ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ መከላከያ ሠራዊት ሕወሓት ላይ የኃይል እርምጃ እንዲወሰድ መታዘዙን መግለጻቸው ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ትላንት ማምሻውን በሰጡት መግለጫ በሁመራ፣ በዳንሻ እና በቅርቃር አካባቢዎች የአገር መከላከያ ሠራዊት እና የአማራ ክልል ልዩ ኃይልና ሚሊሻ “ሕወሓት ያሻውን ሳያደርግ የሞከራቸው ሙከራዎች ከሽፈዋል” ብለዋል።

የአገር መከላከያ ሠራዊትም “የተቃጣበትን ጥቃት በመመከት እንዲሁም በማክሸፍ የሕዝቦችን ደህንነት እና የአገሪቱን ሉዓላዊነት ለመጠበቅ ኃላፊነቱን እየተወጣ” እንደሆነ ገልጿል።

ከቅርቃር በቅርብ ርቀት የሚገኝ ቦታን በቁጥጥር ስር ማዋሉም ተገልጿል።

የትግራይ ክልል መንግሥት ትላንት ባወጣው መግለጫ በክልሉ የሚገኙት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰሜን ዕዝ ሠራዊት አባላትና አዛዦች ከትግራይ ክልል መንግሥት ጎን ለመሰለፍ መወሰናቸውን ገልጿል።

ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጽሕፈት ቤት በተገኘው መረጃ መሠረት፤ ከአገር መከላከያ ሠራዊት ተቀንሰው የነበሩ ሦስት መኮንኖች ወደ ሠራዊቱ እንዲመለሱ ከጠቅላይ ሚንስትሩ ትዕዛዝ ተሰጥቷቸዋል።

እነዚህም ሌ/ጀነራል ባጫ ደበሌ፣ ሌ/ጀነራል ዩሐንስ ገብረመስቀል እና ሌ/ጀነራል አበባው ታደሰ ናቸው።

በተጨማሪም የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አደም ፋራህ እና የገንዘብ ሚንስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ወቅታዊ ጉዳዮችን በማስመልከት ለውይይት ጅግጅጋ መሄዳቸው ተዘግቧል።

በትግራይ ክልል እና በፌደራል መንግሥት የነበረው ውጥረት ወደ ግጭትን ማምራቱን በማስመልከት የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ፣ የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ማይክ ፖምፔዮ እና ሌሎችም አካላት መግለጫ አውጥተዋል።

የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ባወጣው መግለጫ፤ “በፌደራል መንግሥትና በትግራይ ክልል መንግሥት መካከል የተፈጠረው አለመግባባት፣ ውጥረትና መካረር ገደቡን አልፎ ግልጽ የሆነ ወታደራዊ ግጭት መጀመሩ አሳዝኖናል። ይህ እንዳይሆን በማሰብ ሁለቱን አካላት አቀራርበን ለማወያየት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው ሳይሳካ መቅረቱም በእጅጉ ያሳዝናል” ብሏል።

የተፈጠረው ግጭት ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ መቆም እንዳለበትና የፌደራል መንግሥትም ሆነ የትግራይ ክልል መንግሥት ቅድሚያ መስጠት ያለባቸው ለአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት መሆኑ በመግለጫው ተመልክቷል።

“የብልጽግና ፓርቲ እና የሕወሓት መሪዎች በመካከላችሁ የተፈጠረው የፖለቲካ ልዩነት በመነጋገር የሚፈታ ስለሆነ አሁንም በጉዳዮቻችሁ ላይ በግልጽ በመነጋገር እንድትፈቱ ጥሪ እናስተላልፋለን” ሲል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤው መግለጫ ያትታል።

በተጨማሪም የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ እናቶች፣ አባገዳዎች እና ሌሎችም ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ሁለቱን ወገኖች ወደ ሰላማዊ ድርድር እንዲያመጡ መግለጫው አሳስቧል።

አሜሪካ እና የአውሮፓ ሕብረት

የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ማይክ ፖምፔዮ በትዊተር ገጻቸው፤ “ሕወሓት በትግራይ የመከላከያ ሠራዊት ካምፕ ላይ ጥቃት አድርሷል የሚለው ሪፖርት አሳስቦናል” ብለዋል።

የውጪ ጉዳይ ሚንስትሩ አክለውም “ሰላም እንዲመለስ እና ውጥረቱን እንዲረግብ አፋጣኝ እርምጃ እንዲወሰድ እናሳስባለን” ብለዋል።

የአውሮፓ ሕብረት የውጪ ጉዳይ እና ደህንነት ፖሊሲ ከፍተኛ ወኪል እና የአውሮፓ ሕብረት ኮሚሽን ምክትል ፕሬዘዳንት የሆኑት ጆሴፍ ቦሬል ፎንቴልስ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ “ወታደራዊ ግጭት መከሰቱ ለአገሪቱና ለቀጠናው መረጋጋትም አስጊ ነው” ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ጽፈዋል።

ዋነኛው ትኩረት መሆን ያለበት ውጥረቱን ማርገብና ችግሩን በሰላማዊ መንገድ መፍታት እንደሆነም ገልጸዋል።

ትላንት የአሜሪካ እና የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥታት፤ የትግራይና የፌደራል መንግሥት የገቡበትን ውጥረት ሊያረግቡ እንደሚገባ በኤምባሲዎቻቸው በኩል መግለጻቸው ይታወሳል።

አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ትላንት ባወጣው መግለጫ፤ ሁለቱም ወገኖች የገቡበትን ውጥረት እንዲያረግቡ ጥሪ አቅርቦ፤ ለሰላማዊ ሰዎች ደህንነት ቅድሚያ ሊሰጡ ይገባል ብሏል።

የዩናይትድ ኪንግደም ኤምባሲም ውጥረቱ በአፋጣኝ እንዲረግብ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ስም የጠየቀ ሲሆን፤ ሁለቱም ወገኖች የሰላማዊ ዜጎቻቸውን ደህንነት እንዲያስጠብቁ ጠይቋል።

የመብት ተሟጋቾች

የአገር ውስጥ ተቋሞች

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በፍጥነት እየተባባሰ የመጣው የትግራይ ክልል የጸጥታ ሁኔታ እንደሚያሳስበው በመግለጽ ክስተቱን በቅርበት እንደሚከታተለው አስታውቋል።

ዋና ኮሚሽነሩ ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ‘የፌደራልና የክልሉ የጸጥታ ኃይሎች የሲቪል ሰዎችን ደህንነት እና የሰብዓዊ መብቶችን በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ እንዲጠብቁና እንዲያከብሩ” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ኮሚሽነሩ አክለውም፤ በተለይም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በትግራይ ክልል ተፈጻሚ እንዲሆን የቀረበውን የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ረቂቅ አቃጅ ለመምከር በሚሰበሰብበት የዛሬው ዕለት፤ ምግብና መድኃኒት የመሳሰሉ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦቶችን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የስልክና ኢንተርኔት አገልግሎት እንዲሁም ትራንስፖርት ሙሉ በሙሉ እንዳይቋረጥ በማሳሰብ፤ ትግራይ ክልል በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ስደተኞች እንደሚያስጠልልም አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) በበኩሉ፤ በትግራይ ክልልና አዋሳኝ ቦታዎች ያለው እንቅስቃሴ የሰላማዊ ሕዝብን ሕይወትና አካላዊ ደህንነት ብሎም የሲቪል ንብረቶችን አደጋ ላይ የማይጥል እንዲሆንና ሁሉም ወገኖች ከግጭት እንዲቆጠቡ ጥሪ አቅርቧል።

ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የሲቪል ማኅበራት፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ተጽዕኖ ፈጣሪዎችና መላው ኢትዮጵያውያን ግጭቱ ተባብሶ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት በመንቀሳቀስ ልዩነቶች በውይይት እንዲፈቱ በሁሉም ወገኖች ላይ ግፊት እና ጫና እንዲያደርጉ ኢሰመጉ ጠይቋል።

መንግሥትም በየጊዜው የሚፈጠሩ ነገሮች ዙሪያ ተከታታይ መረጃዎችን ለሕዝብ ይፋ እንዲያደርግ ኢሰመጉ አሳስቧል።

ሁሉም የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎችና መገናኛ ብዙኃን፤ ሕዝብን ለግጭት የሚያነሳሱ እና ለሰብዓዊ መብቶች ጥሰት የሚዳርጉ የሐሰት ዜናዎችን እና የተዛቡ መረጃዎችን ከማሰራጨት እንዲቆጠቡ ኢሰመጉ ጥሪውን አቅርቧል።

ዓለም አቀፍ ድርጅቶች

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ሂውማን ራይትስ ዋች የአፍሪካ ዳይሬክተር ማውሲ ሴጋን፤ የፌደራልና የክልል መንግሥታት ሰብዓዊ መብትን ሳይጥሱ ግጭት ማርገብ አለባቸው ብለዋል።

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድምጹን ማሰማት እንዳለበትም አክለዋል።

“በትግራይ ክልል የስልክ እና ኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡ ክስተቱ በማኅበረሰቡ ላይ ስላሳደረው ጫና መረጃ እንዳይገኝ አድርጓል። ሕዝቡ ጤናውና ደህንነቱን በተመለከተ መረጃ እንዳያገኝም ያግዳል” ብለዋል።

ዳይሬክተሯ አያይዘውም፤ የስልክም ይሁን ኢንተርኔት መቋረጥ “መንግሥት ከሚሰጠው መረጃ ባለፈ ሕዝቡ ሐሳቡን እንዳያንሸራሽር ይገታል” ብለው፤ የቴሌኮም አገልግሎቶች በአፋጣኝ እንዲመለሱ አሳስበዋል።

ሌላው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አምንስቲ ኢንተርናሽናል፤ የምሥራቅና ደቡብ አፍሪካ ዳይሬክተር ዴፕሮሴ ሙቻናም መግለጫ አውጥተዋል።

“መከላከያ መላኩ በትግራይ ክልል እና በፌደራል መንግሥት መካከል ያለውም ውጥረት ያባብሳል። የሰዎችን ሕይወት አደጋ ላይ ከመጣሉም ባሻገር ሰብዓዊ መብቶች እንዲጣሱ በር ይከፍታል” ብለዋል።

በትግራይ ክልል ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ፤ ለፌደራል መንግሥትና ለትግራይ ክልል መንግሥትም አሳስበዋል።

“ሞትና የአካል ጉዳት እንዳይከተል ከፍተኛ ኃይል መጠቀም መገታት አለበት” ሲሉም በመግለጫው ጠይቀዋል።

ሰዎች እርስ በእርስ መረጃ እንዲለዋወጡ፣ የንግግር ነጻነት እንዲከበርና ሰብዓዊ መብት አለመጣሱን ለማረጋገጥ የሰልክና ኢንተርኔት አገልግሎቶች እንዲመለሱም ተጠይቋል።

ምንጭ ቢቢሲ

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *