በትግራይ ክልል ማይካድራ ከተማ በርካታ ዜጎች ተገድለዋል የሚል ሪፖርት መውጣቱን ተከትሎ “ግድያዎቹ መረጋገጥ ከቻሉ እንደ ጦር ወንጀል ይቆጠራል” በማለት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስጠንቅቋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኃላፊ ሚሼል ባችሌት በማይካድራ ከተማ ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ በስለት ተገድለዋል የሚለው ሪፖርትም እንዲጣራ ጠይቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ጭፍጨፋውን የፈፀሙት የህወሃት ታጣቂዎች ናቸው ቢሉም የትግራይ ክልል ባለስልጣናት በበኩላቸው በግድያዎቹ እጃችን የለበትም በማለት ውድቅ አድርገውታል።

የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደብረ ፅዮን ገብረ ሚካኤል (ዶክተር) ውንጀላዎቹ “መሰረት” የሌላቸው ናቸው ማለታቸውንም አጃንሰ ፍራንስ ፕሬስ እሳቸውን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በበኩላቸው የፌደራል መንግሥት የምዕራብ ትግራይን “ነፃ ካወጣ” በኋላ የህወሃት ታጣቂዎች በማይካድራ ከተማ በርካታ ንፁሃን ዜጎችን “በአሰቃቂ ሁኔታ ገድለዋል” ብለዋል።

የማይካድራ ከተማ በትግራይ ክልል ደቡብ ምዕራብ ዞን ትገኛለች።

የግድያውን ሪፖርት ያወጣው አምነስቲ ኢንተርናሽናል ግድያውን ማን እንደፈጸመው ለማረጋገጥ አለመቻሉን አመልክቷል። ነገር ግን ያነጋገራቸው የአይን እማኞች ከፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ጋር የሚዋጉትን የህወሓት ታማኝ ኃይሎች ጥቃቱን እንደፈጸሙ ይከሳሉ።

ግድያዎቹ መረጋገጥ ከቻሉም በፌደራል መንግሥትና በትግራይ ክልል መካከል በተነሳው ጦርነት የተገደሉ በርካታ ንፁሃን ዜጎች ያደርጋቸዋል።

ከሳምንት በላይ ባስቆጠረው ግጭት በትግራይ ክልል የስልክም ሆነ የኢንተርኔት አገልግሎት ባለመኖሩ ስለ ግጭቱ መረጃ ለማግኘት አዳጋች አድርጎታል።

ሚሼል ባችሌት እንዳሉት በኢትዮጵያ እየተከሰተ ያለው ሁኔታ ስጋት እንደፈጠረባቸው ጠቅሰው “ከዚህ በበለጠ ግፎች ከመፈፀማቸው በፊት ለመከላከል ያስችል ዘንድ ውጊያው መቆም ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ነው ብለዋል።

ጥቃት የደረሰባቸው እነማን ናቸው?

እንደ አምነስቲ ሪፖርት ከሆነ ግድያዎቹ የተፈፀሙት ጥቅምት 30/ 2013 ዓ.ም ምሽት ነው።

በማይካድራ ከተማ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በስለት ተወግተው ወይም ተቀጥቅጠው እንደተገደሉ አምነስቲ አረጋግጫለሁ ብሏል።

በከተማዋ “በየቦታው ወድው የሚታዩና በአልጋ ላይ የሚታዩ አስከሬኖችን አሰቃቂ ፎቶግራፎችና ቪዲዮዎችን የተረጋገጡ” ናቸው ብሏል።

ጥቃት የደረሰባቸው ግለሰቦች የቀን ሰራተኞች እንደሚመስሉ የተጠቀሰ ሲሆን በግጭቱም ምንም አይነት ተሳትፎ የላቸውም ብሏል። ከየት እንደመጡም ማረጋገጥ እንዳልተቻለም ድርጅቱ አክሎ ገልጿል።

የአይን እማኞችን ዋቢ አድርጌያለሁ ያለው አምነስቲ “ጥቃት የደረሰባቸው ግለሰቦች በስለታማ ነገሮች ለምሳሌም ያህል ቢላና ቆንጨራ ነው” ብለዋል። አንዳንድ የአይን እማኞች ከፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ጋር የሚዋጉትን የህወሓት ታማኝ ኃይሎች ሉግዲ በምትባል ቦታ መሸነፋቸውን ተከትሎ ጥቃቱን እንደፈጸሙ ይከሳሉ። የትግራይ ክልል ይህንን “መሰረት” የለውም በሚል አልተቀበለውም።

ከዚህም በተጨማሪ በመቀሌና በአዲግራት በደረሰ የአየር ጥቃት ንፁሃን ዜጎች መገደላቸውን ደብረፅዮን (ዶ/ር) ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ተናግረዋል።

“በርካቶች በየአቅጣጫው በመሮጥ ሸሽተዋል። የዚህ ግጭት ዋነኛ መዘዝ መፈናቀል ነው። እውነት ነው የሞቱም ሆነ የተጎዱ ሰዎች አሉ። ነገር ግን እስካሁን ቁጥሩን አናውቅም። ይህን ለመቆጣጠር በጣም ትልቅ ነው” ማለታቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ አስነብቧል።

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሻከረ የመጣው የፌደራልና የትግራይ ክልል መንግሥት ግንኙነት የማይታረቅ ደረጃ ደርሶ ከሳምንት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የትግራይ ልዩ ኃይል በክልሉ የሚገኘውን የመከላከያ ሰሜን ዕዝ ካምፕ ላይ ጥቃት ማድረሱን ገልፀው ጦርነት መከፈቱን አስታውቀዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ በአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርበው የመከላከያ ሠራዊት በኮማንድ ፖስት እየተመራ “አገሩን የማዳን ተልዕኮውን እንዲወጣ ትዕዛዝ ተሰጥቶታል” ብለዋል።

የትግራይ ክልል በበኩሉ በክልሉ የሚገኙት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰሜን ዕዝ ሰራዊት አባላትና አዛዦች ከትግራይ ክልል መንግሥት ጎን ለመሰለፍ ወስነዋል ማለቱ ይታወሳል።

ከዚህም በተጨማሪ የፌደራል መንግሥት የአየር ጥቃትም እያደረሰ ነው ተብሏል። በዚህም ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ወደ ጎረቤት አገር ሱዳን የተሰደዱ ሲሆን የሱዳን መንግሥትም በስደተኞች መጠለያ ካምፕ ውስጥ አስገባቸዋለሁ ብሏል።

ምንጭ ቢቢሲ,አምነስቲ

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *