለኛው የሚኒስትሯ የትዊተር መልዕክቶች ሚንስትሯ ትዊተር የሚጠቀሙት በአይፎን ስልክ እንጂ በአንድሮይድ ስልክ እንዳልሆነ ይጠቁማል።

ምንጭ ቢቢሲ

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *